ሕዝቅኤል 24 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምዝገት የበላው የብረት ድስት 1 በተሰደድን በዘጠነኛው ዓመት፥ በዐሥረኛው ወር፥ በዐሥረኛው ቀን፥ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! የባቢሎን ንጉሥ ኢየሩሳሌምን መክበብ የሚጀምርበት ስለ ሆነ ይህን የዛሬውን ዕለት በመዝገብ ጻፈው፤ 3 እኔ ልዑል እግዚአብሔር ስለ እነርሱ የመሰልኩትን ይህን ምሳሌ ዐመፀኞች ለሆኑት ሕዝቤ ንገራቸው፤ ‘ድስት በእሳት ላይ ጥደህ ውሃ አድርግበት፤ 4 ጭንና ወርች የመሳሰሉትን ጥሩ የሥጋ ብልቶች ቈራርጠህ፥ ምርጥ የሆኑትንም አጥንቶች ሰባብረህ በውስጡ ጨምር። 5 ከመንጋው መካከል ምርጥ በግ ውሰድና ዕረድ፤ ከድስቱም ሥር ማገዶ ጨምር፤ ሥጋውንና አጥንቱን እስኪበስል ድረስ ቀቅለው።’ ” 6 ልዑል እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ “ለነፍሰ ገዳዮች ከተማ ወዮላት! ከዝገቱ እንዳልጠራና ከቶም እንደማይጠራ ብረት ድስት ሆናለች፤ በውስጥዋ ያለውን ቊራጭ ሥጋ ሳትመርጥ አንድ በአንድ አውጣው። 7 በከተማይቱ ውስጥ ግድያ ተፈጽሞአል፤ ደሙም የፈሰሰው ትቢያ በሚሸፍነው መሬት ላይ አይደለም፤ ነገር ግን ደሙ የፈሰሰው ምንም በማይሸፍነው ገላጣ አለት ላይ ነው። 8 እርስዋ ያፈሰሰችው ደም እንዳይሸፈን በገላጣ አለት ላይ እንዲፈስ ያስደረግኹት ከፍተኛ ቊጣዬን አስነሥቶ በቀል እንድበቀል ነው።” 9 ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ “ለነፍሰ ገዳዮች ከተማ ወዮላት! ማገዶውን እኔ ራሴ አብዝቼ እጨምራለሁ። 10 ብዙ እንጨት አምጣ! እሳቱንም አቀጣጥል፤ ሥጋውን ቀቅል! መረቁን በቅመም አጣፍጠው! አጥንቱን አቃጥለው! 11-12 የዝገቱ ብዛት በእሳት እንኳ ስላልለቀቀ ጥረቶች ሁሉ ከንቱ ሆነዋል። ስለዚህ ከነሐስ የተሠራውን ባዶ ብረት ድስት በፋመው ከሰል ላይ ጣደው፤ ፍም እስኪመስል ድረስ ይጋል፤ በዚህ ዐይነት ርኲሰቱ ይቀልጣል፤ ዝገቱም ይጠፋል። 13 ኢየሩሳሌም ሆይ! ሴሰኛነትሽ አርክሶሻል፤ እኔ እንኳ ላነጻሽ ብፈቅድ አንቺ ከርኲሰትሽ አልነጻሽም። የቊጣዬ ኀይል እስከሚገለጥብሽ ድረስ ዳግመኛ ንጹሕ አትሆኚም። 14 እኔ ልዑል እግዚአብሔር ‘አንድ ነገር የማደርግበት ጊዜ ቀርቦአል፤ አልገታም፤ አልምርም፤ ሐሳቤን አለውጥም፤ እንደ አካሄድሽና እንደ ሥራሽ እፈርድብሻለሁ’ ” ብዬ ተናግሬአለሁ። የነቢዩ ሚስት መሞት 15 እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 16 “የሰው ልጅ ሆይ! የምትወዳትና የዐይንህ መደሰቻ የሆነችው ሚስትህ ተቀሥፋ በድንገት ትሞትብሃለች፤ በዚህም አትዘን፤ እንባህንም በማፍሰስ አታልቅስ፤ 17 በሐዘንም መንሰቅሰቅህን ሰው አይስማህ፤ ለሟችዋ አታልቅስ፤ መጠምጠሚያህንም በራስህ ላይ አድርግ፤ ጫማህንም በእግርህ አጥልቅ፤ አፍህን አትሸፍን፤ የእዝን እንጀራ አትብላ።” 18 ጠዋት በማለዳም ከሰዎች ጋር እነጋገር ነበር፤ በዚያች ምሽት ሚስቴ ሞተች፤ በሚቀጥለውም ቀን ልክ እንደ ተነገረኝ አደረግሁ። 19 ሰዎችም “ይህን ማድረግህ ከእኛ ጋር ምን ግንኙነት አለው” ሲሉ ጠየቁኝ። 20 እኔም እንዲህ ስል መለስኩላቸው፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 21 ‘ጌታ እግዚአብሔር ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው አለኝ፤ የክብራችሁ ትምክሕት፥ የዐይናችሁ ተስፋና የልባችሁ ደስታ የሆነውን ቤተ መቅደሴን እንዲያረክሱ እተዋቸዋለሁ፤ በኢየሩሳሌም የቀሩት ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ በጦርነት ይገደላሉ። 22 በዚያን ጊዜ እኔ ያደረግኹትን ሁሉ ታደርጋላችሁ፤ አፋችሁን አትሸፍኑም፤ የእዝን እንጀራ አትበሉም፤ 23 ጥምጥማችሁን አታወልቁም፤ ጫማችሁን አውልቃችሁ በባዶ እግራችሁ አትሄዱም፤ አታዝኑም ወይም አታለቅሱም፤ ከኃጢአታችሁም የተነሣ ትመነምናላችሁ፤ እርስ በርሳችሁ በመወያየት ትቃትታላችሁ። 24 በዚህም ዐይነት ሕዝቅኤል ለእናንተ ምልክት ይሆናል፤ እርሱ እንዳደረገውም ታደርጋላችሁ፤’ ይህ በሚፈጸምበት ጊዜ እኔ ልዑል እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።” 25 እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “አሁንም የሰው ልጅ ሆይ! ዘወትር ሊያዩትና ሊጐበኙት የሚወዱትን፥ የሚመኩበትንና የሚደሰቱበትን እጅግ ጽኑ የሆነውን ቤተ መቅደስ ከእነርሱ እወስድባቸዋለሁ፤ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም እወስዳለሁ። 26 እኔ ይህን በማደርግበት ቀን ከጥፋት ያመለጠ ሰው መጥቶ ስለዚህ ሁሉ ድርጊት ይነግርሃል። 27 በዚያኑ ቀን ከዚህ በፊት አጥተኸው የነበረውን የመናገር ችሎታ መልሰህ ታገኛለህ፤ ከእርሱም ጋር ትነጋገራለህ ለሕዝቡም ምልክት ትሆናለህ፤ እነርሱም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።” |