Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 34 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የእስራኤል እረኞች

1 እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦

2 “የሰው ልጅ ሆይ! በእስራኤል ጠባቂዎች ላይ ትንቢት ተናገርባቸው፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ስለ እነርሱ የምለውን ሁሉ በትንቢት እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘መንጋውን መንከባከብና መጠበቅ ትታችሁ ራሳችሁን የምትጠብቁ እናንተ የእስራኤል እረኞች ወዮላችሁ!

3 ወተቱን ትጠጣላችሁ፤ ከጠጒራቸው የተሠራውንም ሱፍ ትለብሳላችሁ፤ የሰባውንም በግ ዐርዳችሁ ትበላላችሁ፤ ነገር ግን በጎችን በማሰማራት አትጠብቁም፤

4 የደከሙትን አላበረታቸሁም፤ የታመሙትን አላዳናችሁም፤ የተሰበሩትን አልጠገናችሁም፤ የባዘኑትን አልመለሳችሁም፤ የጠፉትን አልፈለጋችሁም፤ ይህን በማድረግ ፈንታ በግፍና በጭካኔ ገዛችኋቸው።

5 በጎቹም እረኛ ስለሌላቸው ተበታተኑ፤ በመበታተናቸውም የምድር አራዊትም ቦጫጭቀው በሉአቸው።

6 ስለዚህም በጎቼ በከፍተኞች ኰረብቶችና ተራራዎች ተንከራተቱ፤ በምድርም ገጽ ተበተኑ፤ የሚጠብቃቸውና ፈልጎ የሚያገኛቸውም የለም።’

7 “አሁንም እናንተ እረኞች! እኔ እግዚአብሔር የምላችሁን ስሙ፤

8 እኔ ልዑል እግዚአብሔር ሕያው እንደ መሆኔ እረኞቼ በጎቼን በመመገብና በመጠበቅ ፈንታ ራሳቸውን ብቻ ስለሚመግቡና የጠፉትን በጎቼን የሚፈልግና የሚጠብቅ እረኛ ስለሌላቸው የአውሬ ሲሳይ ሆነው ተበልተዋል።

9 ስለዚህም እናንተ እረኞች አድምጡኝ።

10 እኔ ልዑል እግዚአብሔር የበጎቹን እረኞች እቃወማለሁ፤ በጎቹን ከእረኞች እጅ ወስጄ እንዳያሰማሩአቸው አደርጋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ እረኞቹ ራሳቸውን አይመግቡም፤ ለእነርሱም ምግብ እንዳይሆኑ በጎቼን ከእነርሱ አፍ አስጥላለሁ።


መልካሙ እረኛ

11 “ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘እኔ ራሴ በጎቼን እፈልጋለሁ፤ በጥንቃቄም እጠብቃቸዋለሁ፤

12 የበግ እረኞች ከተበታተኑት በጎቻቸው መካከል መንጋዎቻቸው እንደሚፈለጉ፥ እኔም በጎቼን እፈልጋለሁ፤ በደመናና በድቅድቅ ጨለማ ቀን ከተበታተኑበት ቦታ ሁሉ አድናቸዋለሁ።

13 ከሕዝቦችና ከሀገሮች ሰብስቤ በማውጣት ወደ ሀገራቸው አመጣቸዋለሁ፤ በመኖሪያ ቦታዎችና ውሃ በሚወርድበት ቦታ ሁሉ በእስራኤል ተራራዎች ላይ እመግባቸዋለሁ።

14 በመልካም መሰማሪያ ቦታ አሰማራቸዋለሁ፤ መሰማሪያቸውም በእስራኤል ተራራዎች ከፍተኛ ቦታ ይሆናል። በእስራኤል ተራራዎች ላይ ተመግበው በመልካም መሰማሪያ ቦታዎች ያርፋሉ።

15 እኔ ራሴ ለበጎቼ እረኛ እሆናለሁ፤ እንዲያርፉም አደርጋቸዋለሁ፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’

16 “የጠፉትን እፈልጋለሁ፤ የባዘኑትን እመልሳለሁ፤ የተሰበሩትን እጠግናለሁ፤ ደካሞችን አበረታለሁ፤ እኔ ትክክለኛ እረኛ ስለ ሆንኩ በግፍ የሰቡትንና ብርቱዎች የሆኑትን አጠፋለሁ።

17 “ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘ስለ እናንተ ስለ መንጋዎቼ በመልካም በጎችና በክፉ በጎች በአውራ በጎችና በፍየሎች መካከል እፈርዳለሁ።

18 ከመልካሙ መሰማሪያ የተመገባችሁት አንሶ ነውን? የቀረውን መሰማሪያችሁን በእግራችሁ የምትረግጡት? የጠራ ውሃ ከጠጣችሁ በኋላ የቀረውን ማደፍረስ አለባችሁን?

19 በዚህም ዐይነት ሌሎች በጎቼ እናንተ የረጋገጣችሁትን ሣር ለመብላትና እናንተ ያደፈረሳችሁትንም ውሃ ለመጠጣት ተገደዋል።’

20 “ስለዚህ እነሆ፥ እኔ ልዑል እግዚአብሔር በሰቡና በደካሞች በጎቼ መካከል እፈርዳለሁ።

21 እናንተ በጎናችሁና በትከሻችሁ እየገፈተራችሁ ደካሞችን እንስሶች በቀንዳችሁ ወግታችሁ ወደ ሩቅ ቦታ ታባርሩአቸዋላችሁ።

22 ነገር ግን እኔ በጎቼን እታደጋለሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ማንም ዘርፎ እንዲወስዳቸው አልፈቅድም፤ በመልካም በግና በክፉ በግ መካከል እፈርዳለሁ፤

23 እንደ አገልጋዬ እንደ ዳዊት ያለ ንጉሥ እረኛ አድርጌ አስነሣላቸዋለሁ፤ እርሱም በእንክብካቤ ይጠብቃቸዋል።

24 እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እሆናለሁ፤ አገልጋዬ እንደ ዳዊት ያለ ንጉሥ ይመራቸዋል፤ ይህን እኔ ተናግሬአለሁ።

25 የሰላም ዋስትና የሚያገኙበትን ቃል ኪዳን ከእነርሱ ጋር እገባለሁ፤ አደገኞች የሆኑትን አራዊት ከምድሪቱ አስወግዳለሁ፤ ስለዚህ በጎቼ በየመስኩ በሰላም ተሰማርተው ሊኖሩና በየጫካውም ሊያድሩ ይችላሉ።

26 “እነርሱንና በተራሮቼ አካባቢ ያሉትን ቦታዎች እባርካለሁ፤ ዝናቡንም በወቅቱ አዘንባለሁ፤ እርሱም የበረከት ዝናብ ይሆናል።

27 ዛፎች ያፈራሉ፤ እርሻዎች በቂ የእህል ምርት ይሰጣሉ፤ እያንዳንዱም በገዛ ራሱ ምድር በሰላም ይኖራል፤ የሕዝቤን ቀንበር ሰብሬ ባሪያ አድርገው ከሚገዙአቸው ጨቋኞች እጅ ነጻ ሳወጣቸው እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።

28 ከዚያም በኋላ አሕዛብ አይመዘብሩአቸውም፤ አራዊትም ገድለው አይቦጫጭቁአቸውም፤ የሚያስፈራቸው ሳይኖር በሰላም ይኖራሉ፤

29 ብዙ እህል የሚመረትበትን የእርሻ ቦታ አመቻችላቸዋለሁ፤ ዳግመኛ ለራብ አይጋለጡም፤ የሕዝቦች መሳለቂያም አይሆኑም።

30 እነርሱ እኔ አምላካቸው እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር እንደ ሆንኩና እስራኤላውያን የእኔ ሕዝብ መሆናቸውን ያውቃሉ፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።

31 “በበጎች የተመሰላችሁትና እኔ የማሰማራችሁ መንጋ እናንተ የእስራኤል ሕዝብ ናችሁ፤ እኔም አምላካችሁ ነኝ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告