Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የንስርና የወይን ተክል ምሳሌ

1 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦

2 “የሰው ልጅ ሆይ! ለእስራኤላውያን እንቆቅልሽ አቅርብላቸው፤ በምሳሌም አብራርተህ ግለጥላቸው፤

3-4 እኔ ልዑል እግዚአብሔር ለእነርሱ የምለውን ያውቁ ዘንድ ይህን ንገራቸው፤ የተዋቡ ላባዎችና ታላላቅ ክንፎች ያሉት አንድ ግዙፍ ንስር ነበረ፤ ይህም ንስር ወደ ሊባኖስ ተራራዎች በረረ፤ በአንድ የሊባኖስ ዛፍ ላይ አርፎም ጫፉን በመቊረጥ የንግድ ሥራ ወደ ተስፋፋበት ወደ አንድ አገር አምጥቶም ነጋዴዎች በበዙባት ከተማ አኖረው።

5 ከዚያም በኋላ ከእስራኤል ምድር ዘር ወስዶ በቂ ውሃ እያገኘ በሚያድግበት በአንድ ለም ስፍራ ተከለው።

6 ተክሉም አደገና ከምድር ብዙ ከፍ ሳይል በሰፊው የተንሰራፋ የወይን ተክል ሆነ፤ ቅርንጫፎቹ ወደ ንስሩ ከፍ ብለው አደጉ፤ ሥሮቹም ወደ መሬት ዘልቀው ገቡ፤ የወይን ተክሉ ብዙ ቅርንጫፎችና ቅጠሎች አብቅሎ ነበር።

7 “እንዲሁም ታላላቅ ክንፎችና ብዙ ላባዎች ያሉት ሌላ ግዙፍ ንስር ነበረ፤ አሁን እንግዲህ የወይን ተክሉ ሥሮቹንና ቅርንጫፎቹን ወደ ንስሩ ዘረጋ፤ ይህንንም ያደረገው ከተተከለበት መደብ ውሃ ያጠጣው ዘንድ ነው።

8 ነገር ግን የወይኑ ተክል እንደገና የተተከለው ቅጠሉ በሚገባ ለምልሞ ፍሬ በማፍራት የተዋበ ተክል መሆን በሚችልበት በቂ ውሃ ባለበት ስፍራ ነበር።

9 “ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ተናገር፦ ይህ የተተከለው የወይን ተክል ይጸድቃልን? የመጀመሪያው ንስር ሥሩን ነቅሎ ፍሬው እንዲበሰብስና እንዲደርቅ እንዲሁም ለምለም ቅጠሉ እንዲጠወልግ አያደርገውምን? ሥሩን ለመንቀል ጠንካራ የጦር መሣሪያ ወይም ኀይለኛ ሠራዊት አያስፈልገውም።

10 የወይኑ ተክል ተተክሏል። ታዲያ ጸድቆ ማደግ ይችላልን? ኀይለኛው የበረሓ ነፋስ በሚመታው ጊዜ ባደገበት በመደቡ ላይ እንዳለ ፈጽሞ አይደርቅምን?”


የምሳሌው ትርጒም

11 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦

12 “የምሳሌውን ትርጒም ያውቁ እንደ ሆነ እስቲ እነዚህን ዐመፀኞች ጠይቃቸው፤ የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ንጉሡንና መሳፍንቱን ወደ ባቢሎን የወሰዳቸው መሆኑን ንገራቸው፤

13 ከንጉሡም ቤተሰብ አንዱን ወስዶ ከእርሱ ጋር የስምምነት ውል አደረገ፤ ለእርሱም ታማኝ እንዲሆንለት በመሐላ ቃል አስገባው፤ ሌሎቹንም የታወቁ ሰዎች ወሰዳቸው።

14 ይህንንም ያደረገው የይሁዳ መንግሥት በትሕትናና በታዛዥነት በቃል ኪዳኑ ጸንቶ እንዲኖር ለማድረግ ነው።

15 ነገር ግን የይሁዳ ንጉሥ ዐምፆ ፈረሶችንና ታላቅ ሠራዊት እንዲያመጡለት መልእክተኞችን ወደ ግብጽ ላከ፤ ታዲያ ይህ ዕቅዱ ይሳካለታልን? በዚህስ ሊያመልጥ ይችላልን? ውሉን የሚያፈርስ ከሆነ ከቅጣት ከቶ ያመልጣልን?

16 “ልዑል እግዚአብሔር ሕያው አምላክ እንደ መሆኔ ይህ ንጉሥ በዙፋን ላይ ካስቀመጠው ከባቢሎን ንጉሥ ጋር በመሐላ የገባውን የስምምነት ውል በማፍረሱ ምክንያት በባቢሎን ይሞታል።

17 ባቢሎናውያን ብዙ ሰዎችን ለመግደል ቦይ ቆፍረው ዐፈር በመደልደል ምሽግ በሚሠሩበት ጊዜ፥ የግብጽ ንጉሥ ብዙ ተዋጊና ብርቱ ሠራዊት እንኳ መጥቶ በመዋጋት ሊረዳው አይችልም።

18 እርሱ መሐላውን በመናቅ ቃል ኪዳኑን ስላፈረሰና እጁን ከሰጠ በኋላ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ስላደረገ አያመልጥም።”

19 ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “እኔ ሕያው እንደ መሆኔ በእኔ ስም የማለውን መሐላ ንቆ ቃል ኪዳኑን በማፍረሱ መሐላው በራሱ ላይ እንዲደርስ አደርጋለሁ።

20 መረቤን በእርሱ ላይ ዘርግቼ በወጥመድ እንዲያዝ አደርጋለሁ፤ በእኔ ላይ ስለ ፈጸመው ክሕደት ወደ ባቢሎን አምጥቼ እፈርድበታለሁ።

21 ምርጥ የሆኑ ወታደሮቹ በጦር ሜዳ ይገደላሉ፤ ከሞት የሚያመልጡትም በየአቅጣጫው ይበተናሉ፤ በዚያን ጊዜ ይህን የተናገርኩት እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።”


እግዚአብሔር የሰጠው የተስፋ ቃል

22 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ከሊባኖስ ዛፍ ጫፍ ላይ አንድ ቅርንጫፍ እወስዳለሁ፤ ከዚያም ላይ ከለጋዎቹ ቀንበጦች አንዱን እቀነጥባለሁ፤ እኔው ራሴ በከፍተኛ ተራራ ላይ እተክለዋለሁ።

23 የምተክለው በእስራኤል በሚገኝ በከፍተኛ ተራራ ላይ ነው፤ ይህንንም የማደርገው ቅርንጫፎችን አስገኝቶ ፍሬ በማፍራት የተዋበ የሊባኖስ ዛፍ እንዲሆን ነው። በሥሩም የተለያዩ ወፎች ይኖሩበታል፤ በቅርንጫፎቹም ጥላ ሥር ክንፍ ያላቸው ፍጥረቶች ሁሉ ጎጆዎቻቸውን ይሠሩበታል።

24 በምድሪቱ ያሉ ዛፎች ሁሉ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ፤ እኔ ረጃጅም ዛፎችን አሳጥራለሁ፤ አጫጭር ዛፎችንም ከፍ ብለው እንዲያድጉ አደርጋለሁ፤ እኔ ለምለም ዛፎችን አደርቃለሁ፤ ደረቅ ዛፎችንም አለመልማለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ፤ አደርጋለሁ ያልኩትንም ሁሉ እፈጽማለሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告