Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 30 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


በግብጽ ላይ ስለሚደርስ ችግር

1 እግዚአብሔር እንደገና እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦

2 “የሰው ልጅ ሆይ! እኔ እግዚአብሔር የምገልጥልህን ሁሉ በማስታወቅ ይህን ትንቢት ተናገር፤ ‘ወዮ! ለዚያች ቀን’ ብለህ አልቅስላት።

3 የደመና ቀን ቀርቦአል፤ ይህም የእግዚአብሔር የፍርድ ቀን ነው! እርሱም ለሕዝቦች የመከራ ቀን ይሆናል።

4 በግብጽ ጦርነት ይሆናል፤ በኢትዮጵያም አስጨናቂ ሁከት ይደርሳል፤ ብዙዎች በግብጽ ምድር ይገደላሉ፤ አገሪቱም ተመዝብራ መሠረቶችዋ ይናጋሉ።

5 “ያም ጦርነት ከኢትዮጵያ፥ ከሊብያ፥ ከልድያ፥ ከሊቢያ፥ ከዐረብ አገር፥ በቃል ኪዳን የእኔ ወገኖች ከሆኑት ሕዝብ መካከል እንኳ ተቀጥረው የመጡትን ሁሉ የሚፈጅ ይሆናል።”

6 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከሚግዶል ጀምሮ እስከ አስዋን ድረስ የግብጽ ደጋፊዎች በጦርነት ያልቃሉ፤ የግብጽም ዕብሪተኛ ኀይል ይዋረዳል። እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።

7 ምድሪቱ ባድማ ከሆኑ አገሮች የበለጠ ባድማ ትሆናለች፤ ከተሞችዋም ሁሉ ፍርስራሽ ከሆኑት ከተሞች የበለጠ ይፈራርሳሉ።

8 ግብጽን የሚያጋይ እሳት በማቀጣጥልበት ጊዜ፥ እንዲሁም የደጋፊዎችዋ ኀይል በተንኰታኰተ ጊዜ፥ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።

9 በዚያን ቀን ‘አንዳች ነገር ይደርስብናል’ ብለው ያልተጠራጠሩትን ኢትዮጵያውያንን ለማስፈራራት መልእክተኞች በእኔ ትእዛዝ ይወጣሉ፤ እነርሱም በግብጽ ላይ በእርግጥ በሚመጣው ጥፋት ምክንያት ይጨነቃሉ።”

10 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የግብጽን ብዙ ሕዝብ ያወድም ዘንድ የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን እልከዋለሁ።

11 እርሱም ምሕረት የሌለውን ጨካኝ ሠራዊቱን አስከትሎ ምድሪቱን ለመደምሰስ ይመጣል። እነርሱም ግብጽን በሰይፍ ይመታሉ። አገሪቱም በሬሳ የተሞላች ትሆናለች።

12 የዓባይን ወንዝ ውሃ አደርቃለሁ፤ ግብጽም በክፉ ሰዎች ሥልጣን ሥር እንድትወድቅ አደርጋለሁ። ስለዚህም ባዕዳን ሕዝብ አገሪቱን በሞላ ያጠፋሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።”

13 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በሜምፊስ ያሉትን ጣዖቶችና የሐሰት አማልክት ሁሉ አወድማለሁ፤ በግብጽ ምድር ላይ ገዢ ሆኖ የሚነሣ አይኖርም፤ በሕዝቡም ላይ ፍርሀትን አወርዳለሁ።

14 በደቡባዊ ግብጽ ጳጥሮስ የተባለውን ከተማ ባድማ አደርጋለሁ፤ በሰሜን በኩል በምትገኘው በጾዓን ከተማ ላይም እሳት አቀጣጥላለሁ፤ የቴብስንም ከተማ በፍርድ እቀጣለሁ።

15 የግብጽ ዋና ምሽግ የሆነችው የፔሉስየም ከተማ የቊጣዬ መዓት እንዲወርድባት አደርጋለሁ፤ የቴብስን ብዙ ሕዝብ ሁሉ እገድላለሁ።

16 በግብጽ ላይ እሳት አነዳለሁ፤ ፔሉስየምም በብርቱ ትጨነቃለች፤ የቴብስ የቅጽር ግንቦች ይፈራርሳሉ፤ በሜምፊስም ከተማ ላይ የማያቋርጥ ሥቃይ ይደርስባታል።

17 በኦንና በቡባስቲስ ከተሞች የሚገኙ ወጣቶች ሁሉ በጦርነት ያልቃሉ። የከተሞቹዋ ኗሪዎችም ተማርከው ይወሰዳሉ።

18 የግብጽን ኀይል በመሰባበር የሚመኩበትን ብርታት በማስወግድበት ጊዜ ጣፍናስ በጨለማ ትጋረዳለች፤ ግብጽ በደመና ትሸፈናለች፤ የከተሞችዋ ኗሪዎችም ተማርከው ይወሰዳሉ።

19 ግብጽን በዚህ ዐይነት በምቀጣበት ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።”


የተሰባበረው የግብጽ ንጉሥ ኀይል

20 በተሰደድን በዐሥራ አንደኛው ዓመት የመጀመሪያው ወር በገባ በሰባተኛው ቀን እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦

21 “የሰው ልጅ ሆይ! እኔ የግብጽን ንጉሥ ክንድ ሰብሬአለሁ፤ በሸምበቆ ጠግኖ በጨርቅ በመጠቅለል መልሶ የሚያድነው ወጌሻ የለም፤ ስለዚህም ከእንግዲህ ወዲህ ብርታት አግኝቶ ሰይፍ ማንሣት አይችልም።

22 ከዚህም የተነሣ እኔ ጌታ እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፤ እነሆ፥ እኔ የግብጽን ንጉሥ በቊጣ ተነሥቼበታለሁ፤ ስለዚህም ሁለት እጆቹን፥ ማለትም ከዚህ በፊት የተሰበረውንና ደኅነኛውን ጭምር ልሰብር ተዘጋጅቻለሁ፤ ሰይፉም ከእጁ እንዲወድቅ አደርጋለሁ።

23 ግብጻውያንን በሕዝቦችና በተለያዩ አገሮች መካከል እበትናቸዋለሁ።

24 በዚህም ዐይነት የባቢሎንን ንጉሥ ኀይል በማጠንከር የእኔን ሰይፍ በእጁ አስይዘዋለሁ። የግብጽን ንጉሥ ኀይል ግን እሰብራለሁ፤ እርሱም ለሞት የሚያደርስ ቊስል እንደ ደረሰበት ሰው በጠላቱ ፊት ይቃትታል።

25 የግብጽን ንጉሥ በማዳከም የባቢሎንን ንጉሥ አበረታለሁ። እኔ ለባቢሎን ንጉሥ የምሰጠውንም ሰይፍ ወደ ግብጽ በሚቃጣበት ጊዜ ሰው ሁሉ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃል።

26 ግብጻውያንን በሕዝቦችና በተለያዩ አገሮች መካከል እበትናቸዋለሁ፤ ከዚያም በኋላ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告