Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 16 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


እምነት የጐደላት ኢየሩሳሌም

1 እግዚአብሔርም እንደገና እንዲህ አለኝ፦

2 “የሰው ልጅ ሆይ! ኢየሩሳሌም ያደረገችው ነገር ምን ያኽል አጸያፊ እንደ ሆነ አስታውቃት፤

3 ልዑል እግዚአብሔር ስለ እርስዋ የሚለውንም እንዲህ ብለህ ንገራት፦ “የተወለድሽው በከነዓን ምድር ነበር፤ አባትሽ አሞራዊ ሲሆን እናትሽም ሒታዊ ነበረች፤

4 በተወለድሽ ጊዜ እትብትሽን አልተቈረጠም፤ ንጹሕ ትሆኚ ዘንድ በውሃ አልታጠብሽም፥ ወይም በጨው ታሽተሽ በጨርቅ አልተጠቀለልሽም።

5 ከነዚህ ነገሮች አንዱን እንኳ ለማድረግ ለአንቺ ርኅራኄ ያለው ማንም አልነበረም፤ ስትወለጂ የተጠላሽ ስለ ነበርሽ በሜዳ ላይ ተጣልሽ።

6 “እኔም በዚያ ሳልፍ በገዛ ደምሽ ተነክረሽ ስትንፈራገጪ አገኘሁሽ፤ በደም ተሸፍነሽ ልትሞቺ ነበረ፤ በሕይወት እንድትኖሪ አደረግሁሽ።

7 ምቾት እንዳለው ተክል እንድታድጊ አደረግሁ፤ ቁመትና ጠንካራ ሰውነት በመጨመር አድገሽ የተዋብሽ ወጣት ሆንሽ፤ ጡትሽ አጐጠጐጠ፤ ጠጒርሽ ረዘመ፤ ነገር ግን እርቃንሽን ነበርሽ።

8 “እንደገናም በአጠገብሽ ሳልፍ ጊዜሽ የፍቅር ዕድሜ ነበር፤ የተራቈተውን ሰውነትሽንም በመጐናጸፊያዬ ሸፍኜ ቃል ገባሁልሽ፤ ከአንቺም ጋር እንደ ጋብቻ ያለ ቃል ኪዳን ገብቼ የእኔ የግሌ አደረግሁሽ፤” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው።

9 “ከዚያም በኋላ መላ አከላትሽንና በደም የተበከለ ሰውነትሽን አጠብኩ፤ የወይራ ዘይትም ቀባሁሽ፤

10 ጥበብ ቀሚስ አለበስኩሽ፤ ከምርጥ ቆዳ የተሠራ ጫማ አደረግሁልሽ፤ ሐር ሻሽ በራስሽ ላይ አሰርኩልሽ፤ ውድ የሆነ ካባ ደረብኩልሽ።

11 በጌጥ አስጌጥኩሽ፤ የእጅ አንባርና የአንገት ድሪ አደረግሁልሽ።

12 ለአፍንጫሽ ቀለበት፥ ለጆሮሽ ጒትቻ፥ እንዲሁም በራስሽ ላይ የምትደፊው ውብ የሆነ አክሊል ሰጠሁሽ።

13 ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ብዙ ጌጣጌጦች ነበሩሽ፤ ከልዩ ልዩ ሐር የተሠሩና በጥልፍ ጌጥ የተዋቡ ውድ ልብሶች ነበሩሽ፤ ምርጥ ከሆነ ዱቄት የተጋገረ ዳቦ፥ ማርና የወይራ ዘይት ትመገቢ ነበር፤ ውበትሽ እጅግ እየጨመረ ስለ ሄደ ንግሥት ለመሆን በቃሽ።

14 ግርማ ሞገሴን በአንቺ ላይ አሳርፌ የተዋብሽ ስላደረግሁሽ እንከን ከሌለበት ቊንጅናሽ የተነሣ በሁሉ አገር ታወቅሽ።” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው።

15 “ነገር ግን በውበትሽና በዝናሽ ተማምነሽ ከዐላፊ አግዳሚ ሁሉ ጋር የዝሙት ሥራ ፈጸምሽ።

16 ከልብሶችሽ ጥቂቱን ወስደሽ የመስገጃ ስፍራዎችሽን አስጌጥሽባቸው፤ በዚያም አመንዝራነትሽን ቀጠልሽ፤ እነዚህ ድርጊቶች መፈጸም አልነበረባቸውም፤ ከቶም መፈጸም አይገባቸውም፤

17 እኔ የሰጠሁሽን ከብርና ከወርቅ የተሠሩ ጌጣጌጦችን ወስደሽ የወንድ ጣዖቶችን በመሥራት ከእነርሱ ጋር አመነዘርሽ።

18 እኔ የሰጠሁሽንም በጥልፍ ያጌጡ ልብሶችሽንም ወስደሽ ምስሎቹን አለበስሽ፤ እኔ የሰጠሁሽንም የወይራ ዘይትና ዕጣን ለምስሎቹ አቀረብሽ።

19 ምርጥ የሆነ ዱቄት የወይራ ዘይትና ማር. ምግብ እንዲሆንሽ ሰጥቼሽ ነበር፤ አንቺ ግን ጣዖቶችን ለማስደሰት መልካም መዓዛ ያለው መሥዋዕት አድርገሽ አቀረብሽ፤” ይህም ተደርጓል፤ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።

20 “ዝሙት መሥራትሽ አልበቃ ብሎሽ የወለድሽልኝንም ወንዶችና ሴቶች ልጆች ወስደሽ ለጣዖቶች መሥዋዕት በማድረግ አቀረብሻቸው።

21 ልጆቼን በማረድ ለጣዖቶች መሥዋዕት አድርገሽ አቀረብሽ።

22 እጅግ አጸያፊ በሆነ የአመንዝራነት ኑሮሽ የልጅነትሽን ሁኔታ አላስታወስሽውም፤ ይህም ማለት ራቁትሽን በደም ተነክረሽ ስትንፈራገጪ የነበርሽበት ጊዜ ፈጽሞ ትዝ አላለሽም።”


በኢየሩሳሌም ላይ የተሰነዘረ ወቀሳ

23 ልዑል እግዚአብሔር “ወዮልሽ! ወዮልሽ!” ይላል። ያን ሁሉ ክፉ ነገር ከፈጸምሽ በኋላ

24 መድረክ እየሠራሽ በየ አደባባዩ ለራስሽ ከፍ ያለ ቦታ አዘጋጀሽ።

25 በዚህ ዐይነት በየአውራ መንገዱ ዳር የጣዖት ማምለኪያ ቦታዎችን ሠርተሽ ውበትሽን አረከስሽ፤ ለመጣው ሁሉ ሰውነትሽን አሳልፈሽ እየሰጠሽ በየቀኑ አመንዝራነትሽን አበዛሽ።

26 እነዚያ ቅንዝረኞች የሆኑ ግብጻውያን ጐረቤቶችሽ ከአንቺ ጋር የዝሙት ሥራ እንዲፈጽሙ አደረግሽ፤ እኔን ለማስቈጣት ምንዝርናሽን አበዛሽ።

27 “አሁን ግን አንቺን ለመቅጣትና ድርሻሽ የሆነውንም በረከት ከአንቺ ለመቀነስ እጄን ዘርግቼአለሁ፤ እነርሱ የፈለጉትን እንዲያደርጉ አንቺን ለጠላቶችሽ፥ ብልግናሽ ለሚያስደነግጣቸው ለፍልስጥኤማውያን አሳልፌ ሰጥቼሻለሁ።

28 “ከሌሎች ጋር የምትፈጽሚው የዝሙት ሥራ አልበቃ ብሎሽ ከአሦራውያን ጋር አመነዘርሽ፤ ነገር ግን እነርሱም አላረኩሽም፤

29 ነጋዴዎች ለሆኑት ባቢሎናውያንም ወዳጅ ሆነሽ ታመነዝሪ ነበር፤ ነገር ግን እነርሱም አላረኩሽም።”

30 ልዑል እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ “ኀፍረተቢስ እንደ ሆነች አመንዝራ ሴት ይህን ሁሉ ማድረግሽ እንዴት መንፈሰ ደካማ ብትሆኚ ነው?

31 በየመንገዱ ዳር መድረክሽን ትሠሪአለሽ፤ በየአደባባዩም የጣዖት ማምለኪያ ቦታሽን ታዘጋጂአለሽ፤ ሆኖም እንደ ተራ አመንዝራ ሴት ገንዘብ ለመሰብሰብ እንኳ አልፈለግሽም።

32 አንቺ፥ ዘማዊት ሚስት! ባልዋን ማፍቀር ትታ ከባዕዳን ጋር እንደምታመነዝር ሴት ሆንሽ።

33 አመንዝራ ሴት ገንዘብ ይከፈላት ነበር፤ አንቺ ግን ገንዘብ በመቀበል ፈንታ ለወዳጆችሽ ስጦታ ታበረክቺአለሽ፤ ከየአቅጣጫው መጥተው ከአንቺ ጋር ያመነዝሩ ዘንድ መደለያ ገንዘብ ሰጠሽ።

34 ስለዚህም አንቺ ልዩ ዐይነት አመንዝራ ሴት ሆነሻል። ነገር ግን እንደዚህ እንድትሆኚ ያባበለሽ የለም፤ ገንዘብ ትከፍያቸዋለሽ እንጂ የሚከፍልሽ የለም፤ ስለዚህ በእርግጥ በአመንዝራነትሽ አንቺ ልዩ ነሽ።”


የእግዚአብሔር ፍርድ በኢየሩሳሌም ላይ

35 አንቺ አመንዝራ ኢየሩሳሌም! እግዚአብሔር የሚለውን ስሚ!

36 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በፍትወትሽ ተቃጥለሻል፤ ለፍቅረኞችሽ ገላሽን አጋልጠሽ ሰጥተሻል፤ አጸያፊ ጣዖቶችን ሁሉ አምልከሻል፤ የልጆችሽንም ደም አፍስሰሽ ለጣዖቶቹ መሥዋዕት አቅርበሻል።

37 በዚህ ምክንያት ከእነርሱ ጋር የተደሰትሽባቸውን ማለት የወደድሻቸውንና የጠላሻቸውን ሁሉ ተጋልጠሽ ዕርቃንሽን ያዩ ዘንድ ከአካባቢው ሰብስቤ አንቺን በፊታቸው አራቊትሻለሁ።

38 እኔ በአንቺ ላይ፥ ዝሙት በፈጸሙና ሕይወት ባጠፉ ሴቶች ላይ የሚፈረደውን ፍርድ እፈርድብሻለሁ፤ አንቺን በቅናቴና በቊጣዬ አጠፋሻለሁ።

39 በሥልጣናቸው ሥር እንድትሆኚ አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ እነርሱም መድረክሽንና ከፍተኛ ቦታዎችሽን ያፈራርሳሉ፤ ልብስሽን ገፈው ጌጣጌጥሽንም ወስደው ያራቊቱሻል፤ ባዶ እጅሽንም ያስቀሩሻል።

40 “በድንጋይ ወግሮ፥ በሰይፍ ቈራርጦ የሚገድልሽን ሕዝብ በአንቺ ላይ እያነሣሡ ናቸው፤

41 ቤቶችሽን በእሳት ያቃጥላሉ፤ በብዙ ሴቶች ፊት ፍርድን ተግባራዊ ያደርጉብሻል፤ በዚህ ዐይነት አመንዝራነትሽንና ለወዳጆችሽ የዝሙት ዋጋ መክፈልሽን እንድትተዪ አደርግሻለሁ።

42 ስለዚህ በአንቺ ላይ ያለኝ ቊጣ ያበቃል፤ ቅናቴም ከአንቺ ይርቃል፤ በአንቺ ላይ የነበረው ቊጣዬም ይበርዳል፤ ዳግመኛም አልቈጣም።

43 በልጅነትሽ ወራት ያደረግኹልሽን ሁሉ ረሳሽ፤ በፈጸምሽውም ክፉ ሥራ አስቈጣሽኝ፤ ስለዚህ እኔም በሠራሽው ኃጢአት መጠን ዋጋሽን እንድትቀበይ አደረግሁ፤ በፈጸምሽው አጸያፊ ሥራ ሁሉ ላይ የዝሙትን ርኲሰት መጨመርሽ ለምን ይሆን?” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው።


ልጅትዋም እንደ እናትዋ

44 እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “ኢየሩሳሌም ሆይ! ሰዎች ስለ አንቺ ‘ልጅትዋም እንደ እናትዋ ሆነች!’ እያሉ መተረቻ ያደርጉሻል።

45 በእርግጥም አንቺ የእናትሽ ልጅ ነሽ፤ እናትሽ ባልዋንና ልጆችዋን ጠልታ ነበር፤ አንቺም ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን እንደ ጠሉ እንደ እኅቶችሽ ነሽ፤ አንቺና እኅቶችሽ ሒታዊ እናትና አሞራዊ አባት ነበራችሁ።

46 “ታላቅ እኅትሽ ከመንደሮችዋ ጋር በስተ ሰሜን የምትገኘው ሰማርያ ናት፤ ታናሽ እኅትሽም ከመንደሮችዋ ጋር በስተ ደቡብ የምትገኘው ሰዶም ናት፤

47 የእነርሱን አካሄድ ተከትለሽ አጸያፊ ሥራቸውን መሥራትሽ ብቻ ሳይሆን በአካሄድሽ ሁሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ከእነርሱ የበለጠ ጥፋት ሠራሽ።

48 “እኔ ሕያው እንደ መሆኔ የምለው ይህ ነው፤ እኅትሽ ሰዶምና መንደሮችዋ አንቺና መንደሮችሽ ካደረጋችሁት የባሰ ክፋት አልሠሩም፤” ይላል ልዑል እግዚአብሔር።

49 የእኅትሽ የሰዶም በደል ይህ ነው፤ እርስዋና መንደሮችዋ ኲራት ተሰምቶአቸው ነበር። የተትረፈረፈ ምግብና የተዝናና ኑሮ ቢኖራቸውም ችግረኞችንና ድኾችን አይረዱም ነበር።

50 እነርሱ ትዕቢተኞች በመሆን እኔ የምጠላውን ነገር ሁሉ ፈጸሙ፤ አንቺም እንደምታውቂው ደመሰስኳቸው።

51 “ሰማርያም ብትሆን የአንቺን ግማሽ ያኽል እንኳ ኃጢአት አልሠራችም፤ ከእርስዋ ይበልጥ አንቺ እጅግ አጸያፊ የሆነ ኃጢአት ሠርተሻል። የአንቺ ርኲሰት ከእኅቶችሽ ጋር ቢመዛዘን እነርሱን ከበደል ነጻ ያስመስላቸዋል።

52 እነሆ አሁንም ውርደትሽን ተሸከሚ፤ የአንቺ ኃጢአት እጅግ የከፋ ከመሆኑ የተነሣ እኅቶችሽ ከአንቺ ጋር ሲነጻጸሩ ምንም በደል የሌለባቸው ንጹሖች መስለው ይታያሉ፤ አሁንም እኅቶችሽን በደል የሌለባቸው ንጹሖች እንዲመስሉ በማድረግሽ ኀፍረትን እንደ ልብስ ተከናንበሽ ተቀመጪ።”


የሰዶምና የሰማርያ መታደስ

53 እግዚአብሔር ስለ ኢየሩሳሌም እንዲህ አለ፦ “ለሰዶምና ለመንደሮችዋ፥ ለሰማርያና መንደሮችዋ የቀድሞ ሀብታቸውን እንደምመልስ የአንቺንም ሀብት እመልስልሻለሁ።

54 አንቺም ውርደትሽን ተከናንበሽ ባደረግሽው ነገር ሁሉ ታፍሪአለሽ። ሰዶምና ሰማርያ ይህን ሁናቴሽን በሚያዩበት ጊዜ ያንቺን ያኽል ኃጢአተኞች ባለመሆናቸው ይጽናናሉ።

55 እኅቶችሽን በተመለከተ ግን ሰዶምና መንደሮችዋ ሰማርያና መንደሮችዋ ወደ ቀድሞ ሁናቴአቸው ይመለሳሉ፤ እንዲሁም አንቺና መንደሮችሽ ወደ ቀድሞ ሁናቴአችሁ ትመለሳላችሁ።

56 ዕብሪተኛ በነበርሽበት ዘመን እኅትሽ ሰዶም የአንቺ መሳለቂያ አልነበረችምን?

57 ይህንንስ ያደረግሽው የአንቺ በደል ከመታወቁ በፊት አይደለምን? አሁን ግን አንቺ ለሶርያ ከተሞችና ለጐረቤቶቻቸው እንዲሁም ለፍልስጥኤም ከተሞችና ባካባቢው ላሉ ለሚንቁሽ ሁሉ መሳለቂያ ሆነሻል።

58 በስድነትሽ በአጸያፊ ተግባርሽ ቅጣትሽን መቀበል አለብሽ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።”


ለዘለዓለም የሚጸና ቃል ኪዳን

59 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የሰጠሽውን የተስፋ ቃል ንቀሽ ቃል ኪዳን በማፍረስሽ የሚገባሽን ቅጣት እሰጥሻለሁ።

60 ነገር ግን በወጣትነትሽ ወራት ከአንቺ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አስታውሳለሁ። ከአንቺ ጋርም የዘለዓለሙን ቃል ኪዳን አጸናለሁ።

61 ታላቅና ታናሽ እኅቶችሽን ወስጄ ለአንቺ እንደ ልጆችሽ አድርጌ በምሰጥበት ጊዜ የቀድሞውን አካሄድሽን አስታውሰሽ ታፍሪአለሽ። ይህ የሚሆነው ግን ከአንቺ ጋር በገባሁት ቃል ኪዳን መሠረት አይደለም።

62 ከአንቺ ጋር ቃል ኪዳኔን አድሳለሁ። አንቺም በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቂያለሽ፤

63 ይህንንም የማደርገው፥ ለፈጸምሽው በደል ሁሉ ይቅርታ ሳደርግልሽ ሥራሽን በማስታወስ በድንጋጤ ዐፍረሽ ጸጥ እንድትዪ ነው፤” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告