ሕዝቅኤል 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበኢየሩሳሌም ላይ የተላለፈ ፍርድ 1 የእግዚአብሔር መንፈስ ከምድር ወደ ላይ አንሥቶ በምሥራቅ ትይዩ ወደ ሆነው በእግዚአብሔር ቤት ወደ አለው ወደ ምሥራቁ በር አመጣኝ፤ እዚያም በቅጽር በሩ አጠገብ ኻያ አምስት ሰዎችን አየሁ፤ በእነርሱም መካከል የሕዝብ መሪዎች የሆኑት የዐዙር ልጅ አዛንያና የበናያ ልጅ ፈላጥያ ይገኙባቸዋል። 2 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ “የሰው ልጅ ሆይ! እነዚህ ሰዎች መጥፎ ዕቅድ ያወጣሉ፤ በዚህችም ከተማ ክፉ ምክር ይመክራሉ፤ 3 ‘እንደገና መልሰን ቤቶችን የምንሠራበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፤ ከተማይቱ እንደ ሥጋ መቀቀያ ሰታቴ ስትሆን፥ እኛ ደግሞ በውስጥዋ እንደ ሥጋ ሆነናል’ ብለዋል። 4 ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፥ በእነርሱ ላይ ትንቢት ተናገርባቸው፤ ትንቢት ተናገር።” 5 ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ወረደ፤ እንዲህም አለኝ፦ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ብለህ ተናገር፦ የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! ይህን ነገር ተናግራችኋል፤ እኔም በሐሳባችሁ ያለውን ነገር ዐውቃለሁ። 6 በዚህች ከተማ ብዙ ሰው ገድላችኋል፤ መንገዶችዋንም በሬሳ ሞላችኋቸው። 7 “ስለዚህ እኔ ልዑል እግዚአብሔር የምላችሁ ይህ ነው፦ ‘በሰታቴው ውስጥ ያለው ሥጋ እናንተ የገደላችኋቸው ሰዎች ናቸው፤ ይህችም ከተማ ሰታቴዋ ነች፤ እናንተ ግን ከከተማይቱ ትወገዳላችሁ። 8 እናንተ ጦርነትን ፈርታችኋል፤ እኔ ግን ጦርነትን አመጣባችኋለሁ እኔ ጌታ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ። 9 እናንተን ከከተማይቱ አስወጥቼ ለባዕዳን ሕዝቦች አሳልፌ በመስጠት እፈርድባችኋለሁ። 10 ስለዚህም በገዛ አገራችሁ ድንበር ላይ በጦርነት ትገደላላችሁ፤ በእስራኤል ድንበር ላይ እፈርድባችኋለሁ፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ። 11 ይህች ከተማ ለእናንተ ሰታቴ አትሆንላችሁም፤ እናንተም በውስጥዋ እንደ ሥጋ አትሆኑም፤ በእስራኤል ድንበር ላይ እፈርድባችኋለሁ። 12 የእኔን ሕግና ሥርዓት በመሻር በጐረቤት ያሉ ሕዝቦችን ሥርዓት በመፈጸማችሁ የፈረድኩባችሁ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን ታውቃላችሁ።’ ” 13 እኔም ትንቢት በምናገርበት ጊዜ የበናያ ልጅ ፈላጥያ ወድቆ ሞተ፤ እኔም በግንባሬ ወደ መሬት ተደፍቼ በመጮኽ “ልዑል እግዚአብሔር ሆይ! በእስራኤል የተረፉትን ሁሉ ልትፈጅ ነውን?” አልኩ። እግዚአብሔር ለስደተኞች የሰጠው ተስፋ 14 እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፦ 15 “የሰው ልጅ ሆይ! የኢየሩሳሌም ኗሪዎች ስለ ሥጋ ዘመዶችህ፥ ስለ ተሰደዱት ወገኖችህ፥ በአጠቃላይ ስለ መላው የእስራኤል ሕዝብ በመነጋገር ላይ ናቸው፤ ‘እነርሱ ከእግዚአብሔር ርቀው ስለ ሄዱ እግዚአብሔር ምድሪቱን ለእኛ ርስት አድርጎ ሰጥቶናል’ ይላሉ”። 16 ስለዚህ ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “ሩቅ አገር በሚኖሩ ሕዝቦች መካከል እንዲኖሩ ባደርጋቸውና በተለያዩ አገሮች ብበትናቸውም እንኳ ለጥቂት ጊዜ ግን መገናኛቸው ቤተ መቅደስ እሆንላቸዋለሁ። 17 “ስለዚህ እኔ እግዚአብሔር የምለውን ሁሉ ንገራቸው፤ እነሆ፥ ከሕዝቦች መካከልና ከተበታተናችሁባቸው አገሮች እሰበስባችኋለሁ፤ የእስራኤልንም ምድር እንደገና እሰጣችኋለሁ። 18 በሚመለሱበት ጊዜ የሚያገኙአቸውን አጸያፊና ርኩስ የሆኑ ጣዖቶችን ወዲያ ያስወግዳሉ። 19 አንድ ልብ እሰጣቸዋለሁ አዲስ መንፈስንም በውስጣቸው አኖራለሁ፤ ከሰውነታቸው እንደ ድንጋይ የጠጠረ ልብን አውጥቼ እንደ ሥጋ የለሰለሰ ልብን እሰጣቸዋለሁ። 20 በዚያን ጊዜ ሕጌን ይፈጽማሉ፤ ሥርዓቴንም ሁሉ ያከብራሉ፤ እነርሱ ሕዝቤ ይሆናሉ፤ እኔም አምላካቸው እሆናለሁ። 21 ልባቸው ርኩስና አጸያፊ የሆኑ ጣዖቶችን የሚከተሉትን ግን እንደ ሥራቸው እከፍላቸዋለሁ፤” ይህን የተናገረ ልዑል እግዚአብሔር ነው። የእግዚአብሔር ክብር ከኢየሩሳሌም መለየት 22 በዚህ ጊዜ ኪሩቤል ክንፎቻቸውን ዘርግተው መብረር ጀመሩ፤ መንኰራኲሮቹም ከጐናቸው ነበሩ፤ የእስራኤል አምላክ አንጸባራቂ ክብር ከበላያቸው ነበር፤ 23 የእግዚአብሔርም አንጸባራቂ ክብር ከከተማይቱ ውስጥ ተነሥቶ ከከተማይቱ በስተ ምሥራቅ ወዳለው ተራራ ላይ ቆመ። 24 በራእይም የእግዚአብሔር መንፈስ ከምድር ወደ ላይ አንሥቶ በባቢሎን ወዳሉት ስደተኞች አመጣኝ፤ ከዚህ በኋላ ራእዩ ከእኔ ተለየ። 25 እኔም እግዚአብሔር ያሳየኝን ሁሉ ለስደተኞቹ ነገርኳቸው። |