ሕዝቅኤል 40 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምወደፊት ስለሚሠራው ቤተ መቅደስ የተገለጠ ራእይ 1 በተሰደድን በሃያ አምስተኛው ዓመት፥ ኢየሩሳሌምም በጠላት እጅ በወደቀች በዐሥራ አራተኛው ዓመት፥ በመጀመሪያው ወር፥ ከወሩም በዐሥረኛው ቀን፥ በዚያው ዕለት የእግዚአብሔር ኀይል ወደ እኔ መጥቶ ነበር፤ እርሱም ብድግ አድርጎ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰደኝ፤ 2 በእግዚአብሔርም ራእይ ወስዶ በእስራኤል ምድር በአንድ ከፍተኛ ተራራ ላይ አኖረኝ፤ እዚያም አንድ ብዙ ቤቶች የተሠሩበትን ከተማ የሚመስል ከተራራው በስተደቡብ በኩል አየሁ። 3 ወደዚያ ሲወስደኝም እንደ ነሐስ የሚያበራ መልክ ያለውን አንድ ሰው አየሁ፤ እርሱም ከበፍታ የተሠራ ገመድና መለኪያ ዘንግ ይዞ በቅጽሩ በር አጠገብ ቆሞ ነበር። 4 ሰውየውም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! እዚህ ድረስ እንድትመጣ የተደረገበት ምክንያት እኔ የማሳይህን ሁሉ እንድትረዳ ስለ ሆነ ልብ ብለህ ተመልከት፤ በጥንቃቄም ስማ፤ የምታየውንም ሁሉ ለእስራኤል ሕዝብ ንገራቸው።” የምሥራቁ ቅጽር በር 5 በቤተ መቅደሱ ዙሪያ ቅጥር ነበረ፤ በሰውዬው እጅ ያለው መለኪያ ዘንግ በእርሱ ረጃጅም ክንዶች ስድስት ይሆናል፤ የቅጽሩ ስፋት ሲለካ አንድ ዘንግ፥ ከፍታው ሲለካ አንድ ዘንግ ሆነ። የእርሱ ክንድ ግን በሌሎች ሰዎች ክንድ ሲለካ አንድ ክንድ ከጋት ይሆናል። 6 ከዚያም በኋላ በስተምሥራቅ በኩል ወዳለው የቅጽር በር አልፎ ሄደ፤ ደረጃውንም ወጥቶ ከጫፉ የመድረኩን ወለል ሲለካ አንድ ዘንግ ሆነ፤ 7 አንድ ዘንግ ቁመትና አንድ ዘንግ ወርድ ያላቸው የዘብ ማረፊያ ክፍሎች ነበሩት፤ በማረፊያ ክፍሎቹ መካከል ያለው ርቀት አምስት ክንድ ነው፤ የቅጽሩ በር መግቢያ መድረክ ወደ ውስጥ እስከሚያስገባው መተላለፊያ ጫፍ ድረስ አንድ ዘንግ ነው። 8-9 ሰውየውም የመግቢያውን መተላለፊያ ሲመትር ስምንት ክንድ ሆኖ አገኘው፤ የግንቦቹ ስፋት ሁለት ክንድ ሆነ፤ የበሩ መተላለፊያ ወደ ቤተ መቅደሱ የሚያመራ ነበር። 10 እነዚህም የዘብ ማረፊያ ክፍሎች ከመተላለፊያው በስተጐን እያንዳንዳቸው ተመሳሳይ ስፋት ነበራቸው፤ በእነርሱ መካከል ያሉትም ግንቦች ሁሉ ተመሳሳይ ውፍረት ነበራቸው። 11 የበሩን መግቢያ ሲለካ ወርዱ ዐሥር ክንድ ርዝመቱ ደግሞ ዐሥራ ሦስት ክንድ ሆኖ አገኘው። 12 በእያንዳንዱ ማረፊያ ክፍል ፊት ለፊት ከፍታው አንድ ክንድ ውፍረቱም አንድ ክንድ የሆነ ዝቅተኛ ግንብ ነበር፤ ክፍሎቹም የአራት ማእዘን ቅርጽ ያላቸው ሆነው እያንዳንዱ ማእዘን ስድስት ክንድ ርዝመት ነበረው። 13 ከዚያ በኋላ መግቢያውን ከአንዱ ማረፊያ ክፍል በስተጀርባ እስከ ሁለተኛው ማረፊያ ክፍል በስተጀርባ፥ ከግድግዳ እስከ ግድግዳ ድረስ ለክቶ ኻያ አምስት ክንድ ሆኖ ተገኘ። 14 በስተመጨረሻ ያለው ክፍል ወደ አደባባዩ ያመራ ነበር፤ እርሱም ሲለካ ኻያ ክንድ ሆኖ ተገኘ። 15 ከመግቢያው ጀምሮ እስከ መውጫው ድረስ ያለው የመተላለፊያው ርዝመት ኀምሳ ክንድ ነበር። 16 ማረፊያ ክፍሎቹና ዐምዶቻቸው በውስጥ በኩል ዙሪያውን መስኮቶችና ዐይነ ርግቦች ነበሩአቸው፤ በስተመጨረሻ ያሉትም ክፍሎች በውስጥ በኩል ዙሪያውን መስኮቶች ነበሩአቸው፤ በግድግዳ ዐምዶቻቸውም ላይ የዘንባባ ዛፎች ቅርጽ ነበሩባቸው። የውጪው አደባባይ 17 ከዚያ በኋላ ሰውዬው ወደ ውጪው አደባባይ አመጣኝ፤ በአደባባዩ ዙሪያ የድንጋይ ንጣፍና ክፍሎች ነበሩ ከንጣፉም ፊት ለፊት ሠላሳ ክፍሎች ነበሩ። 18 የድንጋዩም ንጣፍ እስከ አደባባዩ ዙሪያ ይዘልቃል፤ የውጪውም አደባባይ ከውስጠኛው አደባባይ ዝቅ ያለ ነበር። 19 ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያደርስ ከፍ ብሎ የተሠራ የቅጽር በር ነበር፤ ያም ሰው በሁለቱ የቅጽር በሮች ከመካከል ያለውን ርቀት ለካ፤ እርሱም መቶ ክንድ ሆነ። የሰሜኑ ቅጽር በር 20 ያ ሰው በሰሜን በኩል ወደ ውጪው አደባባይ ትይዩ ያለውን የቅጽር በር ለካ፤ 21 ግራና ቀኝ ያሉት ሦስቱ የዘብ ማረፊያ ክፍሎችና የግድግዳ ዐምዶች እንዲሁም በስተመጨረሻ ያለው ክፍል በምሥራቁ የቅጽር በር በኩል ከታዩት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ልክ ነበራቸው፤ የቅጽር በሩ ጠቅላላ ርዝመት ኀምሳ ክንድ፥ ወርዱ ኻያ አምስት ክንድ ነበር። 22 በስተ መጨረሻ ያለው ክፍል መስኮቶቹና የተሳሉት የዘንባባ ዛፍ ቅርጾችም ከዚህ በፊት በምሥራቁ የቅጽር በር ከታዩት ጋር ተመሳሳይ መጠን ነበራቸው፤ ወደ እርሱም የሚያመሩ ሰባት ደረጃዎች ነበሩ፤ በውስጥ መተላለፊያ በስተመጨረሻ ያለው ክፍልም በአደባባዩ ትይዩ ይገኝ ነበር። 23 በምሥራቁ በር እንዳለው ዐይነት በሰሜኑ በር ትይዩ ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያስገባ በር ነበር፤ ሰውዬው ከአንዱ በር እስከ ሌላው በር ሲለካ አንድ መቶ ክንድ ሆነ። የደቡቡ ቅጽር በር 24 ከዚያም በኋላ ወደ ደቡብ ወሰደኝ፤ እዚያም በደቡብ በኩል የሚያስወጣ አንድ በር ነበር፤ ሰውየውም የበሩን የግድግዳ ዐምዶችና በስተመጨረሻ ያለውን ክፍል ለካ፤ ስፋታቸውም ከሌሎቹ ጋር እኩል ነበር። 25 ርዝመቱ ኀምሳ ክንድ ወርዱ ኻያ አምስት ክንድ የሆነው በር ከነመተላለፊያው እንደ ሌሎቹ ቦታዎች መስኮቶች አሉት። 26 ወደዚያም የሚያደርሱ ሰባት ደረጃዎች አሉ፤ በውስጥ መተላለፊያ በስተመጨረሻ ያለው ክፍል ቀጥሎ ይገኛል፤ በሁለቱ በኩል ባሉት የግድግዳ ዐምዶች ላይ ደግሞ የዘንባባ ቅርጾች ተስለውባቸው ነበር። 27 ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያደርስ ሌላም የቅጽር በር ደግሞ ነበር፤ ያም ሰው ውጪኛውን አደባባይ አቋርጦ አደባባይ እስከዚህ እስከ ሁለተኛው ቅጽር በር ያለውን ስፋት ለካ፤ እርሱም መቶ ክንድ ነበር። የውስጠኛው አደባባይ፥ የደቡብ ቅጽር በር 28 ያ ሰው በደቡቡ ቅጽር በር በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ ወሰደኝ፤ እርሱም የቅጽር በሩን ሲለካ ስፋቱ በውጪ ካሉት የቅጥር በሮች ጋር እኩል ሆኖ ተገኘ። 29 የዘብ የማረፊያ ክፍሎቹ የግድግዳ ዐምዶቹና በስተመጨረሻ ያለው ክፍል ስፋት እንደ ሌሎቹ ነበር፤ የበሩና የመተላለፊያው ርዝመት ኀምሳ ክንድ ወርዱም ኻያ አምስት ክንድ ነበር፤ በመተላለፊያውም ዙሪያ ሁሉ መስኮቶች ነበሩ። 30 ዙሪያውም ኻያ አምስት ክንድ ርዝመትና አምስት ክንድ ወርድ ያላቸው መተላለፊያዎች ነበሩ። 31 መግቢያው ክፍል ከውጪው አደባባይ ጋር ትይዩ ነበር፤ በግድግዳ ዐምዶቹም ላይ የዘንባባ ዛፍ ቅርጾች ነበሩ። መወጣጫውም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት። የውስጠኛው አደባባይ፥ የምሥራቁ ቅጽር በር 32 ያም ሰው በምሥራቁ ቅጽር በር በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ ወሰደኝ፤ እርሱም የቅጽሩን በር ሲለካው መጠኑ ልክ እንደ ሌሎቹ ሆኖ አገኘው። 33 የዘብ ማረፊያ ክፍሎቹ፥ የግድግዳ ዐምዶቹና የመግቢያው ክፍል ስፋት እንደ ሌሎቹ ነበር፤ የበሩና የመተላለፊያው ርዝመት ኀምሳ ክንድ ወርዱም ኻያ አምስት ክንድ ነበር፤ በመተላለፊያውም ዙሪያ ሁሉ መስኮቶች ነበሩ። 34 መግቢያው ክፍል ከውጪው አደባባይ ጋር ትይዩ ነበር፤ በግድግዳ ዐምዶቹም ላይ በሁለቱም በኩል የዘንባባ ዛፍ ቅርጾች ነበሩ፥ መወጣጫውም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት። የውስጠኛው አደባባይ፥ የሰሜኑ ቅጽር በር 35 ያ ሰው ወደ ሰሜኑ ቅጽር በር ወሰደኝ፤ በለካውም ጊዜ ስፋቱ በሌሎቹ ልክ ሆኖ ተገኘ። 36 የዘብ ማረፊያ ክፍሎቹ፥ የግድግዳ የዐምዶቹና የመግቢያው ክፍል ስፋት እንደ ሌሎቹ ነበር፤ የበሩ የማረፊያ ክፍል ርዝመት ኀምሳ ክንድ፥ ወርዱም ኻያ አምስት ክንድ ነበር፥ በመተላለፊያውም ዙሪያ ሁሉ መስኮቶች ነበሩ። 37 የመግቢያው ክፍል ከውጪው አደባባይ ጋር ትይዩ ነበር፤ በግድግዳ ዐምዶቹም ላይ በሁለቱም በኩል የዘንባባ ዛፍ ቅርጾች ነበሩ፤ መወጣጫውም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት። በሰሜን ቅጽር በር አጠገብ ያሉት ሕንጻዎች 38 በውጪው አደባባይ በስተ ሰሜን በኩል ከውስጠኛው የቅጽር በር ጋር የተያያዘ ሌላም ተጨማሪ ክፍል ነበር፤ እርሱም ከአደባባዩ ፊት ለፊት ወደሚገኘው ወደ መግቢያው ክፍል የሚያስገባ ሌላ በር ነበረው፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርቡ የእንስሶች ሥጋ የሚታጠበውም በዚያ ነበር። 39 በመግቢያው ክፍል በኩል በግራና በቀኝ ትይዩ ሁለት ሁለት ጠረጴዛዎች ነበሩ፤ በእነዚያም ጠረጴዛዎች ላይ ለሚቃጠል መሥዋዕት፥ ለኃጢአት መሥዋዕትና ለበደል መሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶች ይታረድባቸው ነበር። 40 ከመግቢያው ክፍል በስተውጪ በሰሜን ቅጽር መግቢያ በር አጠገብ ሁለቱ በአንድ በኩል፥ ሁለቱ በሌላ በኩል በትይዩ የተቀመጡ አራት ተመሳሳይ ጠረጴዛዎች ነበሩ። 41 ስለዚህም ለመሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሶች የሚታረዱባቸው በአጠቃላይ ስምንት ጠረጴዛዎች ነበሩ፤ የእነርሱም አቀማመጥ አራቱ በውስጥ በኩል፥ አራቱ ደግሞ በውጭ በኩል ነበሩ። 42 እንደዚሁም ለሚቃጠለው መሥዋዕት ከተጠረበ ድንጋይ የተሠሩ አራት ጠረጴዛዎች ነበሩ፤ ርዝመታቸው አንድ ክንድ ተኩል ወርዳቸው አንድ ክንድ ተኩል፥ ከፍታቸው አንድ ክንድ ነበር፤ እነርሱም ለሚቃጠለውና ለሌሎች መሥዋዕት የማረጃ ዕቃዎች ማስቀመጫነት የሚያገለግሉ ነበሩ። 43 ለጥቃቅን ዕቃዎች ማስቀመጫነት የሚያገለግል ስፋቱ አንድ ጋት የሆነ ክፈፍ በውስጥ በኩል በግድግዳዎቹ ላይ ዙሪያውን ተሠርቶ ነበር፤ በጠረጴዛዎቹም ላይ የመሥዋዕቱ ሥጋ ይቀመጥ ነበር። 44 ከዚህም በኋላ ያ ሰው እኔን ወደ ውስጠኛው አደባባይ አስገባኝ፤ እዚያም ሁለት ክፍሎች ነበሩ፤ ከእነርሱም አንዱ በሰሜን የቅጽር በር አጠገብ ወደ ደቡብ የሚያመለክት ሲሆን፥ ሁለተኛው በደቡብ የቅጽር በር አጠገብ ወደ ሰሜን የሚያመለክት ነበር። 45 ያም ሰው እንዲህ አለኝ፦ “ወደ ደቡብ የሚያመለክተው ክፍል በቤተ መቅደሱ ለማገልገል ኀላፊነት ለተሰጣቸው ካህናት ማረፊያ ነው። 46 ወደ ሰሜን የሚያመለክተውም ክፍል በመሠዊያው ለማገልገል ኃላፊነት ለተሰጣቸው ካህናት ማረፊያ ነው፤ እነዚህ ሁሉ ካህናት ከሳዶቅ ዘር የተወለዱ ሌዋውያን ሲሆኑ፥ በፊቱ ቆመው እግዚአብሔርን ለማገልገል የተፈቀደላቸው እነርሱ ብቻ ናቸው።” የውስጠኛው አደባባይና የቤተ መቅደሱ ሕንጻ 47 ያ ሰው የውስጠኛውን አደባባይ ሲለካ ርዝመቱ መቶ ክንድ ወርዱም መቶ ክንድ ሆነ፤ በቤተ መቅደሱ በፊት ለፊቱም አንድ መሠዊያ ነበር። 48 ከዚያ በኋላ ወደ ቤተ መቅደሱ መግቢያ ክፍል አመጣኝ፤ የመግቢያው ክፍል የግድግዳውም ዐምዶች ሲለካ የሁለቱም ትይዩ አምስት ክንድ ሆኖ አገኘው፤ የመግቢያውም ወርድ ዐሥራ አራት ክንድ ነበር፤ የመግቢያውም ግድግዳ ውፍረት በሁለቱም በኩል ሦስት ሦስት ክንድ ነበር። 49 የመግቢያው ክፍል ርዝመት ኻያ ክንድ፥ ወርዱ ዐሥራ ሁለት ክንድ ነበር፤ ዐሥር የመወጣጫ ደረጃዎቹም ወደዚያ ያደርሱ ነበር፤ በሁለቱ መወጣጫ ደረጃዎች ጐን ዐምዶች ነበሩ። |