ሕዝቅኤል 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበሐሰተኞች ነቢያት ላይ የተነገረ ትንቢት 1 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! ከራሳቸው ሐሳብ አፍልቀው ትንቢት በሚናገሩ የእስራኤል ነቢያት ላይ ትንቢት ተናገር፤ ይልቅስ የእግዚአብሔርን ቃል እንዲሰሙ ንገራቸው።” 3 ልዑል እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፦ “ከአሳባቸው አፍልቀው ትንቢት ለሚናገሩና ራእይ ሳያዩ ‘ራእይ አይተናል’ ለሚሉ ለእነዚህ ለሞኞች ነቢያት ወዮላቸው! 4 የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ነቢዮቻችሁ በፍርስራሽ ቦታዎች መካከል እንደሚኖሩ ቀበሮዎች ናቸው። 5 በእግዚአብሔር ቀን ጦርነቱን ለመቋቋም ይቻል ዘንድ ወደ ፍርስራሹ አልወጣችሁም፤ ወይም የእስራኤልን ቅጥር አልጠገናችሁም። 6 ራእያቸው ሐሰት ነው፤ ሟርታቸውም ውሸት ነው፤ እግዚአብሔር ሳይልካቸው እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ይላሉ፤ ይህም ሆኖ ቃላቸው ተፈጻሚነት እንደሚኖረው ይገምታሉ። 7 እኔ ያልተናገርኩትን ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ ብላችሁ በምትናገሩበት ጊዜ ሐሰተኛ ራእይን ያያችሁና ሟርትን ያሟረታችሁ አይደለምን?” 8 ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላቸዋል፦ “ሐሰትን ስለ ተናገራችሁና ራእያችሁም ውሸት ስለ ሆነ እኔ በእናንተ ላይ እነሣለሁ። ይህንን የተናገርኩ እኔ ጌታ እግዚአብሔር ነኝ። 9 ሐሰተኛ ራእይ በሚያዩና ሟርትን በሚያሟርቱ ነቢያት ላይ እጄን አነሣለሁ፤ እነርሱ በሕዝቤ ማኅበር ውስጥ አይገኙም፤ እንዲያውም በእስራኤል ሕዝብ መዝገብ ውስጥ አይመዘገቡም፤ ወደ እስራኤል ምድርም አይገቡም፤ በዚያን ጊዜ እኔ ልዑል እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ። 10 “እነዚህ ነቢያት የማይታመኑ ሆኑ፤ ሰላም በሌለበት ሰላም አለ ብለው ለሕዝቤ ይናገራሉ፤ የዘመመ ግድግዳን ቀለም በመቀባት ያደሱ የሚመስላቸው ሠራተኞችን ይመስላሉ። 11 ዶፍ ዝናብ ይዘንባል ታላቅ የበረዶ ድንጋዮች ይወርዳሉ፤ ዐውሎ ነፋስም ይነሣል፤ ስለዚህ ግድግዳውን ቀለም ለቀቡ ሰዎች ግድግዳው ይወድቃል በላቸው። 12 ግድግዳው በሚፈርስበት ጊዜ የቀባችሁት ቀለም የት አለ ብለው ሰዎች አይጠይቁአችሁምን?” 13 ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የኢየሩሳሌምን ቅጽር ለማጥፋት በቊጣዬ ዐውሎ ነፋስ እንዲነሣ አደርጋለሁ። ዶፍ ዝናብና የበረዶ ናዳ ይወርዳል። 14 መሠረት ተጋልጦ ከምድር ወለል ጋር እስኪስተካከል ድረስ በቀለም የቀባችሁትን ግድግዳ አፍርሼ እጥለዋለሁ፤ ግድግዳው በሚወድቅበት ጊዜ እናንተም በውስጡ ትጠፋላችሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ። 15 “በቅጥሩ ላይና ቅጥሩን ቀለም በቀቡበት ላይ ኀይለኛ ቊጣዬን አወርዳለሁ፤ ከዚያም በኋላ ቅጥሩም ሆነ ቅጥሩን ቀለም የቀቡት አይኖሩም እላችኋለሁ። 16 እነርሱም ስለ ኢየሩሳሌም ትንቢት የተናገሩና ራእይ ያዩ ሰላም ሳይኖር ‘ሰላም አለ’ ያሉ የእስራኤል ነቢያት ናቸው፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ።” ሐሰተኞች በሆኑ ሴቶች ነቢያት ላይ የተነገረ ትንቢት 17 እግዚአብሔር እንዲህ አለ፦ “አሁንም የሰው ልጅ ሆይ! በሕዝብህ መካከል ከአሳባቸው አፍልቀው ትንቢት በሚናገሩት ሴቶች ላይ አተኲረህ ትንቢት ተናገርባቸው፤ 18 ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው፦ በጡንቻ ላይ የሚደረግ አሸን ክታብን ለሚሰፉ፥ የሰውንም ሕይወት ለማጥመድ በተለያየ ቁመት የራስ መሸፈኛ ሻሽ ለሚያዘጋጁ ሴቶች ወዮላቸው! ከእኔ ሕዝብ መካከል ሰዎችን አጥምዳችሁ እናንተ በሕይወት ትኖራላችሁን? 19 እፍኝ ገብስ እና ቊራሽ እንጀራ ለማግኘት ብላችሁ ሐሰትን ለሚያዳምጡ ለሕዝቤ ሐሰትን እየተናገራችሁ መሞት የማይገባቸውን ሰዎች በመግደልና መኖር የማይገባቸውን ሰዎች እንዲኖሩ በማድረግ ስሜ በሕዝቤ ዘንድ እንዲሰደብ አድርጋችኋል።” 20 ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሕዝቡን የምታጠምዱባቸውን አሸን ክታቦቻችሁን እጠላለሁ፤ አሸንክታባችሁን ከጡንቻዎቻችሁ ላይ በጣጥሼ በመጣል እንደ ወፎች የምታጠምዱአቸውን ነፍሳት ነጻ አወጣለሁ። 21 መሸፈኛ ሻሻችሁን ቀድጄ ሕዝቤን ከእጃችሁ አድናለሁ፤ ዳግመኛ በእናንተ እጅ አይወድቁም፤ እናንተም እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ። 22 “እኔ ተስፋ ያላስቈረጥኳቸውን ጻድቃንን ሐሰት በመናገር ተስፋ አስቈርጣችኋል፤ ክፉዎች ሕይወታቸውን ለማዳን ከኃጢአታቸው እንዳይመለሱ አደፋፍራችኋል። 23 ስለዚህ ከእንግዲህ ወዲያ ሐሰተኛ ራእይ አታዩም፤ የሟርተኝነትንም ሥራ አትሠሩም፤ ሕዝቤን ከእጃችሁ አድናለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።” |