Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ሕዝቅኤል 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ሕዝቅኤል ለመጀመሪያ ጊዜ ያየው ራእይ ( 1፥1—7፥27 ) የእግዚአብሔር ዙፋን

1 በሠላሳኛው ዓመት፥ በአራተኛው ወር፥ ከወሩም በአምስተኛው ቀን በኬባር ወንዝ አጠገብ በአይሁድ ምርኮኞች መካከል ሳለሁ ሰማያት ተከፍተው የእግዚአብሔርን ራእይ አየሁ።

2 ይህም በሆነ ጊዜ ንጉሡ ኢኮንያን ከተማረከ አምስት ዓመት ከአምስት ቀን ሆኖት ነበር፤

3 በከለዳውያን ምድር በኬባር ወንዝ አጠገብ የእግዚአብሔር ቃል የቡዚ ልጅ ወደ ሆንኩት ወደ ካህኑ ወደ እኔ ወደ ሕዝቅኤል መጣ፤ የእግዚአብሔርም ኀይል በእኔ ላይ ነበረ።

4 ቀና ብዬ ስመለከት ብርቱ ዐውሎ ነፋስ ከሰሜን በኩል ሲመጣ አየሁ፤ ከግዙፍ ደመና የመብረቅ ብልጭታ ይታይ ነበር፤ በዙሪያው ያለውም ሰማይ ቀላ፤ መብረቁ በሚበርቅበትም ስፍራ አንዳች ነገር እንደ ነሐስ አበራ።

5 በዐውሎ ነፋሱም መካከል የሰው መልክ ያላቸው አራት ሕያዋን ፍጥረቶች አየሁ፤

6 እያንዳንዱም ፍጥረት አራት አራት ፊትና አራት አራት ክንፍ ነበሩት።

7 እግራቸው ቀጥ ያለ ሲሆን፥ ውስጥ እግራቸው እንደ ኰርማ ሰኮና ነበር፤ መልካቸውም እንደ ተወለወለ ነሐስ ያበራ ነበር፤

8 ከአራቱ ፊቶቻቸውና ከአራቱ ክንፎቻቸው ሌላ እያንዳንዳቸው ከክንፎቻቸው ግርጌ አራት የሰው ዐይነት እጆች ነበሩአቸው።

9 የእያንዳንዱ ፍጥረት ሁለት ክንፎች ግራና ቀኝ ተዘርግተው ጫፎቻቸው ይነካካሉ፤ ስለዚህ ሰውነታቸው ወዲያና ወዲህ ሳይል በኅብረት ይንቀሳቀሱ ነበር።

10 እያንዳንዱ ፍጥረት አራት የተለያዩ ፊቶች ነበሩት፤ ይኸውም ከፊት ለፊት የሰው መልክ የሚመስል፥ በስተቀኝ በኩል የአንበሳ መልክ፥ በስተግራ የበሬ ፊት፥ በስተ ኋላም የንስር መልክ የሚመስል ነበሩት።

11 የእያንዳንዱ እንስሳ ሁለት ክንፎች ወደ ላይ ከፍ ብለው ከእነርሱ ቀጥሎ ያለውን ፍጥረት የክንፎች ጫፍ ይነኩ ነበር፤ የቀሩት ሁለቱ ክንፎቻቸው ግን ተጣጥፈው አካላቸውን ይሸፍኑ ነበር።

12 እያንዳንዱ ፍጥረት በአራት አቅጣጫ ለመመልከት ይችል ስለ ነበር ሁሉም በአንድነት ወዲያና ወዲህ ሳይሉ መንፈስ ወደሚሄድበት አቅጣጫ ሁሉ ይበሩ ነበር።

13 በሕያዋን ፍጥረቶቹ መካከል እንደሚነድ ከሰል እሳት የሚመስል ነገር ነበር፤ እርሱም በፍጥረቶቹ መካከል ወዲያና ወዲህ የሚንቀሳቀስ ችቦ ይመስል ነበር፤ እሳቱ ብሩህ ነበር፤ መብረቅም ከዚያ ይወጣ ነበር።

14 ፍጥረቶቹም እንደ መብረቅ ብልጭታ ወዲያና ወዲህ ተፈናጠሩ።

15 አራቱን ፍጥረቶች በመመልከት ላይ ሳለሁ፥ አራት መንኰራኲሮች ወደ መሬት ተሽከርክረው ሲወርዱና በሕያዋን ፍጥረቶቹ አጠገብ ጐን ለጐን በተርታ ሲቀመጡ አየሁ፤

16 አራቱም መንኰራኲሮች ተመሳሳይ ነበሩ፤ እያንዳንዱም እንደ ከበረ ዕንቊ ያንጸባርቅ ነበር፤ እንዲሁም እያንዳንዱ አንዱ መንኰራኲር በሌላው መንኰራኲር ውስጥ የሚተላለፍ ይመስል ነበር።

17 እነርሱም ከአራቱ አቅጣጫዎች ወደፈለጉት አቅጣጫ ወደ ሌላ ሳይዞሩ ቀጥ ብለው ይሄዳሉ።

18 የመንኰራኲሮቹም ጠርዝ ግዙፍና የሚያስፈራ ነበር፤ አራቱም የመንኰራኲር ጠርዝ ዙሪያቸውን በዐይን የተሞሉ ነበሩ።

19 ፍጥረቶቹ በተንቀሳቀሱ ቊጥር መንኰራኲሮቹ አብረዋቸው ይንቀሳቀሱ ነበር፤ ፍጥረቶቹ ከምድር ተነሥተው ከፍ በሚሉበትም ጊዜ መንኰራኲሮቹ አብረው ከፍ ይሉ ነበር።

20 ፍጥረቶቹ መንፈስ ወደሚሄድበት አቅጣጫ ሁሉ በሚበርሩበት ጊዜ፥ መንኰራኲሮቹም አብረው ይበሩ ነበር፤ ይህም የሆነው የፍጥረቶቹ መንፈስ በመንኰራኲሮቹም ውስጥ ስለ ነበረ ነው።

21 የፍጥረቶቹ መንፈስ በመንኰራኲሮቹም ውስጥ በመኖሩ ፍጥረቶቹ በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ አብረው ይንቀሳቀሳሉ፤ ሲቆሙም አብረው ይቆማሉ፤ ከመሬት ወደ አየር በሚመጥቁበትም ጊዜ፥ አብረው ይመጥቃሉ።

22 ከሕያዋን ከፍጥረቶቹ ራስ በላይ እንደ መስተዋት ከሚያብረቀርቅ የከበረ ድንጋይ የተሠራ ጠፈር የሚመስል ወለል ነበር።

23 ከወለሉም ሥር እያንዳንዱ እንስሳ ከጐኑ ባለው ፍጥረት አንጻር ሁለት ክንፎቹን ዘርግቶ፥ በቀሩትም ሁለት ክንፎቹ ሰውነቱን ሸፍኖ ቆሞ ነበር።

24-25 በሚበርሩበትም ጊዜ ክንፎቻቸው ሲጋጩ ሰማሁ፤ ድምፁም የባሕር ማዕበል ጩኸትና የታላቅ ሠራዊት ሁካታ፥ እንዲሁም የሁሉን ቻዩን የእግዚአብሔርን ድምፅ ይመስል ነበር፤ መብረራቸውን ባቆሙ ጊዜ ክንፎቻቸውን ያጥፉ ነበር፤ በዚያን ጊዜ ከራሳቸው በላይ ካለው ጠፈር ድምፅ ተሰማ።

26 ከጠፈሩም በላይ ሰንፔር ተብሎ ከሚጠራ ዕንቊ የተሠራ ዙፋን የሚመስል ነገር ተዘርግቶ ነበር፤ ሰው የሚመስልም በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ ነበር።

27 ወገቡ ከሚመስለው ክፍል በላይ እሳት ውስጥ ገብቶ የጋለ ብረት የሚመስል ነገር ከወገቡም በታች እሳት የሚመስል ነገር አየሁ፤ የሚያንጸባርቅ ብርሃንም ዙሪያውን ገብቶበታል።

28 በዙሪያው ያለው ነጸብራቅ፥ በዝናብ ጊዜ በደመና ውስጥ እንደሚታየው ቀስተ ደመና ነበር፤ ይህም የእግዚአብሔር ክብር መገለጥን ይመስላል፤ ባየሁትም ጊዜ በግንባሬ ተደፋሁ፤ ከዚያም የንግግር ድምፅ ሰማሁ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告