Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 27 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ስለ ጢሮስ የወጣ ሙሾ

1 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦

2 “የሰው ልጅ ሆይ! ስለ ጢሮስ ሙሾ አውጣ፤

3 ወደ ባሕር መግቢያ በሚወስደው መንገድ ላይ ተቀምጣ ከተለያዩ የጠረፍ ከተሞች ለሚመጡ ነጋዴዎች አገናኝ ለሆነችው ለጢሮስ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገራት፦ ‘ጢሮስ ሆይ! በፍጹም ውብ ነኝ ብለሻል።

4 መኖሪያሽ ባሕር ነው፤ ገንቢዎችሽ እንደ ተዋበች መርከብ ሠርተውሻል።

5 ሳንቃሽ የተሠራው ከሔርሞን ተራራ በተገኘ ጥድ ነው፤ ምሰሶዎችሽ የተሠሩት በሊባኖስ ዛፍ ነው።

6 መቅዘፊያዎችሽ የተሠሩት ከባሳን በተገኘ የወርካ ዛፍ ነው፤ ወለልሽም የተሠራው ከቆጵሮስ በተገኘ ልዩ በሆነ የጥድ ሳንቃ ነው፤ ዙሪያውም በዝሆን ጥርስ ተለብጦአል።

7 የመርከብ ሸራሽ እንደ ዓላማ ሆኖ ከሩቅ ይታይ ዘንድ፥ በእጅ ሥራ ባጌጠ የግብጽ በፍታ ተሠርቶአል፤ መጋረጃዎችሽ ከቆጵሮስ ደሴት በተገኘ እጅግ በሚያምር ሰማያዊ ሐምራዊ ጨርቅ ተሠርቶአል፤

8 ቀዛፊዎችሽ ሲዶናና አርዋድ ከተባሉ ከተሞች የመጡ ናቸው፤ ጢሮስ ሆይ! ባለሙያዎችሽ የመርከብ አዛዦችሽ ነበሩ።

9 የተበላሸውን ለመጠገን በጌባል ልምድ ያካበቱ ባለሙያዎች በአንቺ መካከል ነበሩ፤ መርከበኞች በመርከባቸው ወደ ወደብሽ እየመጡ ከአንቺ ጋር ይገበያዩ ነበር።’

10 “ከፋርስ፥ ከልድያና ከሊቢያ የመጡ ወታደሮች በሠራዊትሽ ውስጥ ያገለግላሉ፤ ጋሻቸውንና የራስ ቊራቸውን በጦር ሰፈርሽ ሰቅለዋል፤ እነርሱ ለአንቺ ክብር ያስገኙ ሰዎች ናቸው።

11 ከአርዋድ የመጡ ወታደሮች የቅጽር ግንቦችሽን ይጠብቁ ነበር፤ ከጋማድም የመጡ ሰዎች ምሽጎችሽን ይጠብቁ ነበር፤ ጋሻዎቻቸውን በግንቦችሽ ላይ ሰቀሉ፤ የተዋብሽ እንድትሆኚ ያደረጉሽ እነርሱ ናቸው።

12 “ከብልጽግናሽ ብዛት የተነሣ ከተርሴስ ጋር ንግድ በመለዋወጥ በአንቺ ዕቃዎች ለውጥ ከእርስዋ ብር፥ ብረት፥ ቆርቆሮና እርሳስ ታገኚ ነበር።

13 ከግሪኮች ከቱባልና ከሜሼክ ጋር የንግድ ሥራ ታካሂጂ ነበር፤ ባሪያዎችንና ከነሐስ የተሠሩ ዕቃዎችን ወስደሽ፥ በምትኩ ሸቀጥሽን ትሰጪአቸው ነበር፤

14 ከቤትቶጋርማ የበረሓ ፈረሶችን፥ የጦር ፈረሶችንና በቅሎዎችን ወስደሽ ሸቀጥሽን ለእነርሱ ትሸጪ ነበር።

15 ከሮድ አገር ሰዎች ጋር የንግድ ሥራ ታካሂጂ ነበር፤ በባሕር ዳር የሚገኙ አገሮች ሕዝቦች ሸቀጥሽን ወስደው በምትኩ የዝሆን ጥርስና ዞጲ ያመጡልሽ ነበር።

16 የሶርያ ሕዝብ የንግድ ሸቀጥሽን ሁሉና ሌሎችንም ብዙ ዕቃዎች ይገዙሽ ነበር፤ በወሰዱአቸውም ዕቃዎች ምትክ በሉር፥ ሐምራዊና በጥልፍ ያጌጠ ልብስ፥ ቀጭን ሐር፥ ከዛጎል የተሠሩ ጌጣጌጦችና ቀይ ዕንቊ ይሰጡሽ ነበር፤

17 የይሁዳና የእስራኤል ነጋዴዎች ለሸቀጥሽ ዋጋ የሚኒት አገር ስንዴ፥ ማሽላ፥ ማር፥ የወይራ ዘይትና ቅመማ ቅመም ይከፍሉሽ ነበር።

18 የደማስቆ ሕዝብ ስለ ሸቀጥሽና ስለ ሌሎችም ዕቃዎችሽ ከሔልቦን የተገኘ የወይን ጠጅና ከሳሖር የተገኘ የበግ ጠጒር ይሰጡሽ ነበር።

19 በኡዛል የሚኖሩ ዳናውያንና ግሪኮች አሞናውያን ያንቺን ዕቃዎች ለመግዛት የንግድ ስምምነት አደረጉ፤ እነርሱም በአንቺ ሸቀጦች ልዋጭ ቀልጦ የተሠራ ብረት፥ ቅመማ ቅመምና የጠጅ ሣር አቀረቡ።

20 የደዳን ሕዝብ ስለ ሸቀጥሽ ልዋጭ የኮርቻ ልብስ ያመጣልሽ ነበር።

21 ዐረቦችና የቄዳር ምድር አለቆች ሁሉ ስለ ንግድ ዕቃሽ ጠቦቶች፥ በጎችና ፍየሎች ያመጡልሽ ነበር፤

22 የሳባና የራዕማ ነጋዴዎች ለሸቀጥሽ ልዋጭ የከበሩ ድንጋዮች፥ ወርቅና ምርጥ የሆኑ ቅመማ ቅመሞች ያቀርቡልሽ ነበር።

23 የካራን፥ የካኔህና የዔደን ከተሞች፥ የሳባ ነጋዴዎች፥ የአሹርና የኪልማድ ከተሞች፥ እነዚህ ሁሉ ከአንቺ ጋር ይነግዱ ነበር።

24 የተዋቡ ልብሶችን፥ ሐምራዊ ጨርቆችንና፥ በእጅ ሥራ ያጌጡ ልብሶችን፥ ደማቅ የሆኑ ሥጋጃዎችን፥ በደንብ በተገመዱ ሲባጎዎችና ገመዶችን አጥብቀው በማሰር ይሸጡልሽ ነበር።

25 የተርሴስ መርከቦች ዕቃዎችሽን ለመጫን ያገለግሉሽ ነበር። “አንቺ በባሕር መካከል በከባድ ሸቀጣ ሸቀጥ ተሞልተሻል፤

26 ቀዛፊዎችሽ አውጥተው ወደ ጥልቁ ባሕር ወሰዱሽ፤ ኀይለኛውም የምሥራቅ ነፋስ አንገላትቶ በባሕሩ ውስጥ ሰባበረሽ።

27 የንግድ ሸቀጥ ሀብትሽ ሁሉ፥ መርከብ ነጂዎችሽ ሁሉ፥ በመርከብ ውስጥ የሚያገለግሉ ጠጋኞችሽና ነጋዴዎችሽ ሁሉ፥ በመርከቢቱ ውስጥ የነበሩ ወታደሮች ሁሉ፥ መርከቦችሽ ሲሰባበሩ ሁሉም ወደ ጥልቁ ባሕር ይሰጥማሉ።

28 መርከበኞቹ ወደ ባሕር ሲሰጥሙ ያሰሙት ጩኸት በባሕር ዳር ያሉትን አገሮች አንቀጠቀጡ።

29 “በዚህም ጊዜ የሌሎች መርከቦች ቀዛፊዎች ነጂዎችና የመርከቦቹ አዛዦች ሁሉ ወጥተው በባሕሩ ጠረፍ ቆሙ።

30 ሁሉም በራሳቸው ላይ ትቢያ ነስንሰው በዐመድ ላይ እየተንከባለሉ፥ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ስለ አንቺ ምርር ብለው ያለቅሳሉ።

31 ስለ አንቺም በማዘን ጠጒራቸውን ተላጭተው ማቅ ይለብሳሉ፤ ከልባቸው በማዘን ምርር ብለው ስለ አንቺ ያለቅሳሉ።

32 በሐዘናቸውም ስምሽን እያነሡ ያለቅሳሉ። ስለ አንቺም ሙሾ ያወጣሉ፤ እንዲህም ይላሉ፦ ‘በባሕር መካከል ጠፍታ እንደ ቀረች እንደ ጢሮስ ያለ ማን ነው?

33 የሸቀጥ ዕቃሽ በየሀገሩ ሲሠራጭ፥ የየሀገሩን ሕዝብ ፍላጎት ያሟላ ነበር፤ ከአንቺ በተትረፈረፈ ሀብትና ሸቀጥ የምድር ነገሥታትን አበልጽገሻል።

34 አሁን ግን በጥልቁ ባሕር ውስጥ ተሰባብረሽ ቀርተሻል፤ የሸቀጥ ዕቃሽና ለአንቺ ያገለገሉ ሰዎች ሁሉ ከአንቺ ጋር አብረው ጠፍተዋል፤’

35 “በባሕር ጠረፍ የሚኖሩ ሁሉ አንቺን ከገጠመሽ መጥፎ ዕድል የተነሣ ደንግጠዋል፤ ንጉሦቻቸውም እንኳ ሳይቀሩ ተሸብረዋል፤ በያንዳንዳቸውም ፊት ላይ ፍርሀት ይነበባል።

36 እነሆ የሕዝቦች ነጋዴዎች ያላግጡብሻል። መጨረሻሽ አስደንጋጭ ሆኖአል፤ ለዘለዓለምም አትገኚም።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告