ሕዝቅኤል 19 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየሐዘን ሙሾ 1 እግዚአብሔር ይህን የሐዘን ሙሾ ስለ እስራኤል መሳፍንት እንድደረድር ነገረኝ፦ 2 እናትህ በአንበሶች መካከል እንዴት ያለች እንስት አንበሳ ነበረች! በደቦል አንበሶች መካከል ተዝናንታ ግልገሎችዋን አሳደገች፤ 3 ከግልገሎችዋ አንዱን ተንከባክባ አሳደገችው እርሱም ደቦል ሆነ፤ አደንንም ተማረ፤ ሰውንም መብላት ጀመረ። 4 ሕዝቦች በእርሱ ላይ ጮኹበት በቈፈሩት ጒድጓድም ውስጥ ተያዘ፤ በመንጠቆም አፍንጫውን ሰንገው እየጐተቱ ወደ ግብጽ ወሰዱት። 5 የነበራት ዓላማ እንዳልተሳካ አይታ ተስፋ በቈረጠች ጊዜ ከግልገሎችዋ ሌላውን ወስዳ ተንከባክባ በማሳደግ ደቦል አንበሳ አደረገችው። 6 ከሌሎች አንበሶች ጋር መዞር ጀመረ። ደቦል አንበሳ ሆነ፤ ዐደንንም ተማረ፤ ሰውንም መብላት ጀመረ። 7 ምሽጎቻቸውን ሰባበረ፤ ከተሞቻቸውንም አፈራረሰ፤ እርሱ ባገሣ ቊጥር ምድሪቱና የሚኖሩባት ሰዎች ሁሉ ይሸበራሉ፤ 8 ሕዝቦች ሁሉ በእርሱ ላይ ተነሡበት፤ ሁላቸውም ከየቦታው መጡ፤ መረባቸውን ዘረጉበት፤ በጒድጓዳቸውም ተያዘ፤ 9 በመንጠቆ ይዘው በወጥመድ ጎጆ ውስጥ አኖሩት፤ ወደ ባቢሎን ንጉሥ ዘንድም ወሰዱት፤ ድምፁ ዳግመኛ በእስራኤል ኰረብቶች እንዳይሰማ፥ ወደ እስር ቤት አስገቡት። 10 እናትህ በውሃ አጠገብ እንደ ተተከለች የወይን ተክል ነበረች፤ እርስዋም ከውሃው መትረፍረፍ የተነሣ በቅርንጫፎችዋና በፍሬ እንደ ተሞላች የወይን ተክል ሆነች፤ 11 ቅርንጫፎቹ ብርቱዎች ስለ ነበሩ፥ በትረ መንግሥት እስከሚገኝባቸው ድረስ አደጉ፤ የወይን ተክሉም ጥቅጥቅ ካለው ደን በላይ አደገ፤ ርዝመቱ ከብዙ ቅርንጫፎች ጋር ከፍ ብሎ ታየ። 12 ነገር ግን በቊጣ ከስሩ ተነቅሎ ወደ ምድር ተጣለ። ከበረሓ የሚነሣ የምሥራቅ ነፋስ አደረቀው፤ ፍሬዎቹም ረገፉ፤ ብርቱ የሆኑት ቅርንጫፎቹም ደረቁ፤ እሳትም በላቸው። 13 አሁን ደግሞ በበረሓ፥ ውሃ በሌለበት ደረቅ ምድር ተተከለ። 14 ከወይን ተክሉ ግንድ እሳት ወጣ፤ ቅርንጫፎቹንና ፍሬውን ሁሉ እሳት በላው፤ ቅርንጫፎቹ ዳግመኛ ብርቱ አይሆኑምና በትረ መንግሥት መሆንም አይችሉም። እንግዲህ በመደጋገም የሚደረደረው ሙሾ ይህ ነው። እርሱም ለለቅሶ ያገለግላል። |