ሕዝቅኤል 45 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበርስት አከፋፈል ለእግዚአብሔር የተለየ ድርሻ 1 ምድሪቱ ለእያንዳንዱ ነገድ በርስትነት በምትከፋፈልበት ጊዜ አንድ ዕጣ ለእግዚአብሔር የተለየ ይሆናል፤ እርሱም ርዝመቱ ኻያ አምስት ሺህ ክንድ፥ ወርዱም ኻያ ሺህ ክንድ ይሆናል፤ ጠቅላላውም ክልል የተቀደሰ ይሆናል። 2 ከዚህም ክልል ውስጥ የእያንዳንዱ ማእዘን ርዝመት አምስት መቶ ክንድ ሆኖ አራት ማእዘን ያለው አንድ ቦታ ለቤተ መቅደሱ ይመደባል፤ በዚህም ክልል ዙሪያ ስፋቱ ኀምሳ ክንድ የሆነ ክፍት ቦታ ይኖራል። 3 ለእግዚአብሔር ከተከለለው ክልል ኻያ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመት፥ ዐሥር ሺህ ክንድ ወርድ ይለካል፤ እርሱም ከሁሉም የበለጠ ለተቀደሰው ቤተ መቅደስ መሥሪያ ይሆናል። 4 ይህ ከጠቅላላው መሬት የተቀደሰ ክፍል ሆኖ ወደ እግዚአብሔር ቀርበው በቤተ መቅደሱ ውስጥ ለሚያገለግሉት ካህናት የተደለደለ ነው፤ ቦታውም ለካህናቱ መኖሪያና ለቤተ መቅደሱ መሥሪያ ይሆናል። 5 ቀሪው አጋማሽ ማለትም ርዝመቱ ኻያ አምስት ሺህ ክንድ ወርዱ ዐሥር ሺህ ክንድ የሆነው ቦታ ደግሞ በቤተ መቅደስ ለሌሎች ልዩ ልዩ አገልግሎት ለተመደቡት ሌዋውያን ርስት ይሆናል፤ ለእነርሱ መኖሪያ የሚሆኑ ከተሞችም በዚያ ይሠራሉ። 6 ከተቀደሰውም ክልል ቀጥሎ ኻያ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመትና አምስት ሺህ ክንድ ወርድ ያለው ለእስራኤል ነገድ ሁሉ የሚሆን ከተማ መሥሪያ ይከለላል። በርስት አከፋፈል የመስፍኑ ድርሻ 7 የሀገሪቱም መሪ ድርሻ ከተቀደሰው ቦታና ከከተማው ክልል ቀጥሎ በሁለቱም በኩል ማለትም በስተምዕራብ እስከ ሀገሪቱ ድንበር ሲደርስ በስተ ምሥራቅም እስከ ሀገሪቱ ድንበር የሚደርስ ይከለላል፤ ርዝመቱም ለአንድ ነገድ የሚደርሰውን ድርሻ ያኽላል። 8 ይህም ክልል በእስራኤል ምድር መሪ ለሚሆነው መስፍን የርስት ድርሻ ይሆናል፤ ከዚህም በኋላ መሪዎች ሁሉ ሕዝቡን መጨቈን የለባቸውም፤ ነገር ግን ከሀገሪቱ ቀሪውን ምድር በሙሉ ለእስራኤል ነገዶች መተው ይኖርባቸዋል። የመስፍኑ መመሪያ ሕግ 9 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እናንተ የእስራኤል መሪዎች! እነሆ ለረጅም ጊዜ ኃጢአት ስትሠሩ ኖራችኋል፤ አሁን ግን ግፍንና ጭቈናን አቁሙ! ቅንና ትክክል የሆነውን ነገር ሥሩ! ሕዝቤ እንደገና ከምድራቸው ተፈናቅለው እንዲባረሩ አታድርጉ! ይህን የምነግራችሁ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ። 10 “እያንዳንዱ ሰው ትክክለኛ ሚዛንና መለኪያ እንዲሁም እኩል የሆነ መስፈሪያ ይኑረው። 11 “የመስፈሪያዎች ሁሉ አማካኝ መለኪያ ጎሞር ይሁን፤ የደረቅ ነገሮች መስፈሪያ የሆነው ኢፍ፥ የፈሳሽ ነገሮች መለኪያ ከሆነው ባት ጋር እኩል መሆን አለበት፤ በዚህም ዐይነት አንድ ጎሞር ከዐሥር ኤፋና ከዐሥር ባት ጋር እኩል ይሆናል። 12 “ሚዛናችሁም፥ ኻያ ጌራህ አንድ ሰቅል፥ ሥልሳ ሰቅል አንድ ምናን ይሁን፤ 13 “የምታቀርቡት መሥዋዕት ከእያንዳንዱ ጎሞር ስንዴ አንድ ስድስተኛ ኢፍ፥ ከእያንዳንዱ ጎሞር ገብስም አንድ ስድስተኛ ኢፍ ነው። 14 ከዘይትም የተመደበው ከያንዳንዱ ቆሮስ አንድ ዐሥረኛ ባት ነው። (አንድ ቆሮስ፥ አንድ ጎሞር ወይም ዐሥር ባት ማለት ነው) 15 እንዲሁም ከእስራኤል የበግ መንጋዎች መካከል ከየሁለት መቶ በግ የተመደበው አንድ በግ ነው፤ ይህም ለእነርሱ የኃጢአት ማስተስረያ ይሆን ዘንድ ከእህል ቊርባን ጋር የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርብ ነው፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 16 በምድሪቱ የሚኖሩ ሕዝብ በሙሉ ይህን ሁሉ የእስራኤል መሪ ለሆነው ይሰጣሉ፤ 17 ለሚቃጠለው መሥዋዕት፥ ለእህል ቊርባንና ለመጠጥ ቊርባን በወር መባቻ፥ በሰንበቶች፥ በተወሰኑትም የእስራኤል ሕዝብ በዓላት እንዲቀርቡ የሚያስፈልጉትን ማዘጋጀት የመሪው ግዴታ ነው፤ ለእስራኤላውያን የኃጢአት ማስተስረያ ይሆን ዘንድ ስለ ኃጢአት የሚቀርበውን መሥዋዕት፥ የእህሉን ቊርባን የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የደኅንነትን ቊርባን ማዘጋጀት አለበት።” የበዓላት አከባበር ( ዘፀ. 12፥1-20 ፤ ዘሌ. 23፥33-43 ) 18 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የመጀመሪያው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን ምንም ነውር የሌለበት አንድ ወይፈን በመሠዋት ቤተ መቅደሱን ታነጻለህ። 19 ካህኑ ከዚህ የኃጢአት ስርየት መሥዋዕት ጥቂት ደም ወስዶ የቤተ መቅደሱን መቃኖች፥ የመሠዊያውን እርከን አራት ማእዘኖችና ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያስገቡትን የቅጽር በሮች መቃኖች ይቀባል፤ 20 ማንም ሆን ብሎ ባለማሰብ ወይም ባለማወቅ ስለ ሠራው ኃጢአት ሁሉ በሰባተኛው ቀን እንደዚሁ ታደርጋለህ፤ በዚህ ሁኔታ ቤተ መቅደሱ እንዲቀደስ ታደርጋለህ። 21 “የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካን በዓል ታከብራላችሁ፤ በዚህም በዓል አከባበር እስከ ሰባት ቀን ድረስ እርሾ ያልነካው ቂጣ ትበላላችሁ። 22 በበዓሉም ቀን በሥልጣን ላይ ያለው መስፍን ስለ ራሱና ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ስርየት አንድ ኰርማ ያዘጋጃል። 23 በዓሉ በሚከበርባቸው ሰባት ዕለቶች በእያንዳንዱ ቀን ምንም ነውር የሌለባቸውን ሰባት ኰርማዎችና ሰባት የበግ አውራዎች በሙሉ ለሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር የሚቀርቡትን ያዘጋጃል፤ ከዚህም ጋር በእያንዳንዱ ዕለት ለኃጢአት ስርየት መሥዋዕት የሚሆን አንድ የፍየል አውራ ያዘጋጃል። 24 እያንዳንዱ ኰርማና እያንዳንዱ የበግ አውራ በሚሠዋበት ጊዜ አንድ አንድ የኤፋ መስፈሪያ እህልና ሦስት ሦስት ሊትር የወይራ ዘይት አብሮ ይቀርባል። 25 “ሰባተኛው ወር በገባ በዐሥራ አምስተኛው ቀን መከበር ለሚጀምረው የዳስ በዓል፥ መስፍኑ በሰባቱ ቀኖች በእያንዳንዱ ዕለት ለኃጢአት ስርየትና በሙሉ ለሚቃጠል ተመሳሳይ መሥዋዕት ያዘጋጃል፤ የእህሉና የዘይቱም መሥዋዕት በተመሳሳይ ሁኔታ ይቀርባል።” |