ሕዝቅኤል 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየነቢዩ ሕዝቅኤል መሰደድ 1 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 2 “የሰው ልጅ ሆይ! አንተ የምትኖረው ዐመፀኞች በሆኑ ሕዝብ መካከል ነው፤ እነርሱ ዐመፀኞች ከመሆናቸው የተነሣ ዐይን እያላቸው አያዩም፤ ጆሮም እያላቸው አይሰሙም። 3 “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ! የስደት ዕቃህን ጠቅልለህ አዘጋጅ፤ እነርሱ እያዩም የስደት ጒዞህን በቀን ጀምር፤ እንደ ስደተኛ ከቦታህ ተነሥተህ ወደ ሌላ ቦታ ሂድ፤ ዐመፀኞች ቢሆኑም እንኳ ያስተውሉ ይሆናል። 4 እንደ ስደተኛ እነርሱ እያዩህ የጒዞ ዕቃህን በቀን ታዘጋጃለህ፤ ስደተኞች እንደሚያደርጉትም እነርሱ እያዩህ ወደ ማታ ጊዜ ወጥተህ ሂድ። 5 በሚመለከቱህም ጊዜ የቤትህን ግድግዳ ሸንቁረህ ቀዳዳ አብጅ፤ ዕቃህንም በዚያ ቀዳዳ አሾልከህ አውጣው፤ 6 የምትሄድበትን ስፍራ እንዳታይ ዕቃህን በትከሻህ ተሸክመህ ፊትህን በመሸፈን በጨለማ ስትሄድ ይመልከቱህ፤ እኔም ለእስራኤላውያን ምልክት አድርጌሃለሁ።” 7 እኔም እግዚአብሔር ያዘዘኝን ሁሉ አደረግሁ፤ በዚያኑ ቀን እንደ ስደተኛ ዕቃዬን ጠቀለልኩ፤ ቀኑም ሲመሽ ግድግዳውን በእጄ ነድዬ ቀዳዳ አበጀሁና በዚያ በኩል ዕቃዬን አወጣሁ፤ ሰዎቹም ሁሉ እያዩኝ የተጠቀለለውን ዕቃዬን በትከሻዬ ላይ አድርጌ በጨለማ ሄድኩ። 8 በማግስቱም ጠዋት እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ተናገረኝ፤ 9 “የሰው ልጅ ሆይ! እነዚያ ዐመፀኞች እስራኤላውያን ‘እነሆ ይህ የምታደርገው ነገር ሁሉ ምንድን ነው?’ ብለው አልጠየቁህምን? 10 ስለዚህ እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምለውን ንገራቸው፤ ይህ የትንቢት ቃል በኢየሩሳሌም ላይ ለሚያስተዳድረው መስፍንና እዚያም ለሚኖሩ ሕዝብ ሁሉ የተነገረ ነው። 11 ይህም አንተ ያደረግኸው ነገር ሁሉ በእነርሱ ላይ ሊፈጸም ለተቃረበው ነገር ምልክት መሆኑን አስታውቃቸው፤ እነርሱም ስደተኞችና ምርኮኞች ይሆናሉ ማለት ነው። 12 እነርሱን የሚያስተዳድረው መስፍን ዕቃውን ጠቅልሎ በትከሻው በመሸከም እነርሱ ግድግዳ ነድለው በሚያወጡለት ቀዳዳ ሾልኮ በጨለማ ይሰደዳል፤ ዐይኑንም ስለሚሸፍን ምድሪቱን አያይም። 13 ነገር ግን እኔ መረቤን ዘርግቼ አጠምደዋለሁ፤ በዐይኑ ሳያያት ወደሚሞትባት ወደ ባቢሎን ከተማ አመጣዋለሁ፤ 14 የቅርብ አማካሪዎቹንና የክብር ዘብ ጠባቂዎቹን ሁሉ በየአቅጣጫው እበትናቸዋለሁ፤ ከኋላቸውም ሆኜ በሰይፍ አሳድዳቸዋለሁ። 15 “በባዕዳን ሕዝቦችና አገሮች መካከል በምበትናቸው ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ፤ 16 ነገር ግን ከእነርሱ ጥቂቶቹን ከጦርነት፥ ከራብና ከቸነፈር እንዲተርፉ አደርጋለሁ፤ በዚህም ዐይነት በሕዝቦች መካከል ሲኖሩ ሥራቸው ምን ያኽል አጸያፊ እንደ ነበር ይገነዘባሉ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንኩ ያውቃሉ።” በፍርሃት የሚሸበረው ነቢይ ምልክት 17 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 18 “የሰው ልጅ ሆይ! በምትበላበት ጊዜ በፍርሃት ብላ፤ በምትጠጣበትም ጊዜ በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ጠጣ፤ 19 በምድሪቱ ለሚኖሩ ሕዝብ ጌታ እግዚአብሔር በእስራኤል ምድር በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ሕዝብ እንዲህ ይላል ብለህ ንገራቸው፦ ‘በምድሪቱ በሚኖሩ ሰዎች ዐመፅ ምክንያት ምድሪቱ በጠቅላላ ስለምትራቈት ምግባቸውን የሚበሉት በፍርሃት ነው፤ ውሃቸውንም የሚጠጡት ተስፋ በመቊረጥ ነው። 20 አሁን በሕዝብ ተሞልተው የሚታዩ ከተሞች ይጠፋሉ፤ አገሪቱም ምድረ በዳ ትሆናለች፤ በዚያን ጊዜ እነርሱ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ያውቃሉ።’ ” ተወዳጅ ምሳሌና የተጠላ የትንቢት ቃል 21 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 22 “የሰው ልጅ ሆይ! ራእዩ ሁሉ ተግባራዊ ሳይሆን ቀኖቹ ተራዘሙ ተብሎ ስለ እስራኤል ምድር የሚነገረው ይህ ምሳሌ ምንድን ነው? 23 እኔ ልዑል እግዚአብሔር ስለዚህ ጉዳይ የምለውን ንገራቸው፤ ይህ ምሳሌ እዚሁ ላይ እንዲያበቃ አደርገዋለሁ፤ ዳግመኛም በእስራኤል አይነገርም፤ በዚህ ፈንታ ‘እነሆ ጊዜው ደርሶአል፤ የትንቢቱም ቃል ሁሉ ሊፈጸም ነው!’ ብለህ ንገራቸው። 24 “በእስራኤል ሕዝብ መካከል ሐሰተኛ ራእይ ወይም ሟርት ከእንግዲህ ወዲህ ከቶ አይነገርም። 25 እኔ እግዚአብሔር በቀጥታ እናገራለሁ፤ የምናገረውም ቃል ሁሉ ይፈጸማል፤ ከእንግዲህ ወዲህም ከቶ አይዘገይም፤ እናንተ ዐመፀኞች ‘በእናንተ ላይ አመጣለሁ’ ብዬ በማስጠንቀቅ የተናገርኩትን ሁሉ በሕይወታችሁ ዘመን እንዲፈጸም አደርጋለሁ፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ።” 26 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 27 “የሰው ልጅ ሆይ! እስራኤላውያን የአንተ ራእይና ትንቢት ‘ከብዙ ዘመን በኋላ የሚፈጸም ነው’ ብለው ይናገራሉ፤ 28 ስለዚህ እኔ እግዚአብሔር የምላቸውን ንገራቸው፤ እኔ የተናገርኩት ሁሉ ይፈጸማል፤ ከቶም አይዘገይም፤ ይህን የተናገርኩ እኔ ልዑል እግዚአብሔር ነኝ።” |