ሕዝቅኤል 44 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየምሥራቁ ቅጽር በር አገልግሎት 1 ያም ሰው በስተ ምሥራቅ በኩል ወደሚገኘው ወደ ቤተ መቅደሱ ውጪ በር ወሰደኝ፤ በሩም ተዘግቶ ነበር፤ 2 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ “ይህ በር እንደ ተዘጋ ይኖራል እንጂ ከቶ አይከፈትም፤ የእስራኤል አምላክ እኔ እግዚአብሔር የገባሁበት ስለ ሆነ፥ ማንም በዚህ በር መጠቀም አይችልም፤ ስለዚህም እንደ ተዘጋ ይኖራል። 3 የሆነ ሆኖ የሕዝቡ መሪ የተቀደሰውን የመሥዋዕት ኅብስት ለመብላት በዚያ መቀመጥ ይችላል፤ በመግቢያውም ክፍል ውስጠኛ ጫፍ በሚገኘው መተላለፊያ በኩል መግባትና መውጣት ይፈቀድለታል።” ወደ ቤተ መቅደሱ ስለ መግባትና ከዚያም ስለ መውጣት የተደነገገ ሕግና ሥርዓት 4 ከዚያም በኋላ ያ ሰው በሰሜኑ ቅጽር በር በኩል አድርጎ ወደ ቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ወሰደኝ፤ በዚያም ሆኜ ስመለከት የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በክብሩ ተሞልቶ አየሁ፤ እኔም በግንባሬ ተደፋሁ፤ 5 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! የምትሰማውንና የምታየውን ነገር ሁሉ ልብ ብለህ አስተውለው፤ እነሆ እኔ ስለ ቤተ መቅደሱ ሕግና ሥርዓት ሁሉ እነግርሃለሁ፤ በቤተ መቅደሱ ውስጥ መግባትና መውጣት የሚፈቀድላቸው ምን ዐይነት ሰዎች እንደ ሆኑ አስተውል። 6 “ ለዐመፀኞቹ ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፦ ‘የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፥ ክፉ አድራጎታችሁን ሁሉ አስወግዱ፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 7 ስብንና ደምን ለእኔ የምግብ ቊርባን አድርጋችሁ በምታቀርቡበት ጊዜ ሊታዘዙኝ ፈቃደኞች ያልሆኑትን ያልተገረዙ ባዕዳን ወደ ተቀደሰው ስፍራዬ በማስገባት ቤተ መቅደሴን አርክሳችኋል፥ በረከሰውም ተግባራችሁ ሁሉ ቃል ኪዳኔን አፍርሳችኋል። 8 የተቀደሰ ቊርባኔንም በኀላፊነት አልጠበቃችሁም፤ እንዲያውም በተሰጣችሁ የኀላፊነት ቦታ ላይ ባዕዳንን መደባችሁበት።’ ” 9 ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሊታዘዙኝ ፈቃደኞች ያልሆኑት ያልተገረዙ ባዕዳን ሁሉ፥ በእስራኤል ሕዝብ መካከል የሚኖሩት እንኳ ቢሆኑ ወደተቀደሰው ስፍራዬ እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም።” የሌዋውያን ከክህነት አገልግሎት መባረር 10 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “ከሌሎቹ የእስራኤል ሕዝብ ጋር እኔን ከድተው ለጣዖታት የሰገዱትን ሌዋውያንን እቀጣለሁ፤ 11 እነርሱ በቤተ መቅደሱ በር ጠባቂነት፥ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ሰዎች የሚያቀርቡአቸውን መሥዋዕቶች በማረድ፥ እንዲሁም ሰዎችን በማገልገል እንዲሠሩ ይፈቅድላቸዋል። 12 ነገር ግን እነርሱ ራሳቸው የጣዖት አምልኮ ሥርዓት መሪዎች በመሆን ሕዝቡን ወደ ኃጢአት ስለ መሩ መቀጣት እንደሚገባቸው በራሴ ምዬአለሁ” ይላል ልዑል እግዚአብሔር። 13 “በክህነት ለማገልገል ወደ እኔ አይቀርቡም፤ በጣም ወደ ተቀደሰው ቅዱስ ቊርባኔም አይቀርቡም፤ እነርሱም ለፈጸሙት አጸያፊ ተግባራቸው አሳፋሪ ውጤት ተጠያቂዎች ይሆናሉ። 14 ስለዚህ በክህነት ሳይሆን በቤተ መቅደሱ ውስጥ ያለውን ሌላውን ተግባር ሁሉ እንዲያከናውኑ እመድባቸዋለሁ።” ለክህነት አገልግሎት ተገቢ የሆኑ ካህናት 15 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ሌሎቹ የእስራኤል ሕዝብ እኔን ከድተው ከፊቴ ሲርቁ፥ በቤተ መቅደስ በታማኝነት ጸንተው እኔን ሲያገለግሉ የኖሩና ነገዳቸው ከሌዊ ወገን ሆኖ ከሳዶቅ የተወለዱ ካህናት አሉ፤ ስለዚህም ስብና የመሥዋዕት ደም በማቅረብ በፊቴ ቆመው ሊያገለግሉኝ የሚገባቸው እነርሱ ናቸው፤ 16 እኔን ለማገልገል ወደ ተቀደሰው ቦታዬ የሚገቡና ወደ ገበታዬ የሚቀርቡ እነርሱ ናቸው። እነርሱም ትእዛዜን ይጠብቃሉ። 17 በቤተ መቅደሱ ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያደርሰውን ቅጽር በር በሚገቡበት ጊዜ ከበፍታ የተሠራ ልብስ መልበስ ይኖርባቸዋል፤ በውስጠኛው አደባባይም ሆነ በቤተ መቅደስ በሚያገለግሉበት ጊዜ ማናቸውንም ከበግ ጠጒር የተሠራ ነገር መልበስ የለባቸውም። 18 በራሳቸው ላይ ከበፍታ የተሠራ መጠምጠሚያ ይጠምጥሙ፤ በወገባቸውም ከበፍታ የተሠራ የውስጥ ልብስ ይልበሱ፤ ማናቸውም ላብ የሚያመጣ መታጠቂያ አይታጠቁ። 19 ሕዝቡ ወደሚገኙበት ወደ ውጪው አደባባይ ከመውጣታቸው በፊት በቤተ መቅደስ ለአገልግሎት የተጠቀሙባቸውን አልባሳት አውልቀው በተቀደሱት ዕቃ ቤቶች ማኖርና ለራሳቸውም ሌላ ልብስ መልበስ አለባቸው፤ ይህንንም የሚያደርጉት ሕዝቡ ያልተፈቀደለትን የእነርሱን የተቀደሰ ልብስ ነክቶ እንዳይጐዳ ነው። 20 “ካህናቱ ራሳቸውን መላጨትም ሆነ ጠጒራቸውን ማሳደግ አይገባቸውም፤ ነገር ግን ፀጒራቸውን በሚገባ ሁኔታ ያስተካክሉ። 21 ካህናቱ ወደ ውስጠኛው አደባባይ በሚገቡበት ጊዜ ማናቸውንም ዐይነት የወይን ጠጅ አይጠጡ። 22 ካህን የሆነ ሁሉ ባልዋ የሞተባትን ወይም ከባልዋ የተፋታችውን ሴት ማግባት አይፈቀድለትም፤ ነገር ግን ድንግል የሆነችውን እስራኤላዊት ልጃገረድ ወይም ካህን የሆነ ባልዋ የሞተባትን ሴት ማግባት ይችላል። 23 “ካህናቱ ለሕዝቤ ቅዱስ የሆነውንና ያልሆነውን ንጹሕ የሆነውንና ርኩስ የሚባለውን ነገር እንዲለዩ ያስተምሩአቸው። 24 ሕግን በሚመለከት አከራካሪ ነገር በሚነሣበት ጊዜ፥ ደንቡ በሚያዝዘው መሠረት ካህናቱ ይወስኑላቸው፤ በሕጌና ሥርዓቴ መሠረት በዓሎቼን፥ እንዲሁም ዕለተ ሰንበትን በመቀደስ ይጠብቁ። 25 “ከወላጆቹ አንዱ፥ ከልጆቹ አንዱ፥ ወይም ወንድሙ ወይም ያላገባች እኅቱ ካልሆኑ በቀር ማንኛውም ካህን የሌላ ሰው ሬሳ በመንካት ራሱን ማርከስ አይገባውም፤ 26 ይህን ካደረገ ግን ከነጻም በኋላ እንኳ ሰባት ቀን መቈየት አለበት፤ 27 ለአገልግሎት ወደ ውስጠኛው አደባባይ፥ ወደ መቅደሱ በሚገባበት ቀን ለኃጢአቱ መሥዋዕት ያቅርብ፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 28 “ይህ የካህናቱ ርስት ነው፤ ይህም ማለት እኔ ርስታቸው ነኝ፤ እኔ ይዞታቸው ስለ ሆንኩ በእስራኤል ምንም ይዞታ አይሰጣቸውም። 29 የእህሉ መሥዋዕት፥ የኃጢአትና የበደል ስርየት መሥዋዕት ለእነርሱ ምግብ ይሁንላቸው፤ በእስራኤል ምድር ለእኔ ተለይቶ የተቀደሰውን ማናቸውንም መባ ሁሉ ይቀበሉ። 30 የመከር መጀመሪያ የሆነውን ያማረውን በኲራትና ለእኔ የቀረበውን ስጦታ ሁሉ ካህናቱ ይውሰዱ፤ ሕዝቡም ሁልጊዜ እህል ሲፈጩ የዱቄቱን በኲራት ለካህናቱ መባ አድርገው ያበርክቱ፤ እኔም ይህንን ሁሉ የሚያደርጉትን ሕዝብ ቤታቸውን በበረከት እሞላዋለሁ። 31 ካህናቱ ሞቶ የተገኘውን ወይም ሌላ አውሬ የገደለውን የወፍ ወይም የእንስሳ ሥጋ አይብሉ።” |