ሕዝቅኤል 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበኢየሩሳሌም ላይ የእግዚአብሔር ቅጣት 1 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም መልሰህ በተቀደሱ ቦታዎችዋ ላይና በእስራኤል ምድር ላይ ትንቢት ተናገር። 3 እንዲህም በላት! ‘እኔ በአንቺ ላይ ተነሥቼአለሁ፤ ሰይፉን ከሰገባው አውጥቼ ኃጢአተኛውንና ጻድቁን ከመካከልሽ አጠፋለሁ። 4 ከመካከልሽም ኃጢአተኛውንና ጻድቁን ለማጥፋት ከደቡብ እስከ ሰሜን ባሉት ሁሉ ላይ ሰይፌ ከሰገባው ይመዘዛል። 5 እኔ እግዚአብሔር ሰይፌን እንደ መዘዝኩና መልሼም ወደ አፎቱ እንደማልከተው ሰው ሁሉ ያውቃል።’ 6 “ስለዚህ በእነርሱ ፊት በተሰበረ ልብና በመረረ ሐዘን ቃትት! የሰው ልጅ ሆይ! ቃትት!” 7 “ለምን ትቃትታለህ” ብለው ቢጠይቁህ “ስለሚመጣው ወሬ ነው” ትላቸዋለህ፤ “በዚያም ወሬ ልብ ሁሉ ይቀልጣል፤ እጅ ሁሉ ይዝላል፤ ወኔ ሁሉ ይከዳል፤ ጒልበት ሁሉ እንደ ውሃ ይፈስሳል፤ እነሆ እየመጣ ነው፤ በእርግጥ ይፈጸማል” ይላል ልዑል እግዚአብሔር። 8 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 9 “የሰው ልጅ ሆይ! ትንቢት ተናገር፤ እኔ እግዚአብሔር የምለውን ለሕዝቡ ተናገር፤ ሰይፍ! የተሳለና የተወለወለ ሰይፍ! 10 ለመግደያ ተስሎአል፤ እንደ መብረቅ ለማብለጭለጭ ተወልውሎአል፤ ሕዝቤ የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያና ቅጣት ሁሉ ችላ ስላሉ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ደስታ አይኖርም። 11 ሰይፉ ተወልውሎ በእጅ እንዲያዝ ተሰጥቶአል፤ ለገዳዩ ይሰጥ ዘንድ ተስሎና ተወልውሎ ተዘጋጅቶአል። 12 የሰው ልጅ ሆይ! በሐዘን ጩኽ፤ ይህ ሰይፍ የተዘጋጀው ሕዝቤንና የእስራኤልን መሪዎች ለማጥፋት ነው። እነርሱም ከቀሩት ሕዝቤ ጋር ይገደላሉ፤ ስለዚህ በሐዘን ደረትህን ምታ። 13 ሕዝቤን እፈትናለሁ፤ ንስሓ መግባት እምቢ ቢሉ ይህ ሁሉ በእነርሱ ላይ ይደርሳል። እኔ ጌታ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 14 “አሁንም የሰው ልጅ ሆይ፥ ትንቢት ተናገር፤ እጅህን በቊጣ አማታው፤ ሰይፉም በመደጋገም ተወዛውዞ እየዞረም የሚገድል፥ የሚያሸብርና የሚያርድ ሰይፍ ነው፤ 15 ሕዝቤ በፍርሃት በመሞላት ተሰናክለው ይወድቃሉ፤ እንደ መብረቅ በሚያብለጨልጭ፥ ለመግደያ የተዘጋጀውን ሰይፍ፥ በየበራፋቸው አድርጌአለሁ። 16 አንተ ስለታም ሰይፍ! ስለትህ በዞረበት በቀኝና በግራ ቈራርጥ! 17 እኔም በቊጣ እጄን አማታለሁ፤ ኀይለኛ ቊጣዬም ይበርዳል፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” የባቢሎን ንጉሥ ሰይፍ 18 እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፦ 19 “የሰው ልጅ ሆይ! የባቢሎን ንጉሥ ሰይፉን ይዞ የሚመጣባቸውን ሁለቱን መንገዶች ምልክት አድርግባቸው፤ የሁለቱም መነሻቸው አንዲት አገር ናት፤ ሁለቱ መንገዶች በሚገናኙበት መስቀለኛ ስፍራ ወደ ከተማ የሚያመራውን ምልክት ትከል። 20 ለጦሩ ወደ አሞናውያን ከተማ ራባ በሚወስደው መንገድ ላይና እንዲሁም ወደ ተመሸገችው የይሁዳ ከተማ ወደ ኢየሩሳሌም በሚወስደው መንገድ ላይ የአቅጣጫ ምልክት አድርግ። 21 የባቢሎን ንጉሥ በመስቀለኛ መንገዶቹ መታጠፊያ አጠገብ ይቆማል፤ በየትኛው መንገድ መሄድ እንዳለበት ለማወቅ ፍላጻዎችን ይወረውራል፤ ጣዖቶቹንም ምክር ይጠይቃል፤ ለመሥዋዕት ከታረደ እንስሳ የጒበት ሞራ ወስዶም ይመረምራል። 22 እነሆ ቀኝ እጁ ‘ኢየሩሳሌም!’ የሚል ጽሑፍ ያለበትን ፍላጻ አንሥቶ ይይዛል፤ እርሱም ሄዶ ምሽግ ማፍረሻዎችን እንዲያዘጋጅ፥ ለጦርነት የሚያዘጋጅ ድንፋታ እንዲያሰማ፥ ምሽግ ማፍረሻዎችን ወደ ቅጽር በሮቹ እንዲያስጠጋ፥ ዐፈር ቈልሎ እንዲደለድልና የከበባ ምሽግ እንዲሠራ ይነግረዋል። 23 እያንዳንዱ ሰው ለባቢሎን ታማኝ ለመሆን ቃል ስለ ገባ ማንም ይህ ነገር ይፈጸማል ብሎ አያምንም ነበር፤ የባቢሎን ንጉሥ በሚማርካቸው ጊዜ ግን ኃጢአታቸውን ያስታውሳቸዋል። 24 እንግዲህ እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምለው ይህ ነው፤ ኃጢአታችሁ ተገልጦአል፤ በደለኞች መሆናችሁን ሰው ሁሉ ያውቃል፤ በምታደርጉት ነገር ሁሉ ኃጢአተኞች መሆናችሁን ታሳያላችሁ፤ ስለዚህ ተማርካችሁ ትሄዳላችሁ። 25 “አንተ ክፋትና ርኲሰት የሞላብህ የእስራኤል መሪ! ለመጨረሻ ጊዜ የምትቀጣበት ቀን እነሆ ቀርቦአል። 26 እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ፤ የራስ ዘውድህን አንሣ! ጥምጥምህን አውልቅ! ነገሮች እንደ ነበሩ አይቀሩም፤ ዝቅተኞችን በሥልጣን ከፍ አድርገህ አሁን ገዢዎች የሆኑትን ዝቅ አድርጋቸው! 27 ጥፋት! ጥፋት! አዎ በእርግጥ ከተማይቱ እንድትጠፋ አደርጋለሁ፤ ነገር ግን ከተማይቱን እንዲቀጣ የመረጥኩት እስከሚመጣ ድረስ ይህ አይሆንም፤ በዚያን ጊዜ ለእርሱ አሳልፌ እሰጠዋለሁ። ሰይፍና ዐሞናውያን 28 “የሰው ልጅ ሆይ! ትንቢት ተናገር፤ ስለ ዐሞናውያንና ስለ ስድባቸው እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምለውን እንዲህ ብለህ አስታውቃቸው፤ ‘አጥፊ ሰይፍ ተዘጋጅቶአል፤ ለመግደልና ለማውደም እንደ መብረቅም ለማብለጭለጭ ተወልውሎአል!’ 29 የምታዩት ራእይ ሐሰት ነው፤ የምትናገሩትም የትንቢት ቃል ውሸት ነው፤ እናንተ ክፋትና ርኲሰት የሞላችሁ ናችሁ፤ ለመጨረሻ ጊዜ ቅጣት የምትቀበሉበት ቀን ቀርቦአል፤ በአንገታችሁ ላይ ሰይፍ ተቃጥቶአል። 30 “ ‘ሰይፉን ወደ አፎቱ መልሱ! በተፈጠራችሁበት ስፍራ፥ በተወለዳችሁበትም አገር እፈርድባችኋለሁ፤ 31 የቊጣዬ ኀይል እንደ ተቀጣጠለ እሳት በእናንተ ላይ ይወርዳል፤ የማጥፋት ልምድ ላላቸው ለጨካኞች ሰዎች አሳልፌ እሰጣችኋለሁ፤ 32 በእሳት ትጠፋላችሁ፤ ደማችሁ በገዛ አገራችሁ ላይ ይፈስሳል፤ ዳግመኛም የሚያስታውሳችሁ አይኖርም፤’ ” እግዚአብሔር ይህን ተናግሮአል። |