Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 18 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ሰው የሚቀጣው ራሱ በሠራው ኃጢአት ብቻ መሆኑ

1 እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፦

2 “በእስራኤል ምድር ተደጋግሞ የሚነገር ይህ ምሳሌ ምንድን ነው? ‘ወላጆች ጐምዛዛ የወይን ፍሬ በሉ፤ ነገር ግን የልጆቻቸውን ጥርስ አጠረሰ’ ይላሉ፤

3 “እኔ ሕያው እንደ መሆኔ ይህን ምሳሌ በእስራኤል ዳግመኛ አትናገሩትም፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ።

4 የእያንዳንዱ ሰው ሕይወት የእኔ ነው፤ የወላጅም ሆነ የልጅ ሕይወት የእኔ መሆኑን ዕወቁ፤ ኃጢአት የሚሠራ ሰው ራሱ ይሞታል።

5 “ሰው ጻድቅ፥ ፍትሓዊና ትክክለኛ ቢሆን፥

6 ለእስራኤላውያን ጣዖቶች አይሰግድም፤ ወይም በተከለከሉ መስገጃዎች የተሠዋውን ማንኛውንም ነገር አይመገብም፤ የሌላ ሰው ሚስትን አይደፍርም፤ ወይም የወር አበባ ከታያት ሴት ጋር ግንኙነት አያደርግም፤

7 ማንንም አይጨቊንም፤ ነገር ግን በመያዣ የያዘውን ይመልሳል፤ አይቀማም፤ ለተራበ ያበላል፤ ለታረዘ ያለብሳል፤

8 ገንዘቡን በአራጣ አያበድርም፤ ወይም ከፍተኛ ወለድ አይወስድም፤ ክፉ ነገር ከመሥራት ይቈጠባል፤ ጠበኞችን ለማስታረቅ ትክክለኛ ፍርድን ይሰጣል።

9 እንዲህ ዐይነቱ ሰው ሕጌን ይፈጽማል፤ ሥርዓቴን ያከብራል፤ ያ ሰው ጻድቅ ስለ ሆነ በሕይወት ይኖራል፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ።

10 “ነገር ግን ይህ ሰው ዐመፀኛና ነፍሰ ገዳይ የሆነ፥ ከእነዚህም ጥፋቶች አንዱን የፈጸመ ልጅ ቢኖረው፥

11 አባቱ ከእነዚህ በደሎች አንዱን እንኳ የፈጸመ ባይሆን፥ ልጁ ግን በተራራ በጣዖት ቦታዎች የታረደውን ቢበላ፥ የሰውን ሚስት ቢደፍር፥

12 ድኾችንና ችግረኞችን ቢያስጨንቅ፥ ቢቀማ፥ ገንዘብ ሲያበድር በመያዣ ስም የወሰደውን ቢያስቀር፥ በአሕዛብ መስገጃ ስፍራዎች ጣዖትን ቢያመልክ አጸያፊ ነገሮችን ቢያደርግ፥

13 ገንዘቡን በአራጣ ቢያበድርና ከፍተኛ ወለድ ቢያስከፍል፥ ታዲያ እንዲህ ዐይነቱ ሰው በሕይወት ሊኖር ይችላልን? ከቶ በሕይወት ሊኖር አይችልም፤ ይህን ሁሉ አጸያፊ ነገር በማድረጉ በእርግጥ ይሞታል፤ ለሞቱም ተጠያቂው እርሱ ራሱ ይሆናል።

14 “ነገር ግን ይህ ሰው በተራው ወንድ ልጅ ቢኖረው አባቱ የሚሠራውን ኃጢአት ሁሉ ቢያይ፥ ነገር ግን የአባቱን ምሳሌነት ባይከተል፥

15 ለእስራኤላውያን ጣዖቶች ባይሰግድ፥ ወይም በተከለከሉ መስገጃዎች የተሠዋውን ማንኛውንም ነገር ባይመገብ፥ የሌላ ሰው ሚስት ባይደፍር፥

16 ማንንም ባይጨቊን፥ ወይም የሰውን ሀብት ባይቀማ፥ ገንዘብ ሲያበድር በመያዣ የወሰደውን ባያስቀር፥ ለተራበ ቢያበላ፥ ለታረዘም ቢያለብስ፥

17 በድኾች ላይ ምንም ዐይነት ግፍ ባይሠራ፥ ገንዘቡን በአራጣ አበድሮ ከፍተኛ ወለድ ባያስከፍል፥ ሕጌን ቢያከብር፥ ሥርዓቴን ቢከተል፥ እንዲህ ዐይነቱ ሰው በእርግጥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አባቱ በሠራው ኃጢአት ምክንያት አይሞትም።

18 አባቱ ግን ብዝበዛን ስለ ፈጸመ፥ ወንድሙን ስለ ቀማና በሕዝቡ ዘንድ መልካም ያልሆነውን ነገር ስላደረገ በበደሉ ይሞታል።

19 “ ‘ታዲያ ልጁ በአባቱ ኃጢአት ምክንያት ያልተቀጣው ስለምንድን ነው?’ ትሉ ይሆናል፤ ልጁ ትክክልና መልካም የሆነውን ነገር አድርጎአል፤ ሕጌን አክብሮአል፤ ስለዚህ እርሱ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፤

20 ሞት የሚገባው ኃጢአት ለሚሠራ ሰው ብቻ ነው፤ ልጅ ስለ አባቱ ኃጢአት አይቀጣም፤ አባትም ስለ ልጁ ኃጢአት አይቀጣም፤ ደግ ሰው በደግነቱ መልካም ዋጋውን ያገኛል፤ ክፉ ሰውም በክፋቱ ይቀጣል።

21 “ክፉ ሰው ኃጢአት መሥራትን ትቶ ሕጌን ቢጠብቅ፥ ትክክልና መልካም የሆነውን ነገር ቢያደርግ፥ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም፤

22 ትክክል የሆነውን ነገር ስላደረገም የሠራው ኃጢአት ሁሉ ይቅር ተብሎለት በሕይወት ይኖራል።

23 እኔ በክፉ ሰው ሞት የምደሰት ይመስላችኋልን? አይደለም፤ እኔ ደስ የሚለኝ ስለ ኃጢአቱ ንስሓ ገብቶ በሕይወት በሚኖር ሰው ነው፤ ይላል ልዑል እግዚአብሔር።

24 “ነገር ግን ደግ ሰው መልካም ማድረጉን ትቶ ክፉ ሰዎች የሚያደርጉአቸውን ክፉና አጸያፊ ነገሮች ማድረግ ቢጀምር፥ በሕይወት መኖር የሚችል ይመስላችኋልን? አይደለም! እንዲያውም ያደረገው የደግነት ሥራ ሁሉ አይታሰብለትም፤ ባለመታመኑና ኃጢአተኛም በመሆኑ ምክንያት ይሞታል።

25 “እናንተም ‘እንዲህ ከሆነ እግዚአብሔር የሚያደርገው ነገር ትክክል አይደለም’ ትሉ ይሆናል፤ እናንተ እስራኤላውያን እኔን አድምጡ፤ እኔ የማደርገው ነገር ሁሉ ትክክል እንዳልሆነ ታስባላችሁን? ነገር ግን ትክክል ያልሆነው የእናንተ አካሄድ ነው።

26 ጻድቅ ሰው መልካም ማድረጉን ትቶ ክፉ ሥራ ሠርቶ ቢሞት የሚሞተው በኃጢአቱ ምክንያት ነው፤

27 እንዲሁም ክፉ ሰው ኃጢአት መሥራት ትቶ ፍትሓዊና ትክክለኛ ሥራ ቢሠራ ሕይወቱን ያድናል፤

28 የሚያደርገው ነገር ከንቱ መሆኑን ተገንዝቦ ኃጢአት መሥራቱን ስለ ተወ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም፤

29 እናንተ እስራኤላውያን ግን ‘ልዑል እግዚአብሔር የሚያደርገው ነገር ትክክል አይደለም’ ትላላችሁ፤ ታዲያ የእኔ ሥራ ትክክል ያልሆነ ይመስላችኋልን? ትክክል ያልሆነውስ የእናንተ አካሄድ ነው።

30 “አሁንም እኔ ልዑል እግዚአብሔር ለእናንተ ለእስራኤላውያን የምላችሁ ይህ ነው፤ በክፉ ሥራችሁ እያንዳንዳችሁን እቀጣለሁ፤ ስለዚህ ከምታደርጉት ክፋት ተመለሱ፤ አለበለዚያ ኃጢአታችሁ ያጠፋችኋል።

31 ከክፉ ሥራችሁ ሁሉ ተላቃችሁ አዲስ መንፈስና አዲስ ልብ ይኑራችሁ፤ እናንተ እስራኤላውያን ለምን ትሞታላችሁ?

32 እኔ ማንም ሰው እንዲሞት አልፈልግም፤ ስለዚህ ሁላችሁም ከኃጢአታችሁ ተመልሳችሁ በሕይወት ኑሩ፤” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告