Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 26 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


በጢሮስ ላይ የተነገረ ትንቢት

1 በተሰደድን በዐሥራ አንደኛው ዓመት በወሩም መባቻ ዕለት እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፥

2 “የሰው ልጅ ሆይ! በጢሮስ ከተማ ያሉ ሕዝቦች የሚደሰቱበት ነገር ይህ ነው፦ ‘ኢየሩሳሌም ፈራርሳለች! የንግድ ኀይልዋም ወድቋል፤ ከእንግዲህ ወዲያ ከእኛ ጋር መወዳደር ከቶ ስለማትችል እኛ እንበለጽጋለን’ ይላሉ።

3 “ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘ጢሮስ ሆይ! እኔ በአንቺ ላይ ተነሥቼ ባሕር ሞገድን እንደሚያስነሣ በአንቺ ላይ ብዙ ሕዝቦቼን አስነሣለሁ።

4 የከተማሽን የቅጽር ግንቦች ያፈራርሳሉ፤ የዘብ መጠበቂያ ግንብሽን ይሰባብራሉ፤ ዐፈሩን ሁሉ ጠራርጌ በማጥፋት አለቱ ብቻ አግጥጦ እንዲቀር አደርጋለሁ፤

5 እዚያው በባሕር መካከል አጥማጆች መረባቸውን ለማድረቅ የሚያሰጡበት ስፍራ አደርጋታለሁ፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ፤ ሕዝቦች ጢሮስን ይመዘብራሉ።

6 በዋናይቱ ምድር ላይ ባሉት መንደሮች የሚኖሩትንም ሕዝብ በጦርነት በሰይፋቸው ይጨፈጭፋሉ፤ በዚያን ጊዜ ጢሮስ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ታውቃለች።’ ”

7 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በጢሮስ ላይ አደጋ እንዲጥል የነገሥታት ንጉሥ የሆነውን የባቢሎንን ንጉሥ ናቡከደነፆርን ከሰሜን በኩል አመጣባታለሁ፤ እርሱም ከታላቅ ሠራዊት ጋር በብዙ ፈረሶችና ሠረገሎች በፈረሰኞችም ታጅቦ ይመጣል።

8 በዋናይቱ ምድር ባሉት መንደሮች ነዋሪ የሆኑ ሕዝብ ሁሉ በጦርነት ያልቃሉ፤ እናንተን የሚከላከልበት ምሽግ ይሠራል። ጠላትም እስከ ቅጽሮችሽ ጫፍ ዐፈር ይደለድላል፤ በጋሻም ብዛት እየተከላከለ ያጠቃችኋል።

9 በምሽግ ማፍረሻ መሣሪያ ቅጽሮችሽን ይመታል፤ የዘብ መጠበቂያ ግንብሽን በምሳር ያፈራርሳል፤

10 በፈረሶቻቸው ኮቴ የሚነሣው አቧራ እንደ ደመና ሆኖ ይሸፍንሻል፤ እርሱ ወደ ቅጥር በሮችሽ በሚገባበት ጊዜ ከፈረሰኛው፥ ከሠረገላውና ከመንኰራኲሩ የሚሰማው ድምፅ ተጥሳ እንደሚገባባት ከተማ ቅጥሮችሽን ያናጋል።

11 ሠራዊቱ በፈረሶቹ ሰኰናዎች መንገዶችሽን ይረጋግጣል፤ ሕዝብሽን በሰይፍ ይገድላል፤ ጠንካራ ዐምዶችሽም ወደ መሬት ይወድቃሉ።

12 ሀብትሽ ይማረካል፤ የንግድ ዕቃሽ ይዘረፋል፤ ቅጥርሽ ይፈርሳል፤ የተዋቡ ቤቶችሽ ይፈራርሳሉ፤ ድንጋዮችሽ፥ ሳንቃዎችሽና ፍርስራሹ ወደ ባሕር ይጣላሉ።

13 ዘፈንሽንና በበገና የምታሰሚውን የሙዚቃ ድምፅ ሁሉ ጸጥ አደርጋለሁ።

14 ዓሣ አጥማጆች መረባቸውን የሚያሰጡበት አለት ብቻ አግጥጦ ይቀራል፤ ከተማይቱ ዳግመኛ አትታደስም፤ ይህም የሚሆነው እኔ ልዑል እግዚአብሔር ስለ ተናገርኩ ነው።”

15 ልዑል እግዚአብሔር ለጢሮስ ከተማ እንዲህ ይላታል፦ “ቊስለኞች ሲቃትቱና በመካከልሽ ግድያ ሲካሄድ ባወዳደቅሽ ድምፅ የጠረፉ አካባቢ አይናወጥምን?

16 በባሕር አጠገብ ያሉ አገሮች ነገሥታት ሁሉ ከዙፋናቸው ይወርዳሉ፤ መጐናጸፊያቸውንና በእጅ ሥራ ጥልፍ ያጌጠ ልብሳቸውን አውልቀው በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ መሬት ላይ ይቀመጣሉ፤ በአንቺ ላይ የደረሰውን አሠቃቂ ሁኔታ እያሰቡ በብርቱ ይሸበራሉ፤ በአንቺም ሁኔታ ይደነግጣሉ።

17 እንዲህም እያሉ ስለ አንቺ ሙሾ ያወጣሉ፤ ‘በባሕር ጠረፍ ያሉ አገሮችን ያሸበራችሁ፥ በባሕር ላይ ኀያል የነበርሽ ዝነኛይቱ ከተማ ሆይ! እንዴት ከባሕር ጠፋሽ?

18 እነሆ አሁን በወደቀችበት ቀን ደሴቶች ተንቀጠቀጡ፤ በላያቸው የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ ከዚህ ታላቅ ጥፋት የተነሣ ደነገጡ።’ ”

19 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ማንም ሊኖርባቸው እንደማይችል እንደ ፈራረሱ ከተሞች ባድማ አደርግሻለሁ፤ ጥልቅ ከሆነ ውቅያኖስ በሚገኝ ውሃ እሸፍንሻለሁ፤

20 ወደ ሙታን ዓለም ወርደሽ በጥንት ዘመን ይኖሩ ከነበሩ ሕዝቦች ጋር እንድትደባለቂ አደርጋለሁ፤ ከሙታን ጋር ተወዳጅተሽ እንድትኖሪ በዚያ ከምድር በታች ባለ ዓለም ውስጥ ዘለዓለም ፈራርሰው ከቀሩ ነገሮች ጋር እተውሻለሁ፤ ከዚህም የተነሣ ዳግመኛ ሰው አይኖርብሽም፤ በሕያዋንም ምድር ለመኖር ቦታ የለሽም፤

21 መጨረሻሽ አስፈሪ እንዲሆን አደርጋለሁ፤ ከዚያም በኋላ ፍጻሜሽ ይሆናል፤ ሰዎች ቢፈልጉሽ እንኳ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ከቶ አያገኙሽም፤” እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告