ሕዝቅኤል 32 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየግብጽ ንጉሥ በባሕር አውሬ መመሰሉ 1 በተሰደድን በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት፥ ዐሥራ ሁለተኛው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን፥ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! ለግብጽ ንጉሥ አልቅስለትና በብርቱም በማስጠንቀቅ እኔ የምሰጥህን እንዲህ ብለህ ንገረው፦ ‘አንተ በአሕዛብ መካከል ስትኖር ራስህን እንደ አንበሳ አድርገህ ቈጥረሃል፤ ነገር ግን አንተ በባሕር ውስጥ እንደሚገላበጥ አስፈሪ የባሕር አውሬ ነህ፤ በእግሮችህ እያንቦጫረቅህ ውሃውን ታደፈርሳለህ። 3 ብዙ አሕዛብ በሚሰበሰቡበት ጊዜ መረቤን እዘረጋብሃለሁ፤ በእኔ መረብ መሳቢያም ጐትተው ወደ ዳር እንዲያወጡህ አደርጋለሁ። 4 በትቢያም ላይ እጥልሃለሁ፤ ሥጋህንም እንዲመገቡት የሰማይ ወፎችና የምድር አራዊትን ሁሉ እጠራለሁ፤ 5 ተራራውንና ሸለቆውን በበሰበሰ በድንህ እንዲሞሉ አደርጋለሁ። 6 ምድሪቱን እስከ ተራራው ድረስ በደምህ አጥለቀልቃለሁ፤ የውሃ መውረጃ ቦዮችም በደምህ ይሞላሉ። 7 እኔ አንተን በማጠፋበት ጊዜ ሰማያትን እሸፍናለሁ፤ ኮከቦቻቸውንም አጨልማለሁ፤ ፀሐይን በደመና እሸፍናለሁ፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ 8 በላይህም አንጸባራቂ የሰማይ ብርሃኖችን አጨልማለሁ፤ ምድርህም ጨለማ እንድትሆን አደርጋለሁ፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።’ 9 “በማታውቃቸው ሕዝቦች መካከል የጥፋትህን ዜና በማሰማበት ጊዜ የብዙ ሕዝቦችን ልብ አስጨንቃለሁ። 10 ብዙ ሕዝቦች አንተን አይተው እንዲደነግጡ አደርጋለሁ፤ ሰይፌን በፊታቸው በማነሣበት ጊዜ ንጉሦቻቸው በአንተ ምክንያት በፍርሃት ይንቀጠቀጣሉ፤ አንተ በምትወድቅበት ቀን እያንዳንዳቸው በየጊዜው ለሕይወታቸው በመፍራት ይርበደበዳሉ።” 11 ልዑል እግዚአብሔር ለግብጽ ንጉሥ እንዲህ ይላል፦ “የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ ይመጣብሃል። 12 ከዓለም ሕዝቦች በጣም ጨካኞች በሆኑት በኀያላን ሰይፍ፥ ብዛት ያለው ሕዝብህ ይወድቃል፤ እነርሱም የግብጽን ትዕቢት ያዋርዳሉ፤ ብዛት ያለው ሕዝብዋም ይጠፋል። 13 በማናቸውም ውሃ በበዛበት ስፍራ አጠገብ የሚገኙ እንስሶችን ሁሉ አጠፋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ውሃውን የሚያደፈርስ ሕዝብ ወይም ከብት ከቶ አይገኝም። 14 ውሃዎችህ እንዲጠሩ፥ ወንዞችህም እንደ ዘይት በሰላም እንዲፈስሱ አደርጋለሁ፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 15 እኔ ግብጽን ወና እና ባድማ በማደርግበትና በእርስዋ የሚኖሩትን ሁሉ በማጠፋበት ጊዜ፥ አንተና ሕዝብህ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ፤ 16 ይህ የሚያወርዱት ሙሾ ነው፤ የሀገሪቱ ሴቶች ሙሾ ያሰማሉ፤ ለግብጽና ብዛት ላለው ሕዝብዋ ያወርዱታል፤ ይላል ልዑል እግዚአብሔር።” ወደ ሙታን ዓለም ስለሚወርዱ ሰዎች 17 በተሰደድን በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አምስተኛው ቀን እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 18 “የሰው ልጅ ሆይ! የግብጽን ሕዝብ ከሌሎች ኀያላን ሕዝቦች ጋር ወደ ሙታን ዓለም በሙሾ ሸኛቸው።” 19 እንዲህም በላቸው፦ “ውበታችሁ ከማን ይበልጥ ይመስላችኋል? ወደ ታች ወርዳችሁ በእግዚአብሔር ከማያምኑ ጋር ተጋደሙ። 20 “በግብጽ ምድር ላይ ሰይፍ ስለ ተዘጋጀ ብዛት ያለው የግብጽ ሕዝብ በሰይፍ ከተገደሉት ሰዎች መካከል ይወድቃሉ። 21 ግብጻውያን ወደ ሙታን ዓለም በሚወርዱበት ጊዜ በሙታን ዓለም ውስጥ የነበሩ ታላላቅ አርበኞች አቀባበል ያደርጉላቸዋል፤ ሲቀበሉአቸውም ‘እናንተ ከተባባሪዎች ጋር ኑ ውረዱ! በጦርነት ከተገደሉት በእግዚአብሔር ከማያምኑ ጋር ተጋደሙ!’ ይሉአቸዋል። 22 “አሦር ከሠራዊትዋ ጋር በዚያ ትገኛለች፤ በሰይፍ በተገደሉ ሠራዊትዋ መቃብር ተከባለች 23 መቃብሮቻቸውም በጥልቁ መጨረሻ ነበር፤ በሕያዋን ዓለም ያሸብር የነበረውና በጦርነት ተገድለው የወደቁ የወታደሮቻቸው መቃብር በዙሪያቸው ነበር። 24 “ብዛት ያለው የዔላም ሕዝብ መቃብርም በዚያ ነበር፤ እነርሱም የሕያዋንን ዓለም ያሸብሩ የነበሩ፥ በጦርነት የተገደሉና በእግዚአብሔር ሳያምኑ የወደቁ ናቸው። ኀፍረታቸውንም ተከናንበው ወደ ጥልቁ ከሚወርዱት ጋር አብረው ይወርዳሉ። 25 ለዔላም ወታደሮችና ብዛት ላለው ሕዝብዋ በሰይፍ በተገደሉት መካከል ማረፊያ ተዘጋጅቶላቸዋል፤ መቃብሮቻቸውም በዙሪያው ነበሩ፤ ሁሉም በእግዚአብሔር ሳያምኑ በጦርነት የተገደሉ ናቸው፤ እነርሱም የሕያዋንን ዓለም ያሸብሩ የነበሩ በጦርነት የተገደሉ ናቸው፤ ኀፍረታቸውንም ተከናንበው ወደ ጥልቁ ከሚወርዱት ጋር አብረው ይወርዳሉ። 26 “የሜሼክና የቱባል ወታደሮች ሕዝቦቻቸው መቃብሮች በዚያ ነበሩ፤ እነርሱ የተገደሉት በጦርነት ነው፤ ሁሉም በእግዚአብሔር ያላመኑ ናቸው፤ ይሁን እንጂ እነርሱም ከዚህ በፊት የሕያዋንን ዓለም የሚያሸብሩ ነበሩ። 27 በሕያዋን ዓለም አሸባሪዎች ስለ ነበሩ እነርሱ ከጦር መሣሪያዎቻቸው ጋር ማለት ሰይፎቻቸው ከወደራስጌ፥ ጋሻቸው በሰውነታቸው ላይ ተደርጎ ይቀበሩ እንደ ነበሩት እንደ ቀድሞ ጦረኞች ሥርዓተ ቀብር አልተደረገላቸውም። 28 “አንተም የግብጽ ንጉሥ ተሰባብረህ በጦርነት ከተገደሉትና በእግዚአብሔር ካላመኑት ጋር ትጋደማለህ። 29 “የኤዶም ነገሥታትና የመሪዎችዋ መቃብር እዚያ ናቸው፤ በአንድ ወቅት እነርሱ ኀያላን ነበሩ፤ አሁን በጦርነት ከተገደሉት በእግዚአብሔር ከማያምኑት ጋር በሙታን ዓለም ተጋድመዋል። 30 “የሰሜን መሳፍንትና ሲዶናውያን እዚያ ናቸው፤ በሥልጣናቸው ተመክተው ሽብር ቢነዙም እንኳ ከተገደሉት ጋር በውርደት ወደ ሙታን ዓለም ወርደዋል፤ በሰይፍ ተገድለው ኀፍረታቸውን በመከናነብ ከወረዱት ጋር በእግዚአብሔር ሳያምኑ ተጋድመዋል። 31 “በሰይፍ የተገደሉት የግብጽ ንጉሥና ሠራዊቱ እነዚያን በሚያዩበት ጊዜ ወደ ሙታን ዓለም ስለ ወረዱት ብዛት ስላላቸው የግብጽ ሕዝብ ንጉሡ ይጽናናል፤ ይላል ልዑል እግዚአብሔር። 32 “እርሱ በሕያዋን ዓለም ሽብርን ይነዛ ስለ ነበረ በሰይፍ በተገደሉት በእግዚአብሔር በማያምኑት መካከል ብዛት ካለው ሕዝቡ ጋር ያርፋል፤” ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል። |