Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 43 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የእግዚአብሔርን ክብር የሚገልጠው ደማቅ ብርሃን ወደ ቤተ መቅደስ መመለሱ

1 ያ ሰው በምሥራቅ አቅጣጫ ወደሚገኘው የቅጽር በር ወሰደኝ፤

2 እዚያም የእስራኤል አምላክ ክብር ከወደ ምሥራቅ እየተገለጠ ነበር፤ ድምፁም እንደ ኀይለኛ የውሃ ማዕበል ነበር፤ የክብሩ ነጸብራቅም በምድር ላይ አበራ።

3 ይህም ራእይ ከዚህ በፊት እግዚአብሔር ኢየሩሳሌምን ለማጥፋት በመጣ ጊዜ ያየሁትን ይመስል ነበር፤ በኬባር ወንዝ አጠገብ ካየሁትም ራእይ ጋር ይመሳሰላል፤ በዚያን ጊዜ በግንባሬ ተደፋሁ።

4 የእግዚአብሔር ክብር በምሥራቁ የቅጽር በር በኩል አልፎ ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ።

5 የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ላይ አነሣኝ፤ ወስዶም ወደ ውስጠኛው አደባባይ አስገባኝ፤ ቤተ መቅደሱም በእግዚአብሔር ክብር ተሞልቶ ነበር፤

6 በዚያም ያ ሰው በአጠገቤ ቆሞ ነበር፤ እግዚአብሔርም ከቤተ መቅደሱ እንዲህ እያለ ሲናገረኝ ሰማሁ፤

7 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ይህ በእስራኤላውያን መካከል ለዘለዓለም በምኖርበት ዙፋኔና የእግሬ ማሳረፊያ ነው፤ እስራኤላውያንና ንጉሦቻቸው ከእንግዲህ ወዲህ ጣዖት በማምለክና በንጉሦቻቸው ሞት ጊዜ በሚያደርጉአቸው ድርጊቶች ስሜን አያሰድቡም።

8 ነገሥታቱ የቤተ መንግሥታቸውን መድረኮችና መቃኖች ወደ ቤተ መቅደሴ መድረኮችና መቃኖች አስጠግተው ስለ ሠሩ፥ የእኔን ቤትና የእነርሱን ቤት የሚለይ አንድ ግንብ ብቻ ሆኖአል፤ በፈጸሙትም አጸያፊ ድርጊት ሁሉ ቅዱስ ስሜን አሰድበዋል፤ ከዚህም የተነሣ በቊጣዬ አጠፋኋቸው።

9 ከእንግዲህ ወዲህ ግን ለጣዖቶች መስገዳቸውን ማቆምና የንጉሦቻቸውንም ሬሳ ከዚህ ማስወገድ አለባቸው፤ ይህን ቢያደርጉ እኔ በእነርሱ መካከል ለዘለዓለም እኖራለሁ።”

10 ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ለእስራኤል ሕዝብ ስለ ቤተ መቅደሱ አሠራር ንገራቸው፤ ንድፉንም ያጥኑ፤ ኃጢአት የሞላበት ሥራቸውንም በማስታወስ እንዲያፍሩ አድርጋቸው።

11 ባደረጉት ነገር ሁሉ የሚያፍሩ ከሆነ ስለ ቤተ መቅደሱ አሠራር ንድፍ፥ ስለ አደረጃጀቱ ስለ መውጫዎቹና ስለ መግቢያዎቹ፥ ስለ አጠቃላይ፥ አሠራሩ ሁኔታ፥ ስለ ሥነ ሥርዓቱ፥ ስለ ሕጎቹ ሁሉ አስረዳቸው፤ አጠቃላይ ንድፉን አጥንተው ሥርዓቱን ሁሉ ተግባራዊ ያደርጉ ዘንድ በእነርሱ ፊት ጻፈው።

12 የቤተ መቅደሱም ሕግ ይህ ነው፤ በተራራው ጫፍ ላይ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ያለው ክልል በሙሉ እጅግ የተቀደሰ ይሆናል።”


የመሠዊያው አሠራር

13 የመሠዊያውም ልክ እንደሚከተለው ነው፦ መሠዊያው ያረፈበት አንድ ረጅም ክንድ ርዝመትና አንድ ረጅም ክንድ ወርድ ሲሆን የዙሪያ ጠርዙም ስፋት አንድ ስንዝር ነው፤ ይህም ረጅም ክንድ በሌላው አንድ ክንድ ከጋት ይሆናል፤ ይህም የመሠዊያው ከፍታ ነው።

14 መሬት ላይ ካረፈው መሠረት ተነሥቶ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ ከፍታው ሁለት ክንድ፥ ወርዱ አንድ ክንድ ነበር። ከትንሹ እርከን እስከ ትልቁ እርከን ድረስ ከፍታው አራት ክንድ፥ ወርዱ አንድ ክንድ ነበር።

15 መሥዋዕቱ የሚቃጠልበት ይህ የላይኛው መጨረሻ እርከን አራት ክንድ ከፍታ ነበረው፤ በአራቱ ማእዘኖች ላይ ያሉት የመሠዊያው ቀንዶች ከመሠዊያው ጫፍ ላይ ካለው ክፈፍ በላይ ከፍ ያሉ ነበሩ።

16 እሳቱ የሚነድበት ክፍል አራት ማእዘን ሲሆን የያንዳንዱ ማእዘን ርዝመት ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበር።

17 የላይኛው እርከን እንደ ሌሎቹ እኩል አራት ማእዘን ነበረው፤ እነርሱም ዐሥራ አራት ክንድ ርዝመትና ዐሥራ አራት ክንድ ወርድ ሲሆኑ የጠርዙ ዙሪያ ግማሽ ክንድ ስፋት ነበረው፤ የማረፊያውም ዙሪያ አንድ ክንድ ስፋት ነበረው፤ መወጣጫዎቹም በስተምሥራቅ በኩል ነበሩ።


የመሠዊያው መቀደስ

18 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ‘የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለማቅረብና በእርሱ ላይ ደምን ለመርጨት ይህ መሠዊያ በተሠራ ጊዜ በመሠዊያው ላይ የሚፈጸመው ሥነ ሥርዓት እንደሚከተለው ይሆናል።

19 በፊቴ ቆመው እኔን ለሚያገልገሉ የሌዊ ነገድ ከሆነው ከሳዶቅ ዘር ለተወለዱ የኃጢአት ሥርየት መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡ ዘንድ ለእነርሱ አንድ ወይፈን ትሰጣቸዋለህ፤’ ይላል ልዑል እግዚአብሔር።

20 አንተም ከደሙ ትንሽ ወስደህ በመሠዊያው ጫፍ በአራቱ ማእዘን ያሉትን የመሠዊያውን ቀንዶች በመሠዊያው እርከን ላይ ያሉትን አራት ማእዘኖችና የመሠዊያውን ጠርዝ ሁሉ ትቀባቸዋለህ፤ በዚህም ሁኔታ መሠዊያውን ታነጻውና ትቀድሰዋለህ።

21 ለኃጢአት ስርየት መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውንም ኰርማ ወስደህ ለቤተ መቅደሱ ከተከለለው የተቀደሰ ቦታ ውጪ ለዚህ በተወሰነው ስፍራ ታቃጥለዋለህ።

22 በማግስቱ ምንም ነውር የሌለበትን አንድ አውራ ፍየል ወስደህ የኃጢአት ስርየት መሥዋዕት አድርገህ ታቀርበዋለህ፤ በኰርማውም ደም ባደረግኸው ዐይነት በፍየሉ ደም መሠዊያውን ታነጻለህ።

23 ይህንን ሁሉ ከፈጸምክ በኋላ ነውር የሌለባቸውን አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ ከመንጋው ወስደህ፥

24 ሁለቱንም ወደ እኔ ወደ እግዚአብሔር ታቀርባቸዋለህ፤ ካህናቱም ጨው ከነሰነሱባቸው በኋላ ለእኔ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው ያቀርቡአቸዋል።

25 ሰባት ቀን ሙሉ በእያንዳንዱ ዕለት አንድ ፍየል፥ ከመንጋው አንድ ወይፈንና፥ አንድ የበግ አውራ፥ የኃጢአት ስርየት መሥዋዕት አድርገህ ታቀርባለህ፤ እነዚህም ሁሉ ነውር የሌለባቸው መሆን አለባቸው።

26 መሠዊያው የነጻ ይሆን ዘንድ ለሰባት ቀን የሚቀደስበትን ሥርዓት ያካሄዳሉ፤ በዚህም መሠዊያው የተቀደሰ ይሆናል።

27 እነዚህ ቀኖች ካለፉ በኋላ ከስምንተኛው ቀን ጀምሮ ካህናቱ የሚቃጠልና የደኅንነት መሥዋዕታችሁን ያቀርባሉ፤ እኔም እቀበላችኋለሁ፤” ይላል ልዑል እግዚአብሔር።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告