ሕዝቅኤል 15 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምስለ ወይን ተክል የቀረበ ምሳሌ 1 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! የወይን ግንድ ከሌሎች ዛፎች ግንድ ቅርንጫፎች ከዱር ዛፎች ቅርንጫፍ በምን ይበልጣል? 3 አንድ ነገር እንኳ ለመሥራት ይጠቅማልን? የዕቃ መስቀያ ኩላብ እንኳ ከእርሱ ሊሠራ ይችላልን? 4 የእሳት ማቀጣጠያ ከመሆን በቀር ሌላ ጥቅም የለውም፤ ጫፎቹ ነደው መካከሉ ካረረ በኋላ በእርሱ አንድ ነገር እንኳ መሥራት ይቻላልን? 5 ከመቃጠሉ በፊት እንኳ ዋጋቢስ ከነበረ አሁንማ እሳቱ ካቃጠለውና ካሳረረው በኋላ የባሰውን ጥቅም የሌለው ይሆናል።” 6 ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “በዱር ካሉ ዛፎች መካከል የወይንን ግንድ ለማገዶ እንዳደረግሁት የኢየሩሳሌምን ሕዝብ እንዲሁ አደርገዋለሁ። 7 እቈጣቸዋለሁ፤ ምንም እንኳ ለጊዜው ከእሳቱ ቢያመልጡ እሳቱ ግን ይበላቸዋል፤ እነርሱንም በምትቈጣበት ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ። 8 እነርሱ በእኔ መታመናቸውን ትተዋል፤ እኔም አገራቸው ምድረ በዳ እንድትሆን አደርጋለሁ፤ ይላል ልዑል እግዚአብሔር።” |