ሕዝቅኤል 25 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበዐሞን ላይ የተነገረ ትንቢት 1 እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! ፊትህን ወደ ዐሞን ምድር አዙረህ በዐሞናውያን ላይ ትንቢት ተናገር። 3 ለአሞናውያን፥ ጌታ እግዚአብሔር የሚለውን ስሙ በላቸው፦ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ቤተ መቅደሴ እንዲረክስ በተደረገ ጊዜ፥ የእስራኤል ምድር ባድማ በሆነ ጊዜ፥ የይሁዳ ሕዝብ ተማርኮ በተወሰደ ጊዜ እሰይ ብላችኋል። 4 በዚህ ሁሉ ደስ ስላላችሁ ከምሥራቅ በሚመጣ ነገድ እንድትወረሩ አደርጋለሁ፤ በአገራችሁ የጦር ሰፈር ሠርተው በዚያው ይኖራሉ፤ ለእናንተ ሊሆን የሚገባውን ፍሬ ይበላሉ፤ ወተቱንም ይጠጣሉ። 5 የራባን ከተማ የግመሎች ማሰማርያ፥ መላውንም የዐሞን አገር የበጎች መዋያ አደርገዋለሁ፤ በዚህም ዐይነት እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ። 6 “ልዑል እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ በእጃችሁ በማጨብጨብና በእግራችሁም በመርገጥ የእስራኤልንም ምድር በንቀት ተመልክታችኋት ነበር። 7 ይህንንም በማድረጋችሁ ኀይሌን እገልጥላችኋለሁ፤ በምርኮኛነት ለሕዝቦች አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ ዳግመኛ በሕዝብነት የማትታወቁ እስክትሆኑ ድረስ ጨርሼ አጠፋችኋለሁ፤ ከዚያ በኋላ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።” በሞአብ ላይ የተነገረ ትንቢት 8 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ሞአብና ኤዶም ‘ይሁዳ ከሌሎች ሕዝቦች አገሮች የተለየች አይደለችም’ በማለታቸው 9 ቤትየሺሞት፥ ባዓልመዖንና ቂርያታይም የተባሉት ዝነኞቹ ከተሞች ሳይቀሩ የሞአብ ጠረፍ የሚጠበቅባቸው ከተሞችን ሁሉ በጠላት እንዲመቱ አደርጋለሁ። 10 ከእንግዲህ ወዲህ ዐሞን በመንግሥትነት እንዳትታወቅ ከምሥራቅ የሚመጡ ነገዶች ሞአብንና ዐሞንን እንዲወሩአቸው አደርጋለሁ። 11 እኔ ሞአብን እቀጣለሁ፤ እነርሱም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።” በኤዶም ላይ የተነገረ ትንቢት 12 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “የኤዶም ሕዝብ በይሁዳ ላይ ጭካኔ የተሞላበት በቀል ፈጽመዋል፤ ይህንንም በማድረጋቸው በደለኞች ሆነዋል ይላል ጌታ እግዚአብሔር። 13 ስለዚህ አሁን ኤዶምን እንደምቀጣና በዚያም ያሉትን ሰዎችና እንስሶች በሙሉ እንደማጠፋ አሳውቃለሁ፤ ከቴማን ከተማ እስከ ደዳን ከተማ ድረስ ባድማ እንዲሆን አደርጋለሁ፤ ሕዝቡም በጦርነት ያልቃሉ፤ 14 ኤዶምን የምበቀላት በሕዝቤ በእስራኤል አማካይነት ነው፤ እስራኤላውያን በኤዶም ላይ እንደ ቊጣዬ ኀይለኛነት ይበቀላሉ፤ ኤዶማውያንም እኔ እንደ ተበቀልኳቸው ይረዳሉ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ።” በፍልስጥኤም ላይ የተነገረ ትንቢት 15 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ፍልስጥኤማውያን በማያቋርጥ ጠላትነት በቀልን ተበቅለዋል፤ ይህም የጥፋት በቀል ተንኰልን በተመላ ልብ ነበር። 16 ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ‘በፍልስጥኤማውያን ላይ ኀይሌን እጠቀማለሁ፤ ብሪታውያንን እፈጃለሁ፤ በባሕር ጠረፍ የቀሩትንም አጠፋለሁ። 17 በቊጣ ከተመላ ቅጣቴ ጋር ታላቅ በቀል እበቀላቸዋለሁ፤ በእነርሱም ላይ በምወስደው እርምጃ እኔ እግዚአብሔር መሆን ያውቃሉ።’ ” |