ሕዝቅኤል 41 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ቀጥሎም የቤተ መቅደሱ ማእከል ወደ ሆነው የተቀደሰ ስፍራ አስገባኝ፤ ወደ እርሱ የሚወስደውንም መተላለፊያ ሲለካ የሁለቱ ጐን ትይዩ ርዝመት ስድስት ክንድ ሆነ። 2 ወርዱም ዐሥር ክንድ ሆነ፤ በግራና ቀኝ የሚገኙትም ግንቦች የእያንዳንዱ ውፍረት አምስት ክንድ ነበር፤ የተቀደሰው ስፍራ ሲለካ ርዝመቱ አርባ ክንድ፥ ወርዱም ኻያ ክንድ ሆነ። 3 ከዚያም አልፎ ወደ ውስጠኛው ክፍል ገባ፤ ወደ እርሱ የሚያስገባውንም መተላለፊያ ሲለካው ርዝመቱ ሁለት ክንድ ወርዱ ስድስት ክንድ ሆነ፤ በግራና ቀኝ የሚገኙትም ግንቦች የእያንዳንዱ ውፍረት ሰባት ክንድ ሆነ። 4 ከመካከለኛው ክፍል ባሻገር ያለውን ውስጠኛ ክፍል ከማእዘን እስከ ማእዘን ሲለካ ርዝመቱ ኻያ ክንድ ወርዱም ኻያ ክንድ ሆነ፤ ከዚያም በኋላ “ይህ ቅድስተ ቅዱሳን ነው” አለኝ። በቤተ መቅደሱ ጥግ ዙሪያውን የተሠሩ ክፍሎች 5 ያ ሰው የቤተ መቅደሱን ሕንጻ የውስጠኛ ግንብ ሲለካ ውፍረቱ ስድስት ክንድ ሆነ፤ ከዚህም ግንብ ጋር ተጠግተው በቤተ መቅደሱ ዙሪያ የተሠሩና የእያንዳንዱ ወርድ አራት ክንድ የሆነ ብዙ ክፍሎች ነበሩ። 6 እነዚህም ክፍሎች አንዱን በአንዱ ላይ በመቀጠል ሦስት ፎቅ ሆነው ተሠርተው፥ እያንዳንዱ ፎቅ ሠላሳ ክፍሎች ነበሩት፤ በእያንዳንዱ ፎቅ ላይ ያለው የቤተ መቅደሱ ውጫዊ ግንብ በታችኛው ካለው ፎቅና ግንብ ይልቅ የሳሳ ነበር፤ ይህም የሆነበት ምክንያት በቤተ መቅደሱ ሕንጻ ላይ ሳያርፍ፥ ክፍሎቹ የተደገፉት በዚያው በዋናው ግንብ ስለ ነበር ነው። 7 የታችኛው ግድግዳ ከፎቁ ግድግዳ የወፈረ ነው፤ ሆኖም ከውጪ ሲመለከቱት ከላይ እስከ ታች ያለው ግድግዳ እኩል ውፍረት ያለው ይመስላል። ግድግዳዎቹ ከታች ወደላይ እየሳሱ ስለሚሄዱ ወደ ላይ በተወጣ ቊጥር ክፍሎቹ እየሰፉ ይሄዳሉ። መወጣጫዎቹም ከምድር ወደ ላይኛው ፎቅ የሚወጡት በመካከለኛው ፎቅ በኩል አድርገው ነው። 8 የቤተ መቅደሱ መሠረት ስድስት ክንድ ከፍ ያለ ነበር፤ የውጪዎቹ ክፍሎችም መሠረት በዚያው ልክ ነበር። 9-10 የውጪው ክፍሎች ግድግዳ ውፍረት አምስት ክንድ ነበር፤ ከቤተ መቅደሱ ጐን ካሉት ክፍሎችና ከሚቀጥሉት ሕንጻዎች መካከል ባዶ ቦታ ነበር፤ የዚህም ባዶ ቦታ ስፋት በሃያ ክንድ ቤተ መቅደሱን ይዞር ነበር። 11 በቤተ መቅደሱ ጐን ያሉት ክፍሎች በሮቻቸው የሚከፈቱት ወደ ባዶው ቦታ አቅጣጫ ሲሆን አንዱ በሰሜን በኩል ሌላው ደግሞ በደቡብ በኩል ይከፈታል፤ የተተወውም ባዶ ቦታ ዙሪያው አምስት ክንድ ነበር። 12 በምዕራብ በኩል በባዶው ቦታ ጫፍ አንድ ሕንጻ አለ፤ የሕንጻው ግድግዳ ውፍረት ዙሪያው አምስት ክንድ፥ ወርዱ ሰባ ክንድ፥ ርዝመቱ ደግሞ ዘጠና ክንድ ነው። የቤተ መቅደሱ ሕንጻ አሠራርና ልክ 13 ያ ሰው ቤተ መቅደሱን ሲለካ አንድ መቶ ክንድ ሆኖ አገኘው፤ ከቤተ መቅደሱ በኋላ በኩል ባዶው ቦታውን አቋርጦ በስተ ምዕራብ እስካለው የሕንፃው መጨረሻ ድረስ ሲለካ በአንድነት ርዝመቱ አንድ መቶ ክንድ ሆነ። 14 ከቤተ መቅደሱም በምሥራቅ በኩል ባለው በር ፊት ለፊት ያለው ርዝመት በሁለቱም አቅጣጫ ያሉትን ክፍት ቦታዎች ጨምሮ መቶ ክንድ ሆነ፤ 15 በሁለቱም በኩል ያሉትን መተላለፊያዎች ጨምሮ በምዕራብ በኩል ያለውን የሕንጻውን ርዝመት ሲለካው አንድ መቶ ክንድ ሆነ። የቤተ መቅደሱ መተላለፊያ፥ ቅዱሱ ስፍራና ወደ ውስጥ ዘልቆ የሚገኘው ቅድስተ ቅዱሳን፥ 16 ሦስቱም ወደ ውስጥ ገባ ያሉ በዙሪያቸው ክፈፍ ያሉአቸው መስኮቶች ነበሩአቸው፤ ግድግዳዎቻቸውም ከወለሉ እስከ መስኮቶቹ ድረስ በእንጨት የተለበዱ ነበሩ፤ የመስኮቶቹ መዝጊያዎችም በዚሁ የተሠሩ ነበሩ። 17 እንዲሁም በውጪ በኩል ወደ ቤተ መቅደሱ የውስጥ ክፍል የሚያስገባው ከበር በላይ ያለው ስፍራም ተለብዶ ነበር፤ በውስጠኛውና በመካከለኛው ክፍል ያሉት ዙሪያ ግድግዳዎች ቅርጽ ባለው መለበጃ የተለበዱ ነበሩ። 18 በመለበጃውም ላይ ያለው ቅርጽ የዘንባባ ዛፎችና የኪሩቤል ስዕል ነበር፤ በክፍሉም ዙሪያ የዘንባባና የኪሩቤል ሥዕሎች ተሰባጥረው ተስለውበታል፤ እያንዳንዱም ኪሩብ ሁለት ፊቶች ነበሩት፤ 19 በአንድ በኩል የሰው ፊት ቅርጽ ያለው ወደ ዘንባባው ሲመለከት፥ በሌላም አቅጣጫ የደቦል አንበሳ ቅርጽ ያለው ወደ ዘንባባው ዛፍ ይመለከት ነበር። እነርሱም በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ተቀርጸው ነበር። 20 ከወለሉ አንሥቶ ከበሮቹ በላይ እስካለው ስፍራ ድረስ በግድግዳዎቹ ላይ የኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ቅርጽ ተቀርጸው ነበር። 21 የመቅደሱም የበር መቃኖች ቅርጽ ሁሉ እኩልነት ያለው አራት ማእዘን ነበር። ከእንጨት የተሠራው መሠዊያ 22 በቅድስተ ቅዱሳኑ መግቢያ ፊት ለፊት፥ ከእንጨት የተሠራ መሠዊያ የሚመስል ነገር ይታይ ነበር፤ እርሱም እኩልነት ያለው አራት ማእዘን ሲሆን፥ እያንዳንዱ ማእዘን ሁለት ክንድ ነበር፤ ከፍታውም ሦስት ክንድ ነበር፤ የማእዘን መደገፊያ ምሰሶዎቹ፥ መሠረቱና ጐኖቹ ሁሉ ከእንጨት የተሠሩ ነበሩ፤ ያም ሰው “ይህ በእግዚአብሔር ፊት የሚገኝ ጠረጴዛ ነው” አለኝ። በሮቹ 23 የተቀደሰው ቦታና ቅድስተ ቅዱሳኑ ድርብ መዝጊያዎች አሉአቸው። 24 እያንዳንዱ መዝጊያ ሁለት ሳንቃዎች ነበሩት፤ ይህም ማለት ለያንዳንዱ መዝጊያ በመግፋት ወይም በመሳብ በሁለት በኩል የሚከፈቱ ሁለት ሳንቃዎች ማለት ነው። 25 በግድግዳዎቹ ላይ እንደተቀረጸው በተቀደሰው ስፍራ በር ላይም ኪሩቤልና የዘንባባ ዛፎች ቅርጽ ተቀርጸው ነበር። በመግቢያው ክፍል ፊት ለፊት በስተውጪ ከእንጨት የተሠራ አጎበር ነበር። 26 በመግቢያው ክፍል ግድግዳዎች፥ በሁለቱም በኩል ወደ ውስጥ ገባ ያሉ መስኮቶች የዘንባባ ዛፎች ቅርጽ ነበሩ። |