ሕዝቅኤል 31 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምግብጽ በዝግባ ዛፍ መመሰልዋ 1 በተሰደድን በዐሥራ አንደኛው ዓመት፥ ሦስተኛው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! ለግብጽ ንጉሥና ብዛት ላለው ሕዝቡ እንዲህ ብለህ ንገር፥ ‘በታላቅነት ከማን ጋር ትመሳሰላለህ? 3 አንተ የተዋቡ ጥላማ ቅርንጫፎች እንዳሉትና የቁመቱም ርዝመት ደመናዎችን እንደሚነካ የሊባኖስ ዛፍ ነህ። 4 እዚያም ዛፉን የሚያሳድገው በቂ ውሃ ነበረው፤ በመሬት ውስጥ ያለው ጥልቅ ውሃ ዛፉን ያሳድገዋል፤ ጅረቶችም በሜዳ በተተከሉ ዛፎች ዙሪያ ይፈስሳሉ። 5 ይህም ዛፍ ብዙ ውሃ በማግኘቱ፥ ቁመቱ ከሌሎች ዛፎች ሁሉ የረዘመ ሆነ፤ ቅርንጫፎቹም ወፍራሞችና ረጃጅሞች ሆኑ። 6 የወፍ ዐይነቶች ሁሉ በቅርንጫፎቹ ላይ ጎጆአቸውን ሠሩ፤ የምድር አራዊትም ግልገሎቻቸውን በጥላዎቹ ሥር ወለዱ፤ ታላላቅ ሕዝቦች ሁሉ በጥላው ሥር ያርፉ ነበር። 7 ብዙ ውሃ ወዳለበት ሥሮቹን ስለ ሰደደ፥ ታላቅነቱና የቅርንጫፎቹ መስፋፋት ውበትን ሰጥቶት ነበር። 8 በእግዚአብሔር ገነት ውስጥ ያለው የሊባኖስ ዛፍ ሊወዳደረው አይችልም፤ የጥድ ዛፍም ቅርንጫፉን አያኽልም፤ የግራር ዛፎች ቅርንጫፍ ከእርሱ ቅርንጫፎች ጋር ሲወዳደር እንደ ኢምንት ነው። በእግዚአብሔር ገነት ውስጥ ካሉ ዛፎች መካከል አንዳቸው እንኳ እንደ እርሱ ያለ ውበት የላቸውም። 9 እኔ እርሱን በተንሠራፉ ቅርንጫፎች የተዋበ አደረግሁት፤ እርሱ እኔ እግዚአብሔር በተከልኳት በዔደን ገነት ያለውን ዛፍ ሁሉ የሚያስቀና ነበር።’ 10 “እንግዲህ አድጎ እስከ ደመናት በደረሰ መጠን፥ ትዕቢት በሚሰማው በዚያ ዛፍ ላይ እኔ ልዑል እግዚአብሔር የማደርገው ይህ ነው፤ 11 እኔ እርሱን አውጥቼ እጥለዋለሁ፤ ለሕዝቦች መሪ አሳልፌ እሰጠዋለሁ፤ እርሱም እንደ ክፋቱ መጠን ይደረግበታል። 12 ከምድር ሕዝቦች በጣም ጨካኞች የሆኑት ዛፉን ቈርጠው ይጥላሉ። ቀንበጦቹም በተራሮችና በሸለቆዎች ላይ ይወድቃሉ፤ ቅርንጫፎቹ ተሰባብረው በወራጅ ውሃ ላይ ይጋደማሉ። በጥላው ሥር ተጠልለው የነበሩት የምድር ሕዝቦች ሁሉ ትተውት ይሄዳሉ። 13 ወፎች መጥተው በወደቀው ግንድ ላይ ያርፋሉ፤ ቅርንጫፎቹም ለአራዊት መጠጊያ ይሆናሉ፤ 14 የቱንም ያኽል ውሃ እየጠጣ ቢያድግ በዚህ ዐይነት ከፍተኛ ቁመት እስከ ደመና የሚደርስ ዛፍ ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አይኖርም። ሟቾች በሆኑ ሰዎች ላይ የሚደርሰው የሞት ፍርድ በእነርሱም ላይ ይደርሳል፤ ወደ ሙታን ዓለምም ይወርዳሉ።” 15 ልዑል እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ “ያ ዛፍ ተቈርጦ ወደ ሙታን ዓለም በሚወርድበት ጊዜ ጥልቁን ውሃ ዘግቼ እየተለቀሰለት ይሸፈናል። ወንዞችም እንዲቋረጡ አደርጋለሁ፤ ኀይለኞቹ ወራጅ ውሃዎችም እንዲቆሙ ይደረጋሉ። በዚህም ምክንያት በሊባኖስ ተራራዎች ላይ የጨለማ ግርዶሽ አመጣለሁ፤ ስለዚህም የሜዳ ዛፎች ሁሉ ይጠወልጋሉ። 16 እኔ ያን ዛፍ ወደ ሙታን ዓለም እንዲወርድ በማደርግበት ጊዜ አወዳደቁ የሚያሰማው ድምፅ ሕዝቦችን ሁሉ ያንቀጠቅጣል፤ ወደ ሙታን ዓለም የወረዱ የዔደን ዛፎችና የጥሩ መስኖ ውሃ የሚጠጡ የተመረጡ የሊባኖስ ዛፎች ሁሉ እርሱ ወደ ሙታን ዓለም በመውረዱ ደስ ይላቸዋል፤ 17 በጥላው ሥር የነበሩትና ከሕዝቦች መካከል ተባባሪዎቹ የነበሩት በሰይፍ ወደ ተገደሉት ከእርሱ ጋር ወደ ሙታን ዓለም ይወርዳሉ። 18 “ዛፉ የግብጽ ንጉሥና የሕዝቡ ሁሉ ምሳሌ ነው፤ በዔደን ገነት ከነበሩት ዛፎች መካከል እንኳ በቁመትና በውበት እርሱን የሚያኽል አልነበረም። አሁን ግን በዔደን ገነት እንደ ነበሩት ዛፎች ወደ ሙታን ዓለም ይወርዳል፤ እዚያም በእግዚአብሔር የማያምኑ በጦርነት ከተገደሉት ሁሉ ጋር ይደባለቃል፤” ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል። |