Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 እግዚአብሔርም “የሰው ልጅ ሆይ! የቀረበልህን ብላ፥ ይህን የብራና ጥቅል ብላ፤ ወደ እስራኤልም ሕዝብ ሄደህ ተናገር!” አለኝ።

2 ስለዚህ አፌን ከፈትኩ፤ የብራናውንም ጥቅል እንድበላው ሰጠኝ፤

3 “የሰው ልጅ ሆይ! ይህን የሰጠሁህን የብራና ጥቅል ብላው! ሆድህንም በእርሱ ሙላው!” አለኝ፤ እኔም በበላሁት ጊዜ ጣፋጭነቱ እንደ ማር. ነበር።

4 ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! ወደ እስራኤል ሕዝብ ሄደህ እኔ የምነግርህን ቃል ንገራቸው፤

5 እኔ የምልክህ ወደ እስራኤላውያን እንጂ ቋንቋቸው ወደማይታወቅ ባዕዳን ሕዝብ አይደለም፤

6 ንግግራቸው ግራ የሚያጋባ፥ ቋንቋቸው ወደማይታወቅና የቃላቸውን ትርጒም ልታስተውለው ወደማትችል ታላላቅ ሕዝቦች ልኬህ ቢሆን ኖሮማ በሰሙህ ነበር።

7 ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ልበ ደንዳኖችና እልኸኞች ስለ ሆኑ እኔን ለመስማት ፈቃደኞች አልሆኑም፤ አንተንም አይሰሙህም።

8 እኔ ግን አንተን እንደ እነርሱ እልኸኛና የማትበገር አደርግሃለሁ።

9 አንዳችም የሚገታህ ነገር እስከማይኖር ድረስ መልእክቴን ለመናገር ቈራጥ ትሆናለህ፤ አንተን ይበልጥ ያጠነከርኩህ ስለ ሆነ እነዚህን በዕብሪት ዐመፀኞች የሆኑትን የምትፈራበት ምንም ምክንያት የለም።”

10 ቀጥሎም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! የምናገረውን ሁሉ በጥንቃቄ አድምጠህ አስብበት።

11 በምርኮ ወደሚገኙት የአገርህ ሕዝብ ሄደህ ቢሰሙህም ባይሰሙህም እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምላቸውን ሁሉ ንገራቸው።”

12 ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ላይ ከፍ አደረገኝ፤ ከበስተኋላዬም “በሰማይ ለሚኖር እግዚአብሔር ምስጋናና ክብር ይሁን!” የሚል ታላቅ ድምፅ ሰማሁ።

13 የሕያዋን ፍጥረቶቹ ክንፎቹ እርስ በርሳቸው በአየር ላይ ሲፋጩ ሰማሁ፤ ከመንኰራኲሮቹም የሚሰማው የጋጋታ ድምፅ ከፍተኛ ነበር።

14 መንፈስ አንሥቶ በወሰደኝ ጊዜ ስሜቴ በምሬትና በቊጣ ተሞልቶ ነበር፤ የእግዚአብሔርም ኀይል በእኔ ላይ በርትቶ ነበር።

15 ስለዚህ በኬባር ወንዝ አጠገብ ወዳለው ወደ ቴል አቢብ መጣሁ፤ ይህም ስፍራ የምርኮኞች መኖሪያ ነበር፤ ባየሁትና በሰማሁት ነገር ሁሉ በመደንገጥ ደንዝዤ በመካከላቸው ሰባት ቀን ቈየሁ።


እግዚአብሔር ሕዝቅኤልን እረኛ አድርጎ እንደ ሾመው
( ሕዝ. 33፥1-9 )

16 ሰባቱ ቀኖች ካለፉ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦

17 “የሰው ልጅ ሆይ! እኔ ለእስራኤል ሕዝብ ጠባቂ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ እኔ የምናገረውን ቃል ስማ፤ የምሰጥህንም የማስጠንቀቂያ ቃል ንገራቸው።

18 እኔ አንድን በደለኛ በኃጢአቱ ምክንያት በእርግጥ ትሞታለህ ብለው አንተ ግን ያን ሰው ከኃጢአቱ ተመልሶ ይድን ዘንድ ባታስጠነቅቀው እርሱ በኃጢአቱ ይሞታል፤ ስለ እርሱ ሞት ግን አንተን ተጠያቂ አደርግሃለሁ።

19 ኃጢአተኛውን አስጠንቅቀኸው፥ ከኃጢአቱ ባይመለስ እርሱ በኃጢአተኛነቱ ይሞታል፤ አንተም በኀላፊነት ከመጠየቅ ራስህን ታድናለህ።

20 “በደግነቱ የታወቀ ጻድቅ ሰው ክፉ ሥራ መሥራት ቢጀምርና እኔም በችግር ላይ እንዲወድቅ ባደርገው፥ አንተ ካላስጠነቀቅኸው በቀር በኃጢአቱ ይሞታል፤ ከዚያ በፊት የፈጸመው መልካም ሥራ ሁሉ አይታሰብለትም፤ ስለ እርሱ ሞት አንተን በኀላፊነት እጠይቅሃለሁ።

21 በደግነቱ የታወቀ ጻድቅ ሰው ኃጢአት ከመሥራት እንዲገታ ብታስጠነቅቀውና የአንተን ማስጠንቀቂያ ተቀብሎ ኃጢአት ከመሥራት ቢቈጠብ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፤ አንተም በኀላፊነት ከመጠየቅ ራስህን ታድናለህ።”


የሕዝቅኤል አንደበት መተሳሰር

22 ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ኀይል በእኔ ላይ ነበረ፤ “ተነሥተህ ወደ ሸለቆ ሂድ፤ በዚያም አነጋግርሃለሁ” አለኝ።

23 ስለዚህ ተነሥቼ ወደ ሸለቆው ወረድኩ፤ እዚያም በኬባር ወንዝ አጠገብ ባየሁት ሁኔታ የእግዚአብሔር ክብር ተገለጠልኝ፤ በግንባሬም ወደ መሬት ተደፋሁ፤

24 ነገር ግን የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ እኔ ገብቶ በእግሬ አቆመኝ፤ እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ “ወደ ቤትህ ሂድ፤ በርህንም ዘግተህ ተቀመጥ።

25 የሰው ልጅ ሆይ! በገመድ ስለምትታሰር ወደ አደባባይ መውጣት አትችልም፤

26 ይህን ዐመፀኛ ሕዝብ ማስጠንቀቅ እንዳትችል አንደበትህ እንዲተሳሰር አደርገዋለሁ፤”

27 ዳግመኛ ስናገርህና አንደበትህን ስከፍትልህ እንዲህ ትላቸዋለህ፦ “ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘እነርሱ ዐመፀኞች ስለ ሆኑ ለመስማት የሚፈቅዱ ይስሙ፥ ለመስማት የማይፈቅዱ ይተዉት።’ ”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告