ሕዝቅኤል 22 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየኢየሩሳሌም ሕዝብ የፈጸሙት በደል፤ 1 እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! በነፍሰ ገዳዮች የተሞላችውን ከተማ ልትፈርድባት ተዘጋጅተሃልን? እንግዲያውስ የፈጸመቻቸውን አጸያፊ ነገሮች ሁሉ ገልጠህ አሳያት። 3 ለከተማይቱ እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፦ በውስጥሽ ያሉትን ብዙዎችን ስለ ገደልሽና ጣዖቶችን በማምለክ ራስሽን ስላረከስሽ እንድትጠፊ የተወሰነበት ጊዜ ተቃርቦአል። 4 በፈጸምሽው ግድያ በደለኛ ሆነሻል፤ በሠራሻቸውም ጣዖቶች ረክሰሻል፤ ስለዚህ የምትጠፊበት ጊዜ ቀርቦአል! ያፋጠንሽውም አንቺ ነሽ። ሕዝቦች እንዲቀልዱብሽ፥ አገሮችም በንቀት አመለካከት እንዲያፌዙብሽ ያደረግኹትም ስለዚህ ነው። 5 ስምሽ የጠፋ የሁከት ከተማ ሆይ! በቅርብና በሩቅ ያሉ አገሮች በንቀት አመለካከት ያፌዙብሻል። 6 በውስጥሽ ያሉ የእስራኤል መሪዎች ሁሉ እንደየ ሥልጣናቸው የግድያ ወንጀል ይፈጽማሉ፤ 7 በውስጥሽም አባትና እናት ይናቃሉ፤ የውጪ አገር ሰዎች ይታለላሉ፤ ባሎቻቸው የሞቱባቸው ሴቶችና አባትና እናት የሌላቸው ልጆች ይበደላሉ። 8 ለእኔ የተቀደሱ በሆኑ ነገሮች ላይ አክብሮት የላችሁም፤ ሰንበቴንም አረከሳችሁ። 9 ከእናንተ አንዳንዶቹ ሌሎችን ለማስገደል ሐሰት ይናገራሉ፤ አንዳንዶቹ ለጣዖት የተሠዋውን ሁሉ ይመገባሉ፤ አንዳንዶቹ ዘወትር ፍትወታቸውን ለማርካት ይጣደፋሉ። 10 አንዳንዶቹ ከእንጀራ እናታቸው ጋር በመተኛት የአባታቸውን አልጋ ይደፍራሉ፤ አንዳንዶቹ በወር አበባ ጊዜ ውስጥ ያሉትን ሴቶች በማስገደድ ግንኙነት ይፈጽማሉ። 11 አንዳንዶቹ ከጐረቤቶቻቸው ሚስቶች ጋር ያመነዝራሉ፤ ሌሎችም ምራቶቻቸውን ይደፍራሉ፤ እንዲሁም ከአባት የተወለዱትን እኅቶቻቸውን ያረክሳሉ፤ 12 ከሕዝብሽ አንዳንዶቹ ገንዘብ ተቀብለው ሰው ይገድላሉ፤ አንዳንዶቹ ለገዛ ወገኖቻቸው ለእስራኤላውያን ሳይቀር በአራጣ ያበድራሉ፤ እነርሱንም በመበዝበዝ ያለ አግባብ ይበለጽጋሉ፤ እኔንም ፈጽሞ ረስተዋል፤” ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል። 13 “ዝርፊያችሁንና ነፍስ መግደላችሁን በመቃወም በእናንተ ላይ እጄን አነሣለሁ። 14 እኔ እናንተን በምቀጣበት ጊዜ ወኔ የሚቀርላችሁ ይመስላችኋልን? ወይስ ለመከላከል ኀይል የሚኖራችሁ ይመስላችኋልን? እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ፤ የተናገርኩትንም ቃል እፈጽማለሁ። 15 ሕዝብሽን ወደየአገሩና ወደየሕዝቡ እበትናለሁ፤ ክፉ ሥራሽም እንዲያከትም አደርጋለሁ፤ 16 ሌሎች አሕዛብ ያዋርዱሻል፤ ስለዚህም አንቺ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቂያለሽ።” 17 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 18 “የሰው ልጅ ሆይ! እስራኤላውያን ለእኔ ምንም አይጠቅሙኝም፤ እነርሱ ለእኔ ብር በእሳት ከነጠረ በኋላ ዝቃጩ እንደሚቀር የመዳብ፥ የቆርቆሮ፥ የብረትና የእርሳስ ዝቃጭ ናቸው። 19 ስለዚህ እነርሱ እንደ ማዕድን ዝቃጭ ስለ ሆኑ ሁሉንም በአንድነት ሰብስቤ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣቸዋለሁ፤ 20 ብር፥ መዳብ፥ ብረት፥ እርሳስና ቆርቆሮ ተሰብስበው ወደ ማቅለጫ እንደሚጨመሩና እንዲቀልጡ እሳት ከስር እንደሚነድባቸው እኔም እናንተን በኀይለኛ ቊጣዬ ሰብስቤ እንድትቀልጡ አደርጋለሁ። 21 አዎ በኢየሩሳሌም እሰበስባቸዋለሁ፤ እሳትንም አቀጣጥዬ በቊጣዬ አቀልጣቸዋለሁ። 22 ብር በምድጃ ውስጥ እንደሚቀልጥ፥ እነርሱም በእርስዋ ውስጥ ይቀልጣሉ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር የቊጣዬን ኀይል እንዳወረድኩባቸው ያውቃሉ።” የእስራኤል መሪዎች በደል 23 እግዚአብሔር እንደገና እንዲህ አለኝ፦ 24 “የሰው ልጅ ሆይ! ምድራቸው ስለ ረከሰች በቊጣዬ ዝናብ እንዳይዘንብ በማድረግ ልቀጣት የተዘጋጀሁ መሆኑን ለእስራኤላውያን ንገራቸው፤ 25 መሪዎቻቸው፥ በገደሉአቸው እንስሶች ዙሪያ እንደሚያገሡ አንበሶች ናቸው፤ ሕዝቡንም በጭካኔ ይገድላሉ፤ ገንዘብም ሆነ ሌላ ንብረት ያገኙትን ሁሉ ይወስዳሉ፤ በግድያቸውም ብዙዎችን ሴቶች ያለ ባል አስቀርተዋል። 26 ካህናቱ ሕጌን ይጥሳሉ፤ ቅዱስ ለሆነ ነገርም አክብሮት የላቸውም፤ ቅዱሱን ከርኩሱ አይለዩም፤ ንጹሕ በሆነና ባልሆነ ነገር መካከል ያለውን አያስተምሩም፤ ሰንበትንም ያቃልላሉ፤ ከዚህ የተነሣ የእስራኤል ሕዝብ እኔን አያከብሩኝም። 27 ባለ ሥልጣኖቹ፥ የገደሉትን እንስሳ እንደሚቦጫጭቁ ተኲላዎች ናቸው፤ ያለ አግባብ ለመበልጸግ ሰውን ይገድላሉ፤ 28 ነቢያቱ ግድግዳን ኖራ እንደሚቀባ ሰው ይህን ሁሉ ኃጢአት ይሸፍናሉ፤ በሐሰት ራእይ አየን ይላሉ፤ የውሸት ትንቢትም ይናገራሉ፤ ይህ የልዑል እግዚአብሔር ቃል ነው ይላሉ፤ ነገር ግን እኔ እግዚአብሔር ምንም ቃል አልነገርኳቸውም። 29 የሀገሪቱ ሰዎች ዝርፊያና ቅሚያ ያካሄዳሉ፤ ድኾችን፥ ችግረኞችንና መጻተኞችን ፍትሕ በመንሣት ይበድላሉ። 30 በቊጣዬ አገሪቱን ከማጥፋቴ በፊት የቅጽር ግንብ የሚሠራ፥ ቅጽሮቹ በፈረሱበት በኩል በመቆም በእኔና በሕዝቡ መካከል ገብቶ ቊጣዬን የሚያበርድ ሰው ፈለግኹ፤ ነገር ግን ማንንም አላገኘሁም። 31 ስለዚህ ቊጣዬን በእነርሱ ላይ አወርዳለሁ፤ በኀይለኛ ቊጣዬም አጠፋቸዋለሁ፤ በደላቸውንም በራሳቸው ላይ እመልሳለሁ።” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው። |