Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 40 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የድንኳኑ መተከልና የአገልግሎት መጀመር

1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦

2 “የመጀመሪያው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን የመገናኛውን ድንኳን ትከል።

3 ዐሥሩ ትእዛዞች የተጻፉበትን ጽላት የያዘውን የቃል ኪዳኑን ታቦት በውስጡ አኑር፤ ለመከለያ የተሠራውንም መጋረጃ ከፊት ለፊቱ አድርግ።

4 ጠረጴዛውንም ወደ ውስጥ አስገብተህ የመገልገያ ዕቃዎችን በእርሱ ላይ አኑር፤ መቅረዙንም አስገብተህ መብራቶቹን በእርሱ ላይ አኑር፤

5 ዕጣን የሚቃጠልበትን የወርቅ መሠዊያ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት አቁመው፤ በድንኳኑም መግቢያ ደጃፍ መጋረጃውን ስቀል።

6 የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ በድንኳኑ መግቢያ ፊት አኑር።

7 የመታጠቢያውን ሣሕን በድንኳኑና በመሠዊያው መካከል አስቀምጠህ ውሃ ሙላበት።

8 አደባባዩን በዙሪያው ትከል፤ መጋረጃውንም በድንኳኑ መግቢያ ደጃፍ ላይ ስቀለው።

9 “ከዚያም በኋላ ድንኳኑን ከመገልገያ ዕቃዎቹ ጋር የቅባቱን ዘይት በመቀባት ለእግዚአብሔር የተለየ አድርገው፤ የተቀደሰም ይሆናል።

10 ቀጥሎም መሠዊያውን ከመገልገያ ዕቃዎቹ ጋር በመቀባት ለእግዚአብሔር የተለየ አድርገው፤ ፈጽሞም የተቀደሰ ይሆናል።

11 የመታጠቢያውንም ሳሕን ከነማስቀመጫው በዚሁ ዐይነት ቀብተህ ለእግዚአብሔር የተለየ አድርግ።

12 “አሮንንና ልጆቹን ወደ ድንኳን ደጃፍ አምጥተህ እንዲታጠቡ አድርጋቸው፤ እጠባቸው፤

13 የተቀደሱትን ልብሶች አልብሰህ በመቀባት አሮንን ለእኔ የተለየ ካህን ሆኖ እንዲያገለግለኝ አድርገው።

14 ልጆቹንም አምጥተህ ቀሚስ አልብሳቸው።

15 እነርሱም ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ ልክ አባታቸውን በቀባኸው ዐይነት ቀባቸው፤ በመቀባታቸውም ምክንያት በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ካህናት ሆነው ያገለግሉኛል።”

16 ሙሴም ልክ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ሁሉን ነገር አደረገ።

17 ስለዚህ ከግብጽ በወጡ በሁለተኛው ዓመት፥ የመጀመሪያው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን የመገናኛው ድንኳን ተተከለ።

18 ሙሴ ድንኳኑን ተከለ፤ የድንኳኑን እግሮች አኖረ፤ ተራዳዎቹንና ምሰሶዎቹን አቆመ፤ መወርወሪያዎቹንም አያያዘ።

19 እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ክዳኑን በድንኳኑ ላይ ዘረጋ፤ የውጪውንም ክዳን በላዩ አደረገ፤

20 ሁለቱንም የድንጋይ ጽላቶች ወስዶ በቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ አስቀመጣቸው፤ መሎጊያዎችንም በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ አስገባ፤ የስርየት መክደኛውንም በታቦቱ ላይ አኖረ፤

21 ታቦቱንም ወደ ድንኳኑ ውስጥ አስገባውና የሚከለልበትን መጋረጃ ሰቀለ፤ በዚህም ዐይነት ልክ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ታቦቱን ሸፈነው።

22 ጠረጴዛውን ወደ ድንኳኑ ውስጥ አስገብቶ ከመጋረጃው ውጪ በስተ ሰሜን በኩል አስቀመጠው።

23 እግዚአብሔርም ባዘዘው መሠረት ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን የተቀደሰ ኅብስት በገበታው ላይ አሰናዳ።

24 መቅረዙንም ወደ ድንኳኑ አስገብቶ ከገበታው ፊት ለፊት በድንኳኑ በደቡብ በኩል አስቀመጠው።

25 እንዲሁም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በዚያ በእግዚአብሔር ፊት መብራቶቹን አበራ።

26 የወርቁንም መሠዊያ ወደ ድንኳኑ አስገብቶ ከመጋረጃው ፊት ለፊት አኖረው።

27 እግዚአብሔርም ባዘዘው መሠረት ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን በላዩ ላይ አጠነ።

28 መጋረጃውንም በድንኳኑ መግቢያ ደጃፍ ላይ ሰቀለ።

29 እዚያም በድንኳኑ መግቢያ ፊት ለፊት የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ አኖረ፤ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን ቊርባን እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በእርሱ ላይ አቀረበ፤

30 የመታጠቢያውንም ሳሕን በድንኳኑና በመሠዊያው መካከል አስቀምጦ ውሃ ሞላበት።

31 ሙሴ፥ አሮንና ልጆቹ እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን በዚያ ታጠቡ፤

32 ወደ ድንኳኑ በሚገቡበትና ወደ መሠዊያው በሚቀርቡበት ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ይህን ማድረግ ነበረባቸው።

33 ሙሴ በድንኳኑና በመሠዊያው ዙሪያ የሚሆነውን ድንኳኑ ሠራ፤ ወደ ድንኳኑ በሚያስገባው ደጃፍ መጋረጃ ሰቀለ፤ በዚህም ዐይነት ሥራውን ሁሉ ፈጸመ።


የእግዚአብሔር ክብር
( ዘኍ. 9፥15-23 )

34 ከዚህ በኋላ ድንኳኑ በደመና ተሸፈነ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ድንኳኑን ሞላው።

35 ደመናው ስለረበበበትና የእግዚአብሔርም ክብር ድንኳኑን ስለ ሞላው ሙሴ ወደ ድንኳኑ ለመግባት አልቻለም።

36 በጉዞአቸው ሁሉ እስራኤላውያን የሰፈሩበትን ቦታ ለቀው የሚንቀሳቀሱት ደመናው ከድንኳኑ ላይ በሚነሣበት ጊዜ ብቻ ነበር፤

37 ደመናው እዚያው እስካለ ድረስ ሰፈራቸውን ለቀው አይሄዱም ነበር።

38 በሚጓዙበት ጊዜ ሁሉ በቀን የእግዚአብሔርን ክብር የሚገልጠው ደመና ድንኳኑን ሲሸፍን፥ በሌሊት ደግሞ በደመናው ውስጥ እሳት ያዩ ነበር።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告