Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 4 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ሕዝቅኤል የኢየሩሳሌምን በጠላት መከበብ በምሳሌ ማስረዳቱ

1 እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “አንተ የሰው ልጅ ሆይ! አንድ ጡብ ወስደህ በፊትህ አኑር፤ በላዩም ላይ የኢየሩሳሌምን ከተማ የሚያመለክት ካርታ ንደፍበት።

2 ልክ እንደ አንድ ከተማ አስመስለህ በጡቡ ላይ አደጋ ለመጣል ተዘጋጅ፤ እስከ ጫፍ ድረስ የዐፈር ቊልልና መወጣጫ ሠርተህ ጡቡን በጠላት ወታደር እንደሚከበብ አስመስለህ ክበባት። በሁሉም አቅጣጫ የእንጨት ምሰሶ ሠርተህ የከተማይቱን የቅጥር በር የምታፈርስ አስመስል።

3 የብረት ምጣድም ወስደህ በአንተና በከተማይቱ መካከል እንደ ቅጽር አቁመው፤ ፊትህንም ወደ ከተማይቱ አቅና፤ የተከበበችም ትምሰል፤ የምትከባትም አንተው ነህ፤ ይህም ለእስራኤል ሕዝብ ምልክት ይሆናል።

4 “እንግዲህ በግራ ጐንህ ተኝተህ የእስራኤላውያንን ኃጢአት ተሸከም፤ በጐንህ በምትተኛባቸው ቀኖች ቊጥር የእነርሱን ኃጢአት ትሸከማለህ።

5 እስራኤላውያን ኃጢአት በሠሩባቸው ዓመቶች ብዛት ቀኖችን መድቤልሃለሁ፤ ይህም አንድ ቀን ለአንድ ዓመት ማለት ነው፤ ስለዚህ ለሦስት መቶ ዘጠና ቀኖች የእስራኤላውያንን ኃጢአት ትሸከማለህ።

6 ያንንም ከፈጸምክ በኋላ ተዛውረህ በቀኝ ጐንህ በመተኛት እንደገና የይሁዳን በደል አርባ ቀን ትሸከማለህ፤ ይህም እነርሱን በምቀጣበት በእያንዳንዱ ዓመት ልክ ይሆናል ማለት ነው።

7 “ወደ ኢየሩሳሌም ከበባ ትኲር ብለህ ተመልከት፤ እጅህንም አንሥተህ የማስጠንቀቂያ ትንቢት በእርስዋ ላይ ተናገር።

8 ከበባው እስኪፈጸም ድረስ ከአንድ ጐንህ ወደ ሌላው እንዳትዘዋወር በገመድ አስርሃለሁ።

9 “አሁንም ስንዴና ገብስ፥ ባቄላና ምስር፥ ማሽላና ጠመዥ ውሰድ፤ ሁሉንም በአንድነት ደባልቀህ እንጀራ ጋግር፤ ይህም በግራ ጐንህ በምትተኛባቸው በ 390 ቀኖች ውስጥ የምትመገበው ነው።

10 በየቀኑ 230 ግራም የሚመዝን ምግብ ትወስዳለህ፤ እርሱም እስከሚቀጥለው ቀን እንዲበቃህ በማድረግ በተወሰነ ሰዓት ትመገበዋለህ።

11 የምትጠጣውም ውሃ የተመጠነ መሆን ስለሚገባው በቀን ሁለት ኩባያ ብቻ ትጠጣለህ።

12 የደረቀውን የሰው ዐይነ ምድር በማገዶነት ተጠቅመህ ሰው ሁሉ አንተን በሚያይበት ስፍራ እንደ ገብስ እንጀራ ጋግረህ ትመገበዋለህ።”

13 እግዚአብሔርም፦ “ይህም እስራኤላውያንን በባዕድ አገሮች ሁሉ በምበትናቸው ጊዜ በሕግ የተከለከሉትን የረከሱ ምግቦች የሚመገቡ መሆናቸውን ያመለክታል” አለ።

14 እኔም እንዲህ ስል መለስኩ፦ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! ይህስ ከቶ አይሁን! እኔ ከቶ ረክሼ አላውቅም፤ ከሕፃንነቴ ጀምሮ የበከተ ወይም አውሬ የገደለው ከብትን ሥጋ የበላሁበት ጊዜ የለም፤ ጸያፍ ምግብም አልበላሁም።”

15 እግዚአብሔርም “መልካም ነው፤ እንግዲያውስ በሰው ዐይነ ምድር ፈንታ የእንስሶችን ኩበት ወስደህ እርሱን በማቀጣጠል እንጀራ ጋግር” አለኝ።

16 ቀጥሎም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ለኢየሩሳሌም የሚቀርበው ምግብ ሁሉ እንዲቋረጥ አደርጋለሁ፤ በዚያ የሚኖሩ ሕዝብ በፍርሃትና በስጋት ተሞልተው የሚበሉትን እህልና የሚጠጡትን ውሃ እየመጠኑ እንዲመገቡና እንዲጠጡ አደርጋለሁ።

17 የእንጀራና የውሃ እጥረት ያጋጥማቸዋል፤ ስለዚህም ተስፋ በመቊረጥ እርስ በርሳቸው ይተያያሉ፤ ከበደላቸውም ብዛት የተነሣ ሰውነታቸው ይመነምናል።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告