ሕዝቅኤል 46 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእስራኤል መሪና የበዓላቱ አከባበር 1 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያስገባው ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ የሚያመለክተው በር በስድስቱ የሥራ ቀኖች ዝግ መሆን አለበት፤ ነገር ግን በሰንበት ቀንና በየወሩ መባቻ ቀን ይከፈታል። 2 መስፍኑ በመግቢያው ክፍል በኩል ከውጪ አደባባይ ወደ ውስጥ ገብቶ በቅጽሩ በር መቃን አጠገብ ይቆማል፤ ካህናቱ ደግሞ እርሱ ያዘጋጀውን የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕት ያቀርባሉ፤ መስፍኑም በመድረኩ ላይ እንዳለ ይሰግዳል፤ ከዚያ በኋላ እርሱ ይወጣል፤ የቅጽሩ በር ግን እስከ ምሽት ድረስ አይዘጋም። 3 በእያንዳንዱም ሰንበትና በየወሩም መባቻ ሕዝቡ ሁሉ በምሥራቁ መግቢያ በር በኩል ለእግዚአብሔር ይስገዱ። 4 “መስፍኑ በሰንበት ቀን በሙሉ ለሚቃጠል መሥዋዕት ምንም ነውር የሌለባቸውን ስድስት የበግ ጠቦቶችና አንድ የበግ አውራ ለእግዚአብሔር ያቅርብ። 5 ከእያንዳንዱም የበግ አውራ ጋር አንድ የኢፍ መስፈሪያ እህል ያምጣ፤ እንዲሁም ከእያንዳንዱ ጠቦት ጋር ለማቅረብ የፈለገውን ያኽል ያቅርብ፤ ከእያንዳንዱም ኢፍ መሥዋዕት ጋር አብሮ የሚቀርብ ሦስት ሊትር ዘይት ያምጣ። 6 በእያንዳንዱ የወር መባቻ ደግሞ ምንም ነውር የሌለባቸውን አንድ ወይፈን፥ ስድስት የበግ ጠቦቶችና አንድ የበግ አውራ ያቅርብ። 7 ከእያንዳንዱ ኰርማና ከእያንዳንዱ የበግ አውራ ጋር አንድ አንድ ኢፍ የእህል መባ ይሁን፤ እንዲሁም ከእያንዳንዱ የበግ ጠቦት ጋር የሚቀርበው መባ መስፍኑ ለመስጠት የፈቀደውን ያኽል ይሁን፤ ከእያንዳንዱም ኢፍ ጋር ሦስት ሊትር የወይራ ዘይት አብሮ ይቅረብ። 8 መስፍኑም ሲገባ በበሩ መተላለፊያ በኩል ገብቶ ሲወጣም በዚያው በኩል ይውጣ። 9 “በማናቸውም የበዓል ቀን ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ለመስገድ በሚመጡበት ጊዜ በሰሜን ቅጽር በር የገቡት በደቡብ ቅጽር በር ይውጡ፤ በደቡብ ቅጽር በር የገቡትም በሰሜን ቅጽር በር ይውጡ፤ ማንም ሰው በገባበት በር አይውጣ፤ ነገር ግን በአንጻሩ ባለው በሌላ በር መውጣት አለበት። 10 መስፍኑም ሕዝቡ በሚገቡበት ጊዜ ገብቶ፥ በሚወጡበት ጊዜ ይውጣ። 11 በታላላቅና በታናናሽ በዓላት ቀኖች ከእያንዳንዱ ኰርማና ከእያንዳንዱ የበግ አውራ ጋር የሚቀርበው የኽህል መባ አንድ የኢፍ መስፈሪያ ይሁን፤ ለእግዚአብሔር የሚሰግደው ሰው ከእያንዳንዱ የበግ ጠቦት ጋር የፈቀደውን ያኽል ያቅርብ። ከእያንዳንዱም የኢፍ መስፈሪያ መባ ጋር ሦስት ሊትር የወይራ ዘይት አብሮ ይቅረብ። 12 “በሥልጣን ላይ ያለው መስፍን በሙሉ የሚቃጠልም ሆነ ወይም የደኅንነት መሥዋዕት በበጎ ፈቃደኛነት በግሉ ለእግዚአብሔር ማቅረብ ቢፈልግ ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያስገባው የምሥራቁ በር ይከፈትለት፤ የመባውንም አቀራረብ በሰንበት ቀን በሚያደርገው ዐይነት ይፈጽም፤ እርሱም ወጥቶ ከሄደ በኋላ በሩ ይዘጋ።” በየዕለቱ የሚቀርብ መሥዋዕት 13 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “መስፍኑ በየማለዳው የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ነውር የሌለበት የአንድ ዓመት የበግ ጠቦት ማዘጋጀት አለበት። 14 ከእርሱም ጋር በየማለዳው ሳያስታጒል ሁለት ኪሎ ያኽል የእህል ቊርባንና ለምርጡ ዱቄት መለወሻ እንዲሆን አንድ ሊትር ዘይት ያዘጋጃል። ይህም የዘወትር ሥርዓት ይሆናል። 15 በዚህም ዓይነት የበጉ ጠቦት፥ የእህሉ ቊርባንና ዘይቱ በየማለዳው መቅረብ ያለበት የሚቃጠል መሥዋዕት ነው።” መስፍኑና የምድሪቱ ይዞታ 16 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በሥልጣን ላይ ያለው መስፍን ከርስቱ ላይ ቀንሶ ከልጆቹ ለአንዱ ቢሰጥ ያ ርስት ለርሱና ለራሱ ቤተሰብ ጸንቶ ይቈያል። 17 ነገር ግን በሥልጣን ላይ ያለው መስፍኑ የራሱ ድርሻ ከሆነው ርስት ከፍሎ ከአገልጋዮቹ ለአንዱ ቢሰጥ፥ በኀምሳ ዓመት ዞሮ በሚመጣው በኢዮቤልዩ ዓመት ለመስፍኑ ይመለስለት፤ ንብረቱ የራሱ ስለ ሆነ ይዞታው ለዘለዓለሙ የእርሱና የልጆቹ ብቻ መሆን አለበት። 18 በሥልጣን ላይ ያለው መስፍን ርስት ከሕዝቡ ነጥቆ መውሰድ የለበትም፤ ለልጆቹ ከፍሎ የሚሰጠው መሬት ለራሱ ከተመደበለት ድርሻ ላይ ብቻ መሆን አለበት፤ በዚህም ዐይነት የርስት ድርሻቸውን በመቀማት ሕዝቤን አይጨቊን።” መሥዋዕት የሚዘጋጁበት ልዩ ክፍል 19 ከዚያ በኋላ ያ ሰው በበሩ ጥግ መግቢያ በኩል በሰሜን ወዳለው የተቀደሱ የካህናት መደዳ ክፍሎች ወደ ሆኑት አመጣኝ፤ ከክፍሎቹም በስተ ምዕራብ መጨረሻ አንድ ቦታ አየሁ። 20 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “ይህ ቦታ ካህናቱ ለኃጢአትና ለበደል ማስተስረያ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውን ሥጋ የሚቀቅሉበትና የእህል መሥዋዕት የሚጋግሩበት ክፍል ነው፤ በዚህም ዐይነት በሕዝቡ ላይ ጒዳት እንዳይደርስ ከተቀደሰው መሥዋዕት ሁሉ ወደ ውጪው አደባባይ አይወጣም።” 21 ከዚያም በኋላ ያ ሰው ወደ ውጪው አደባባይ አምጥቶ በአራቱ ማእዘን አዞረኝ፤ በያንዳንዱም ማእዘን አንድ አደባባይ ነበር። 22 በአራቱ ማእዘኖች ያሉት ትናንሽ አደባባዮች እኩል ነበሩ፤ እያንዳንዳቸውም አርባ ክንድ ርዝመትና ሠላሳ ክንድ ወርድ ነበራቸው። 23 በእነዚህም አራት አደባባዮች ዙሪያ በውስጥ በኩል አጭር ግንብ ነበራቸው፤ በግንቦቹም ሥር የእሳት ማንደጃዎች ነበሩ። 24 ያም ሰው “እነዚህ ሁሉ የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች፥ ሕዝቡ የሚያቀርበውን መሥዋዕት የሚያበስሉባቸው ክፍሎች ናቸው” አለኝ። |