ሕዝቅኤል 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር ሕዝቅኤልን ለነቢይነት መጥራቱ 1 ከዚያም በኋላ “የሰው ልጅ ሆይ! ተነሥተህ በእግርህ ቁም፤ እኔም አነጋግርሃለሁ” አለኝ። 2 በተናገረኝም ጊዜ ወዲያውኑ የእግዚአብሔር መንፈስ በውስጤ ገብቶ በእግሮቼ አቆመኝ፤ የሚናገረኝንም ሰማሁ፤ 3 እርሱም እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! በእኔ ላይ ወደ ዐመፁት ወደ እስራኤል ሕዝብ እልክሃለሁ፤ እነርሱና የቀድሞ አባቶቻቸው እስከ ዛሬ ድረስ በእኔ ላይ እንዳመፁ ናቸው። 4 ትውልዱ እልኸኛና ልበ ደንዳና ነው። ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ እንድትነግራቸው ወደ እነርሱ እልክሃለሁ። 5 እነዚያ ዐመፀኞች ቢሰሙህም ባይሰሙህም ነቢይ በመካከላቸው መኖሩን ያውቃሉ። 6 “ነገር ግን የሰው ልጅ ሆይ! እነርሱንም ሆነ የሚናገሩትን ቃል አትፍራ፤ እንደ እሾኽና እንደ አሜከላ ሆነውብህ በጊንጦች መካከል እንደምትኖር ሆነህ ቢሰማህም ቃላቸውንም ሆነ የእነዚያን ዐመፀኞች የቊጣ ፊት ከቶ አትፍራ። 7 ዐመፀኛ ሕዝብ ስለ ሆኑ ቢሰሙህም ባይሰሙህም እኔ የምልህን ቃል ትነግራቸዋለህ። 8 “የሰው ልጅ ሆይ! እኔ የምነግርህን ስማ፤ አንተም እንደ እነርሱ ዐመፀኛ አትሁን፤ አፍህን ክፈት፤ እኔም የምሰጥህን ብላ።” 9 ከዚህ በኋላ የብራና ጥቅል የያዘ እጅ ወደ እኔ ተዘርግቶ አየሁ። 10 ያም እጅ የብራናውን ጥቅል ፈቶ በፊቴ ዘረጋው፤ እርሱም በሁለት በኩል ጽሑፍ ያለበት መሆኑን አየሁ፤ በእርሱም ላይ የለቅሶ፥ የሐዘንና የዋይታ ቃሎች ተጽፈውበት ነበር። |