ሕዝቅኤል 38 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምጎግ የእግዚአብሔር መሣሪያ ሆኖ ይነሣል 1 እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! በማጎግ ምድር የሚገኙት የሜሼክና የቱባል ሕዝቦች ገዢ የሆነውን ጎግን በመቃወም ትንቢት ተናገርበት፤ 3 እኔ ልዑል እግዚአብሔር እርሱን የምቃወም መሆኔን ንገረው። 4 በመንጋጋው መንጠቆ አስገብቼ በመጐተት እርሱንና ሠራዊቱን ወደ መጡበት ወደ ኋላቸው እመልሳቸዋለሁ፤ ሠራዊቱ ከፈረሶችና የጦር ልብስ ከለበሱ ፈረሰኞቹ ጋር እጅግ የበዛ ነው፤ እያንዳንዱ ወታደር ትልቅና ትንሽ ጋሻ አንግቦ ሰይፍ ታጥቆአል፤ 5 ከፋርስ፥ ከኢትዮጵያና ከሊቢያ የመጡ ሰዎችም ሁሉ ጋሻ አንግበው የራስ ቊር ደፍተው የእርሱ ተባባሪዎች በመሆን ከእርሱ ጋር ተሰልፈዋል። 6 ጎሜር ከሠራዊቱ ሁሉ ጋርና፥ ራቅ ካለው የሰሜን ክፍልም ቤት ቶጋርማና ሠራዊቱ ከእርሱ ጋር ናቸው፤ እንዲሁም ከሌሎች ብዙዎች አገሮች የመጡ ሰዎች ከእርሱ ጐን ተሰልፈዋል። 7 ስለዚህ እንዲዘጋጅ ንገረው፤ ሠራዊቱንም ሁሉ በእርሱ ትእዛዝ ሥር እንዲያዘጋጅ አስታውቀው። 8 መዘጋጀትም ያለበት ከብዙ ጊዜ በኋላ በጦርነት ወድማ የነበረችውን የእስራኤልን ምድር እንዲወር ስለማዘው ነው፤ ለብዙ ጊዜ ባድማ ሆና ነበር፤ ሕዝብዋ ይኖሩባቸው ከነበሩት አገሮች ተመልሰዋል፤ አሁን እስራኤላውያን በሀገራቸው ውስጥ በሚገኙ ተራራዎች ላይ በሰላም ይኖራሉ። 9 እርሱና ሠራዊቱ፥ እንዲሁም ከእርሱ ጋር ያሉ ብዙ ሕዝብ እንደ ማዕበል ሞገድ ሆነው ይመጣሉ፤ እንደ ደመናም ሆነው ምድሪቱን ይሸፍናሉ።” 10 ልዑል እግዚአብሔር ለጎግ የሚለው ይህ ነው፥ “ያ ዘመን ሲደርስ ሐሳብ ወደ አእምሮህ ይመጣል፤ ክፉ ዕቅድም ታቅዳለህ። 11 አንተም እንደዚህ ትላለህ፦ ቅጽር በሌላቸው መንደሮች ላይ እወጣለሁ፤ ቅጽርና ባለ መወርወሪያ መዝጊያ ሳይኖራቸው ጸጥ ብለው በሰላም በሚኖሩ ሰዎች ላይ አደጋ እጥላለሁ። 12 ከሕዝቦች መካከል የተመለሱትም ሰዎች በምድር እምብርት ላይ ይኖራሉ፤ እነርሱም እንስሶችና ቈሳቊስ አሉአቸው። ባድማ የነበረችውም ምድር አሁን የሰው መኖሪያ ሆናለች፤ ሐሳቤ ምርኮን ለመማረክና ለመውሰድ፥ እንዲሁም በእነርሱ ላይ አደጋ ለመጣል ነው። 13 ሳባና ዴዳን፥ እንዲሁም የተርሴስ ነጋዴዎችና ወጣት ጦረኞች እንዲህ ይሉሃል፦ ‘ምርኮን ለመውሰድ መጣህን? ብርንና ወርቅን፥ እንስሶችና ቈሳቊስን፥ ማለት ብዙ ምርኮን እንዲያጓጒዙልህ ብዛት ያላቸውን ሰዎችህን ሰበሰብክን?’ ” 14 ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ! በጎግ ላይ እንዲህ ብለህ ትንቢት ተናገር፤ “ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘በዚያን ቀን ሕዝቤ እስራኤል በሰላም በሚኖሩበት ጊዜ አንተ ራስህን ታነሣሣለህ። 15 በስተ ሰሜን በኩል ርቀህ ከምትኖርበት ስፍራ ሁሉም በፈረስ ላይ የሚቀመጡትን የብዙ ሕዝቦች ታላላቅ ሠራዊትን መርተህ ትመጣለህ። 16 በሕዝቤ በእስራኤል ላይ ምድርን እንደሚሸፍን ደመና ትመጣባቸዋለህ፤ ጎግ ሆይ፥ በኋለኛው ዘመን በምድሬ ላይ እንድትመጣ አደርግሃለሁ፤ ይህንንም የማደርገው በአንተ አማካይነት ቅድስናዬን በፊታቸው በምገልጥበት ጊዜ ሕዝቦች እንዲያውቁኝ ነው።’ ” 17 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ በሕዝቤ በእስራኤል ላይ አንተን እንደማመጣ አገልጋዮቼ የእስራኤል ነቢያት በቀድሞ ዘመን በመደጋገም ትንቢት ተናግረዋል።” እግዚአብሔር በጎግ ላይ የሚያመጣው ቅጣት 18 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ጎግ እስራኤልን በሚወርበት ጊዜ የእኔ ብርቱ ቊጣ ይነሣሣል፤ 19 በዚያን ቀን በእስራኤል ምድር ታላቅ የመሬት መንቀጥቀጥ እንደሚሆን በቅናቴና በሚነድ ቊጣዬ ዐውጃለሁ። 20 እያንዳንዱ የዓሣና የወፍ ዐይነት፥ እያንዳንዱም አውሬና እንስሳ በምድር የሚኖር እያንዳንዱ ሰው እኔን በመፍራቱ ይንቀጠቀጣል፤ ተራራዎች ይወድቃሉ፤ ገደሎች ተፈረካክሰው ይናዳሉ፤ እያንዳንዱም የቅጽር ግንብ ይደረመሳል። 21 በተራሮቼ ሁሉ በጎግ ላይ ሰይፍ እንዲመዘዝ አደርጋለሁ፤ የያንዳንዱም ሰው ሰይፍ ጓደኛውን ይበላል። 22 በቸነፈርና በግድያ እንዲቀጣ እፈርድበታለሁ፤ በእርሱ ላይ፥ በወታደሮቹ ላይና ከእርሱ ጋር በነበሩት ሰዎች ላይ የዝናብ ዶፍ፥ የበረዶ ናዳ፥ እሳትና ዲን አዘንብባቸዋለሁ። 23 በዚህም ዐይነት ታላቅነቴንና ቅድስናዬን አሳያለሁ፤ በብዙ ሕዝቦችም ዘንድ ራሴን አሳውቃለሁ፤ ከዚያ በኋላ እነርሱ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።” |