ሕዝቅኤል 10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእግዚአብሔር ክብር ከቤተ መቅደሱ መራቁ 1 ከኪሩቤል ራሶች በላይ ያለውን ጠፈር ተመለከትኩ፤ በኪሩቤል ላይ ከሰንፔር ዕንቊ የተሠራ ዙፋን የሚመስል ነገር አየሁ። 2 እግዚአብሔርም ቀጭን ሐር የለበሰውን ሰው “ከሕያዋን ፍጥረቶች በታች ባሉት መንኰራኲሮች መካከል አልፈህ ሂድ፤ ከከሰልም ፍም በእጅህ አፍሰህ ውሰድና በከተማይቱ ላይ በትነው!” አለው። እኔም እያየሁት ገባ፤ 3 ወደ ውስጥ በሚገባበትም ጊዜ ኪሩቤል ከቤተ መቅደሱ በስተ ደቡብ በኩል ቆመው ነበር፤ በውስጥ በኩል ያለውንም አደባባይ ደመና ሞላው፤ 4 የእግዚአብሔር ክብር ከኪሩብ ተነሥቶ ወደ ቤተ መቅደሱ መድረክ ሄደ፤ ደመና ቤቱን ሞላው፤ አደባባዩም በእግዚአብሔር ክብር ነጸብራቅ ተሞላ። 5 ኪሩቤል በክንፎቻቸው የሚያሰሙት ድምፅ በውጪ በኩል ባለው አደባባይ እንኳ ይሰማ ነበር፤ ድምፁም ሁሉን የሚችል አምላክ ድምፅ ይመስል ነበር። 6 እግዚአብሔር ያንን በፍታ የለበሰውን ሰው ከኪሩቤል ሥር ከነበሩት መንኰራኲሮች መካከል እሳት እንዲወስድ ባዘዘው ጊዜ ወዲያውኑ ወደ ውስጥ ገብቶ ከመንኰራኲሮቹ በአንደኛው አጠገብ ቆመ፤ 7 ከኪሩቤልም አንዱ በመካከላቸው ባለው እሳት ውስጥ እጁን ሰድዶ ጥቂት ፍሞች አነሣና በፍታ በለበሰው ሰው እጅ ላይ አኖረው፤ ሰውየውም ፍሙን ይዞ ሄደ። 8 እኔም እያንዳንዱ ኪሩብ የሰው እጅ የሚመስል እጅ በየክንፎቹ ሥር ያለው መሆኑን ተመለከትኩ፤ 9 ስመለከት እያንዳንዱ መንኰራኲር በያንዳንዱ ኪሩብ አጠገብ ሆኖ አራት መንኰራኲሮችን አየሁ፤ የመንኰራኲሮቹም መልክ የሚያንጸባርቅ ዕንቊ ይመስል ነበር። 10 የአራቱ መንኰራኲሮች መልክ ተመሳሳይ ነበር፤ እነርሱም በመንኰራኲር ውስጥ የሚተላለፉ መንኰራኲሮች ይመስሉ ነበር። 11 ወደ ፊታቸው በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ ወደ የትኛውም አቅጣጫ ሳይዞሩ በቀጥታ ይሄዳሉ፤ የፊቱ መንኰራኲር ወደ የትኛውም አቅጣጫ ቢሄድ ሌሎቹ ሳይዞሩ በቀጥታ ይከተላሉ። 12 መላ አካላቸውም ሆነ ጀርባቸው፥ እጆቻቸውም ሆኑ ክንፎቻቸው መንኰራኲሮቹ እንኳ ሳይቀሩ ሁሉም ብዙ ዐይኖች ነበሩአቸው፤ 13 መንኰራኵሮቹም እኔ እየሰማሁ የሚሽከረከሩ መንኰራኩሮች ተብለው ተጠሩ። 14 እያንዳንዱ ኪሩብ አራት ፊቶች ነበሩት፤ የመጀመሪያው የበሬ ፊት፥ ሁለተኛው የሰው፥ ሦስተኛው የአንበሳ፥ አራተኛው ደግሞ የንስር ፊት ይመስል ነበር። 15 ኪሩቤል ወደ ላይ ተነሡ እነርሱም በኬባር ወንዝ አጠገብ ያየኋቸው ሕያዋን ፍጥረቶች ናቸው። 16 ኪሩቤሉ ሲንቀሳቀሱ ከጐናቸው ያሉት መንኰራኲሮችም አብረው ይንቀሳቀሳሉ፤ ኪሩቤሉ ለመነሣት ክንፋቸውን ሲዘረጉ ከጐናቸው ያሉት መንኰራኲሮችም ወደ ሌላ አይዞሩም። 17 የሕያዋን ፍጥረቶች መንፈስ በመንኰራኲሮቹ ውስጥ ስላለ ፍጥረቶቹ ሲቆሙ መንኰራኲሮቹም አብረው ይቆማሉ፤ ኪሩቤሉ ሲነሡ መንኰራኲሮቹም ወደ ሌላ አይዞሩም። 18 ከዚህ በኋላ የእግዚአብሔር ክብር ከቤተ መቅደሱ መድረክ ተነሥቶ ከኪሩቤል በላይ ወዳለው ስፍራ ወጥቶ ቆመ። 19 እኔም ይህን በመመልከት ላይ ሳለሁ፥ ኪሩቤል ክንፎቻቸውን ዘርግተው ከመሬት ወደ ላይ በሚወጡበት ጊዜ ከጐናቸው የነበሩትም መንኰራኲሮቹ አብረዋቸው ሲወጡ አየሁ፤ በቤተ መቅደሱ በስተ ምሥራቅ ባለው የቅጽር በር ሲደርሱ ቆሙ፤ የእስራኤል አምላክም ክብር በእነርሱ ላይ ነበር። 20 እነዚህም በኬባር ወንዝ አጠገብ ከእስራኤል አምላክ ሥር ያየኋቸው ሕያዋን ፍጥረቶች ናቸው፤ እኔም ኪሩቤል መሆናቸውን ዐወቅሁ። 21 እያንዳንዳቸውም አራት ፊቶችና አራት ክንፎች ነበሩአቸው፤ በእያንዳንዱም ክንፍ ሥር የሰው እጅ የመሰለ ነገር ነበረ። 22 ፊቶቻቸውም እነዚያኑ በኬባር ወንዝ አጠገብ ያየኋቸውን ፊቶች ይመስሉ ነበር፤ እያንዳንዱም ኪሩብ በቀጥታ ወደ ፊት ይሄድ ነበር። |