Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 39 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የካህናት ልብስ አሠራር
( ዘፀ. 28፥1-14 )

1 ካህናቱ በተቀደሰው ስፍራ ሲያገለግሉ የሚለብሱአቸውን እጅግ የተዋቡትን የካህናት ልብሶች ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ ሠሩ፤ የአሮንንም የክህነት ልብሶች እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ሠሩ።

2 ኤፉዱንም ከወርቅ ክር፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና፥ ከቀይ ከፈይ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ሠሩ፤

3 ወርቁንም ቀጥቅጠው ስስ በማድረግ እንደ ክር አድርገው ቈራረጡት፤ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ ከተፈተለም ጥሩ በፍታ ጋር በጥበብ አሠራር ጠለፉት።

4 ለኤፉዱም ማንገቻ በትከሻ ላይ የሚወርዱ ሁለት ጥብጣቦች ሠርተው ኤፉዱ እንዲጠብቅ በጐንና በጐኑ አያያዙአቸው።

5 እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ከወርቅ ክር፥ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና፥ ከቀይ ከፈይ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ በብልኀት የተጠለፈው ቀበቶ አንድ ወጥ በመሆን ከኤፉዱ ጋር ተያይዞ ተሠራ።

6 የመረግድ ድንጋዮችንም አዘጋጅተው በወርቅ ፈርጥ ላይ አስቀመጡአቸው፤ በእነርሱም ላይ የዐሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች ስሞች እንደ ቀለበት ማኅተም ተቀርጸውባቸው ነበር፤

7 እነርሱም እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ዐሥራ ሁለቱን የእስራኤል ነገድ በመወከል እንዲታሰቡ በትከሻ ላይ በሚወርዱት በኤፉዱ ጥብጣቦች ላይ አኖሩአቸው።


የደረት ኪስ አሠራር
( ዘፀ. 28፥15-30 )

8 የደረቱንም ኪስ ኤፉዱ ከተሠራባቸው ተመሳሳይ ነገሮች በተመሳሳይ የጥበብ ጥልፍ ሠሩት፤

9 እርሱም በሁለት የታጠፈ አራት ማእዘን ሆኖ ርዝመቱ ኻያ ሁለት ሳንቲ ሜትር፥ የጐኑም ስፋት ኻያ ሁለት ሳንቲ ሜትር ነበር፤

10 የከበሩ ድንጋዮችንም በአራት ረድፍ አደረጉበት፤ በመጀመሪያው ረድፍ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮንና የሚያብረቀርቅ ዕንቊ፤

11 በሁለተኛውም ረድፍ በሉር፥ ሰንፔርና ዐልማዝ፥

12 በሦስተኛው ረድፍ ያክንት፥ ኬልቄዶንና አሜቴስጢኖስ፥

13 በአራተኛው ረድፍ ቢረሌ፥ መረግድና ኢያስጲድ፤ እነዚህ ሁሉ በወርቅ ፈርጥ ላይ የተቀመጡ ነበሩ።

14 የከበሩት ድንጋዮች ዐሥራ ሁለቱን የእስራኤል ነገድ በመወከል እንዲታሰቡ በእያንዳንዱ ድንጋይ ላይ ከዐሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች ስሞች አንዱ ስም ተቀርጾበታል።

15 ለደረቱ ኪስም እንደ ገመድ የተጐነጐኑትን ድሪዎች ከጥሩ ወርቅ ሠሩ።

16 ሁለት የወርቅ ፈርጦችና ሁለት የወርቅ ቀለበቶችም ሠርተው፥ ሁለቱን ቀለበቶች በደረት ኪሱ በላይ በኩል ካሉት ማእዘኖች ጋር አያያዙአቸው።

17 ሁለቱንም የወርቅ ድሪዎች ከቀለበቶቹ ጋር እንዲያያዙ አደረጉ፤

18 ሌሎቹንም የሁለቱን ድሪዎች ጫፎች ከሁለቱ ፈርጦች ጋር እንዲገናኙ አደረጉ፤ በዚህም ዐይነት በትከሻ ላይ በሚወርዱት በኤፉድ ማንገቻ ጥብጣቦች ፊት ለፊት እንዲያያዙ አደረጉ።

19 በተጨማሪም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠርተው በኤፉዱ ፊት ለፊት ባለው የደረት ኪስ ሁለት የውስጥ ጫፎች ላይ አደረጉአቸው።

20 ቀጥሎም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠርተው በትከሻ ላይ በፊት በኩል ከሚወርዱት ከሁለቱ የኤፉዱ ጥብጣቦች ጋር ከታች በኩል አያያዙአቸው፤ እነርሱም የተያያዙት በብልኀት ከተጠለፈው ቀበቶ በላይ ከመጋጠሚያው አጠገብ ነበር።

21 እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት በደረት ኪሱ ላይ ያሉትን ቀለበቶች ከኤፉዱ ቀለበቶች ጋር በሰማያዊ ክር አሠሩ፤ በዚህ ዐይነት የደረት ኪሱ ከቀበቶው በላይ ስለሚውል በቀላሉ የማይፈታ ጥብቅ ነበር።


የቀሩት የካህናት ልብሶች አሠራር
( ዘፀ. 28፥31-43 )

22 የኤፉዱ መደረቢያ ቀሚስ የተሠራው ሙሉ በሙሉ ከሰማያዊ ከፈይ ነበር፤

23 የቀሚሱም ማጥለቂያ አንገትጌ እንዳይተረተር ታጥፎ ዙሪያውን የተዘመዘመ ነበር፤

24 በልብሱ ግርጌ ከሰማያዊ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ ከጥሩ በፍታ የተጠለፈ የሮማን ፍሬን የመሰለ ጥልፍ ሠሩ።

25 ከጥሩ ወርቅም መርገፎችን ሠሩ፤ መርገፎችም በልብሱ ግርጌ ዙሪያ ባለው እንደ ሮማን ፍሬ በሚመስለው ጥልፍ መካከል አስቀመጡአቸው።

26 እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት መርገፎቹ የሮማን ፍሬ፥ በልብሱ ግርጌ ዙሪያ አከታትለው አደረጉ።

27 ለአሮንና ለልጆቹ የሚከተሉትን ልብሶች አዘጋጁ፤ ሸማኔ ከሠራው ከጥሩ በፍታ ሸሚዞችን፥

28 የራስ መጠምጠሚያዎችን፥ ቆቦችንና ሱሪዎችን፥

29 መታጠቂያውንም ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ ከተፈተለ ጥሩ በፍታ ሠርተው እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት በጥልፍ ጥበብ አስጌጡት።

30 የተቀደሰውንም የአክሊል ምልክት ከንጹሕ ወርቅ ሠርተው “ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለየ” የሚል ቃል እንደ ማኅተም ቀረጹበት።

31 እርሱንም እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ከመጠምጠሚያው ፊት በሰማያዊ ክር አሰሩት።


የሥራው ሁሉ ፍጻሜ
( ዘፀ. 35፥10-19 )

32 በመጨረሻም የመገናኛው ድንኳን አሠራር በሙሉ ተፈጸመ፤ እስራኤላውያን ሁሉን ነገር እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት አደረጉ፤

33 ከዚህ በኋላ የሚከተሉትን ዕቃዎች ሁሉ ወደ ሙሴ አመጡአቸው፤ ድንኳኑንና የመገልገያ ዕቃዎቹን ሁሉ እነርሱም፦ ኩላቦቹ፥ ተራዳዎቹ መወርወሪያዎቹ፥ ምሰሶዎቹና የሚቆሙባቸው እግሮች፥

34 ከአውራ በግ ቆዳ ተሠርቶ ቀይ ቀለም የተነከረው መደረቢያ፥ ከለፋ ቆዳ የተሠራው መደረቢያ፥ ለመከለያ የተሠራው መጋረጃ፥

35 የድንጋይ ጽላቶቹ ያሉበት የቃል ኪዳኑ ታቦት፥ መሎጊያዎቹና የስርየት መክደኛው፥

36 ገበታውና የመገልገያ ዕቃዎቹ በሙሉ፥ ለእግዚአብሔር የሚቀርበው የተቀደሰው ኅብስት፥

37 ከንጹሕ ወርቅ የተሠራው መቅረዝ፥ የተደረደሩት መብራቶቹና መገልገያ ዕቃዎቹ፥ ለመብራቶቹ የሚሆነው ዘይት፥

38 ከወርቅ የተሠራው መሠዊያ፥ የቅባቱ ዘይት፥ ጣፋጭ ሽታ ያለው ዕጣን፥ ለድንኳኑ ደጃፍ የተሠራለት መጋረጃ፥

39 ከነሐስ የተሠራው መሠዊያ ከነሐስ ከተሠራው መከላከያው ጋር፥ መሎጊያዎቹና የእርሱ መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፥ የመታጠቢያው ሳሕንና ማስቀመጫው፥

40 ለመገናኛው ድንኳን መግቢያ የሚሆኑት መጋረጃዎች፥ ምሰሶዎቹና የሚቆሙባቸው እግሮች፥ ለአደባባዩ መግቢያ የተሠራው መጋረጃና አውታሮቹ፥ ድንኳኑ የሚተከልባቸው ካስማዎች፥ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ የሚገኙ የመገልገያ ዕቃዎች፥

41 ካህኑ አሮንና ልጆቹ በተቀደሰው ስፍራ በክህነት ሲያገለግሉ የሚለብሱአቸው የተቀደሱና ውብ የሆኑ የክህነት አልባሳት ናቸው።

42 እስራኤላውያን ሥራውን ሁሉ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ሠሩ፤

43 ሙሴም ሁሉን ነገር መርምሮ ልክ እግዚአብሔር ባለው መሠረት መሥራታቸውን አረጋገጠ፤ ስለዚህም ሙሴ ባረካቸው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告