ሕዝቅኤል 39 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየጎግ መሸነፍ 1 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! የሜሼክና የቱባል ሕዝብ ገዢ በሆነው በጎግ ላይ ትንቢት ተናገርበት፤ በእርሱም ላይ የተነሣሁ መሆኔን ንገረው። 2 አቅጣጫውን አስለውጬ ሩቅ ከሆነው ከሰሜን አገር ገፋፍቼ በእስራኤል ተራራዎችም ላይ እንዲዘምት አደርገዋለሁ፤ 3 ከዚያም በኋላ እርሱን መትቼ ቀስቱን ከግራ እጁ፥ ፍላጻውንም ከቀኝ እጁ አስጥለዋለሁ። 4 ጎግና ሠራዊቱ፥ እንዲሁም ከእርሱ ጋር የተሰለፉ የጦር ጓደኞቹ ሁሉ ሞተው በእስራኤል ተራራዎች ላይ ይወድቃሉ፤ ሬሳቸውንም ለሰማይ ወፎችና ለምድር አራዊት ምግብ እንዲሆን አደርገዋለሁ። 5 በአውላላ ሜዳ ላይ ወድቀው ይቀራሉ፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 6 በማጎግ ምድርና በባሕር ዳርቻዎች ሰዎች ያለ ስጋት በሚኖሩባቸው ስፍራዎች ሁሉ እሳት አቀጣጥላለሁ፤ በዚያን ጊዜ ሁሉም እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ። 7 ቅዱስ ስሜ በሕዝቤ በእስራኤል ዘንድ እንዲታወቅ አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህም ወዲህ ስሜ እንዲሰደብ አልፈቅድም፤ ከዚያም በኋላ ሕዝቦች ሁሉ እኔ እግዚአብሔር የእስራኤል ቅዱስ መሆኔን ያውቃሉ።” 8 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እየመጣ ነው፤ በእርግጥ ይፈጸማል፤ ይመጣል ብዬ የተናገርኩት ቀን ይህ ነው። 9 በእስራኤል ከተሞች የሚኖሩ ሕዝብ ወጥተው የተጣለውን የጦር መሣሪያ ሁሉ ለእሳት ማገዶ እንዲሆን ይሰበስባሉ፤ ጋሻውን፥ ቀስቱን፥ ፍላጻውን፥ ጦሩንና ዱላውን ሁሉ ሰብስበው ያነዱታል፤ ለሰባት ዓመት የሚበቃም ማገዶ ይኖራቸዋል። 10 ስለዚህም ከየስፍራው የማገዶ እንጨት መሰብሰብም ሆነ፥ ከየጫካውም ዛፍ መቊረጥ አያስፈልጋቸውም፤ ምክንያቱም ወድቆ የቀረውን የጦር መሣሪያ ሁሉ ሰብስበው ማንደድ ይችላሉ፤ ቀድሞ የበዘበዙአቸውንና የዘረፉአቸውን አሁን በተራቸው መበዝበዝና መዝረፍ ይችላሉ፤” ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል። የጎግ መቃብር 11 ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ይህ ሁሉ በሚሆንበት ጊዜ በእስራኤል ምድር በሚገኘው፥ ከሙት ባሕር በስተ ምሥራቅ ባለው በመንገደኞች ሸለቆ ውስጥ፥ ለጎግ የመቃብር ቦታ እሰጠዋለሁ፤ እርሱም ከብዛቱ የተነሣ መተላለፊያ መንገዱን ይዘጋል፤ ጎግና ሠራዊቱ ሁሉ በዚያ ይቀበራሉ፤ ስለዚህም ያ ሸለቆ ‘የጎግ ሠራዊት ሸለቆ’ ተብሎ ይጠራል። 12 ከዚያም በኋላ እስራኤላውያን ያንን ሁሉ ሬሳ ቀብረው ምድሪቱን እንደገና ለማጽዳት ሰባት ወራት ይፈጅባቸዋል። 13 በምድሪቱ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ሬሳውን በመቅበር ይተባበሩአቸዋል፤ የእኔ ክብር በሚገለጥበት ቀን ለእነርሱም ክብር ይሆንላቸዋል፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 14 ከሰባት ወራትም በኋላ በምድር ላይ የተረፉ ሬሳዎች ቢኖሩ በየስፍራው በመዘዋወር እየፈለጉ በመቅበር ምድሪቱን የሚያጸዱ ሰዎች ይመደባሉ። 15 በሀገሪቱም ውስጥ ሲዘዋወሩ የሰው ዐፅም በሚያገኙበት ጊዜ በጐኑ ምልክት አድርገውበት ያልፋሉ፤ መቃብር ቆፋሪዎችም መጥተው በሐሞን ጎግ ሸለቆ ይቀብሩታል። 16 በዚህም ዐይነት ምድሪቱ እንደገና ትጸዳለች፤ በዚያም አቅራቢያ ሐሞና ተብላ የምትጠራ ከተማ ትኖራለች።” 17 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “አንተም የሰው ልጅ ሆይ! ለተለያዩ የአሞራ ዘሮችና ለአራዊት ሁሉ እንዲህ በላቸው፦ ‘በእስራኤል ተራራዎች ላይ በማዘጋጅላችሁ ታላቅ የመሥዋዕት በዓል ሥጋን ለመብላትና ደምን ለመጠጣት ከየአቅጣጫው ተሰብስባችሁ ኑ።’ 18 እንደ ቅልብ የባሳን ጠቦትና ሙክት ፍየልና ኰርማ የሆኑትን የኀያላን ሰዎችን ሥጋ ትበላላችሁ፤ የምድር ልዑላንንም ደም ትጠጣላችሁ። 19 እኔ በማዘጋጅላችሁ የመሥዋዕት በዓል ላይ እስክትጠግቡ ድረስ ጮማ ትበላላችሁ፤ እስክትሰክሩም ድረስ ደም ትጠጣላችሁ። 20 እኔ ከማቀርብላቸው ማእድ የፈረሶችንም ሆነ የፈረሰኞችን፥ የወታደሮችንም ሆነ የሌሎችን ጦረኞች ሥጋ እስከሚጠግቡ ይመገባሉ፤” ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል። የእስራኤል መመለስ 21 ቀጥሎም እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ክብሬን በሕዝቦች መካከል እገልጣለሁ፤ ሕዝቦችም ሁሉ ተግባራዊ ያደረግኹትን ፍርዴንና እነርሱን የቀጣሁበትን ኀይሌን ያያሉ። 22 እስራኤላውያንም ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደ ሆንኩ ያውቃሉ። 23 እስራኤላውያን ተማርከው የሄዱትም እኔን በመበደላቸው ምክንያት መሆኑን ሕዝቦች ሁሉ ያውቃሉ፤ እኔ ችላ ስላልኳቸው ጠላቶቻቸው በጦርነት ድል አድርገው ሁላቸውንም ገድለዋቸዋል። 24 እንደ ርኲሰታቸውና እንደ በደላቸው አደረግሁባቸው፤ ርዳታም አላደረግሁላቸውም።” 25 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “አሁን ግን የያዕቆብ ልጆች ለሆኑት ለእስራኤል ሕዝብ ምሕረት አደርግላቸዋለሁ፤ እንደገናም አበለጽጋቸዋለሁ፤ ቅዱስ ስሜም እንዳይሰደብ እከላከላለሁ። 26 የሚያስፈራቸው ነገር ሳይኖር በገዛ ምድራቸው በሰላም ይኖሩ በነበረ ጊዜ የፈጸሙትን አሳፋሪ ተግባርና ለእኔ አለመታመናቸውን ሁሉ ይረሳሉ። 27 እነርሱን ከሕዝቦች መካከል ስመልሳቸውና ከጠላቶቻቸው አገሮችም ብዙ ሕዝቦች እያዩ ስሰበስባቸው በእነርሱ አማካይነት ቅድስናዬን እገልጣለሁ። 28 ተማርከው ወደ ስደት እንዲሄዱ ያደረግኋቸው እኔ ብሆንም እንኳ አሁን ከእነርሱ አንድም ሰው ወደኋላ ሳይቀር ወደ ገዛ አገራቸው እንዲመለሱ አድርጌአለሁ። ስለዚህ ሕዝቤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው መሆኔን ያውቃሉ። 29 መንፈሴን በእስራኤል ሕዝብ ላይ አፈሳለሁ፤ ዳግመኛም ችላ አልላቸውም፤” ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል። |