ሕዝቅኤል 33 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየማስተማር ኀላፊነት ( ሕዝ. 3፥16-21 ) 1 እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! ለሕዝብህ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ ‘በአንድ አገር ላይ ጦርነትን ባመጣ ሕዝቡም በመካከሉ ጠባቂ ቢመድብ፥ 3 ጠባቂውም ጠላት ሲመጣ ቢያይና ከአደጋ መጠንቀቅ የሚያስችል የመለከት ድምፅ ለሰዎች ሁሉ ቢያሰማ፥ 4 ማንም ሰው ይህን የማስጠንቀቂያ ድምፅ ሰምቶ ባለማጤኑ ምክንያት ጠላት አደጋ ጥሎበት ቢሞት ጥፋቱ የራሱ ነው፤ 5 ማስጠንቀቂያውን ባለማጤኑ ለሞት ያበቃው የራሱ ስሕተት ነው፤ ማስጠንቀቂያውን ቢያጤንማ ኖሮ ከጥፋት ባመለጠ ነበር፤ 6 ነገር ግን ጠባቂው ጠላት ሲመጣ እያየ ከአደጋ ማስጠንቀቂያውን ድምፅ ሳያሰማ ቢቀር፥ ጠላት መጥቶ ከእነዚያ መካከል አንዱን ቢገድል ያ ሰው የሞተው በኀጢአቱ ነው፤ እኔ ግን ስለ እርሱ ለደሙ ኀላፊ አድርጌ የምጠይቀው ጠባቂውን ነው።’ 7 “አሁንም የሰው ልጅ ሆይ! እነሆ፥ እኔ አንተን ለእስራኤል ሕዝብ ጠባቂ አድርጌሃለሁ፤ እኔ የምሰጥህን ማስጠንቀቂያ ሁሉ ለእነርሱ ማስተላለፍ አለብህ፤ 8 ኃጢአተኛውን ሰው ‘ኃጢአተኛ ሆይ! በእርግጥ ትሞታለህ’ በምለው ጊዜ አንተ ከክፉ ሥራው እንዲመለስ ባታስጠነቅቀው፥ ያ ሰው ኃጢአተኛ እንደ ሆነ በኃጢአቱ ይሞታል፤ ስለ እርሱም ሞት አንተን ራስህን በኀላፊነት ተጠያቂ አደርግሃለሁ። 9 ኃጢአተኛውን ሰው ከክፉ ሥራው እንዲመለስ ካስጠነቀቅኸው በኋላ፥ ከክፉ ሥራው ሳይመለስ በኃጢአቱ ጸንቶ ቢሞት ግን፥ አንተ ራስህን ከኀላፊነት ነጻ ታደርጋለህ።” ሰው ሁልጊዜ በንስሓ መኖር እንደሚገባው 10 የሰው ልጅ ሆይ! ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፦ “እናንተ በደላችንና ኃጢአታችን ከብደውናል፤ በእነርሱም ምክንያት እየመነመንን ነው፥ ታዲያ እንዴት መኖር እንችላለን ብላችኋል። 11 እኔ ልዑል እግዚአብሔር ሕያው እንደ መሆኔ ኃጢአተኛ ሰው፥ ኃጢአት መሥራቱን ትቶ በሕይወት እንዲኖር እንጂ በኃጢአቱ እንዲሞት አልፈቅድም፤ ስለዚህ እስራኤል ሆይ! ክፉ ሥራችሁን ተዉ፤ መሞትን ለምን ትፈልጋላችሁ? ብለህ ንገራቸው። 12 “አሁንም የሰው ልጅ ሆይ! ጻድቅ የነበረ ሰው ኃጢአት መሥራትን ቢጀምር፥ ቀድሞ የፈጸመው መልካም ሥራ አያድነውም፤ ክፉ ሰውም ክፉ መሥራቱን ካቆመ የቀድሞ ክፉ ሥራው እንቅፋት አይሆንበትም፤ ጻድቅ ሰውም ኃጢአት መሥራት ቢጀምር፥ የቀድሞ ጽድቁ ከሞት ሊያድነው አይችልም። 13 ጻድቅ ሰው በእርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ብለውም እርሱ ግን ‘የቀድሞ የጽድቅ ሥራዬ ይበቃኛል’ ብሎ ኃጢአት መሥራት ቢጀምር፥ ከቀድሞ መልካም ሥራው አንዱንም እንኳ አላስታውስለትም፤ ስለዚህም በኃጢአቱ ምክንያት ይሞታል። 14 አንድን ክፉ ሰው በእርግጥ እንደሚሞት ባስታውቀውና እርሱ ግን ኃጢአት መሥራቱን ትቶ ሕጋዊና ትክክለኛ የሆነውን ነገር ቢያደርግ፥ 15 ይህም ማለት፥ ስለ ብድር በመያዣ ስም የያዘውን ወይም የሰረቀውን ንብረት ቢመልስ፥ ኃጢአት መሥራትን ትቶ ሕይወትን የሚሰጡ ሕጎችን ቢጠብቅ፥ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም፤ 16 የሠራውን ኃጢአት ሁሉ ይቅር እልለታለሁ፤ እውነተኛና ትክክለኛ የሆነውን ሥራ በመሥራቱ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል። 17 “የአንተ ሕዝብ ግን እኔ የማደርገው ነገር ትክክል አይደለም ይላሉ፤ ይልቅስ ትክክል ያልሆነው የእነርሱ መንገድ ነው። 18 ጻድቅ ሰው የጽድቅ ሥራውን ትቶ ክፉ መሥራትን ቢጀምር፥ ስለ ክፉ ሥራው ይሞታል፤ 19 ክፉም ሰው ኃጢአት መሥራትን ትቶ እውነተኛና ትክክለኛ የሆነውን ነገር ቢያደርግ በእርሱ ይኖራል። 20 እናንተ እስራኤላውያን ግን እኔ እግዚአብሔር የማደርገው ሁሉ ትክክል አይደለም ትላላችሁ፤ ሆኖም እያንዳንዳችሁን እንደየአካሄዳችሁ እፈርድባችኋለሁ።” የኢየሩሳሌምን መውደቅ የሚገልጥ ዜና 21 በተሰደድን በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፥ ዐሥረኛው ወር በገባ በአምስተኛው ቀን ከኢየሩሳሌም አምልጦ የመጣ አንድ ሰው ከተማይቱ በጠላት እጅ መውደቋን ነገረኝ። 22 አምልጦ የመጣው ሰው እኔ ዘንድ ከመድረሱ ከአንድ ቀን በፊት በምሽቱ የእግዚአብሔር ኀይል ወደ እኔ መጣ፤ በማግስቱ ጠዋት ሰውዬው ወደ እኔ ከመምጣቱ በፊት እግዚአብሔር አንደበቴን ከፈተልኝ፤ ስለዚህ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መናገር አልተሳነኝም። የእስራኤል ሕዝብ በደል 23 እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 24 “የሰው ልጅ ሆይ! በእስራኤል ምድር በፈራረሱ ከተሞች የሚኖሩ ሕዝብ እንዲህ ይላሉ፦ ‘አብርሃም ብቸኛ የሆነ አንድ ሰው ነበረ፤ ምድሪቱ በሞላ ለእርሱ ተሰጠች፤ እኛ ግን እነሆ፥ ብዙዎች ነን፤ ምድሪቱም በእርግጥ በርስትነት ተሰጥታናለች።’ 25 “እኔ ልዑል እግዚአብሔር ስለ እነርሱ የምለውን እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ሥጋ ከነደሙ ትበላላችሁ፤ ጣዖት ታመልካላችሁ፤ ግድያ ትፈጽማላችሁ፤ ታዲያ፥ ይህን ሁሉ እያደረጋችሁ እንዴት ምድሪቱ የእኛ ርስት ናት ትላላችሁ? 26 በሰይፋችሁ ትተማመናላችሁ፤ አጸያፊ ነገር ትፈጽማላችሁ፤ እያንዳንዱ ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ዝሙት ይፈጽማል፤ ታዲያ፥ ምድሪቱ እንዴት የእኛ ርስት ናት ትላላችሁ?’ 27 “እንግዲህ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ሕያው እንደ መሆኔ በፈራረሱ ከተሞች የሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ በእርግጥ ይገደላሉ ብዬ ያስጠነቀቅኋቸው መሆኑን ገልጠህ ንገራቸው፤ በገጠር የሚኖሩ የአራዊት ምግብ ይሆናሉ፤ በየተራራውና በየዋሻው ተደብቀው ያሉትም በመቅሠፍት ያልቃሉ፤ 28 ምድሪቱንም ባድማና ወና አደርጋታለሁ፤ ዕብሪተኛ ኀይልዋም ያበቃል፤ የእስራኤል ተራራዎች ማንም በዚያ በኩል የማያልፍባቸው ባዶ ይሆናሉ። 29 እነርሱ በፈጸሙአቸው አጸያፊ ነገሮች ሁሉ ምክንያት ምድሪቱን ባድማና ወና በማደርግበት ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።” የነቢዩ መልእክት ያስገኘው ውጤት 30 እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ሕዝቡ በከተማይቱ ቅጽር አጠገብና በየቤታቸው ደጃፍ የሚወያዩት ስለ አንተ ነው፤ እርስ በርሳቸውም ‘ኑና ከእግዚአብሔር ምን ቃል እንደ መጣ ሲነገር እንስማ’ ይላሉ። 31 ስለዚህም ሌሎች ሕዝቦች እንደሚያደርጉት ሕዝቤ አንተ ምን እንደምትናገር ለማዳመጥ ብቻ ይሰበሰባሉ፤ ነገር ግን የምትነግራቸውን ሁሉ አይፈጽሙም፤ የምትናገረውን ቃል የሚወዱት መስለው ይታያሉ፤ ነገር ግን ከበዝባዥነታቸው አይመለሱም፤ 32 አንተ በእነርሱ ዘንድ ጥሩ ድምፅ እንዳለውና ደኅና አድርጎ የሙዚቃ መሣሪያን እንደሚጫወት እንደ ፍቅር ዘፈን አቀንቃኝ ነህ፤ አንተ የምትለውን ይሰማሉ እንጂ፤ አይፈጽሙትም። 33 ነገር ግን አንተ የተናገርካቸው ቃላት በእርግጥ ይፈጽማሉ፤ እውን ሆነው በሚፈጸሙበትም ጊዜ በመካከላቸው ነቢይ መኖሩን ያውቃሉ።” |