ዘፀአት 38 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ አሠራር ( ዘፀ. 27፥1-8 ) 1 የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ከግራር እንጨት ሠራ፤ እርሱም አራት ማእዘን ሆኖ ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ርዝመት፥ ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ስፋት፥ አንድ ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር ቁመት ነበረው፤ 2 ከመሠዊያው ጋር አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ጒጦችንም በአራቱ ማእዘን አደረገበት ሁሉንም በነሐስ ለበጠው። 3 በመሠዊያው ላይ ያሉትንም የመገልገያ ዕቃዎች፥ ድስቶችንም፥ የእሳት መጫሪያዎቹንም፥ ጐድጓዳ ሳሕኖችንም፥ ሜንጦዎቹንም፥ ማንደጃዎቹንም ከነሐስ ሠራ፤ 4 መረብ የሚመስል የነሐስ መከላከያ ሠራ፤ እርሱንም እስከ መሠዊያ ግማሽ ቁመት እንዲደርስ አድርጎ በመሠዊያው ክፈፍ ሥር አኖረው፤ 5 ለመሸከሚያ የሚያገለግሉ መሎጊያዎች መሹለኪያ ይሆኑ ዘንድ አራት ቀለበቶችን ሠርቶ በአራቱ ማእዘኖች ላይ አደረጋቸው። 6 መሎጊያዎችንም ከግራር እንጨት ሠርቶ በነሐስ ለበጣቸው። 7 በመሠዊያው ጐንና ጐን ባሉት ቀለበቶችም ውስጥ አስገባቸው፤ መሠዊያው ከሳንቃ የተሠራ ሆኖ ውስጡ ክፍት ነበር። የመታጠቢያው ሳሕን አሠራር ( ዘፀ. 30፥18 ) 8 የመታጠቢያውን ሳሕንና ማስቀመጫውን ጭምር ከነሐስ ሠራ፤ ነሐሱም የተገኘው በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ የሚያገለግሉ ሴቶች ካመጡት የነሐስ መስተዋቶች ነው። የድንኳኑ መግቢያ ክፍል አሠራር ( ዘፀ. 27፥9-19 ) 9 ለተቀደሰው ድንኳን መግቢያ ክፍል መጋረጃዎችን ከጥሩ በፍታ ሠራ፤ የመጋረጃዎቹም ርዝመት በደቡብ በኩል አርባ አራት ሜትር ነበር፤ 10 መጋረጃዎችን የሚደግፉ ኻያ ምሰሶዎችንና ኻያ እግሮቻቸውን ከነሐስ ሠራ፤ የምሰሶዎቹንም ኩላቦችና ዘንጎች ከብር ሠራ፤ 11 ከሰሜንም በኩል የአደባባዩ አሠራር እንደዚሁ ነበር፤ 12 በምዕራብ በኩል ኻያ ሁለት ሜትር ርዝመት ያላቸው መጋረጃዎች ነበሩ፤ እነርሱም ዐሥር እግሮች ያሉአቸው ዐሥር ምሰሶዎች ነበሩአቸው፤ ምሰሶዎቹም ከብር የተሠሩ ኩላቦችና ዘንጎች ነበሩአቸው። 13 የመግቢያው ደጅ ባለበት በምሥራቅ በኩል የአደባባዩ ስፋት ኻያ ሁለት ሜትር ነበር። 14 በአንድ በኩል ያለው የበሩ መጋረጃ ስድስት ሜትር ከስድሳ ሳንቲ ሜትር ተኩል ርዝመት፥ ሦስት ምሰሶዎችና ሦስት እግሮችም ነበሩት። 15 እንዲሁም በሌላው በኩል በአደባባዩ ደጅ በዚህና በዚያ ስድስት ሜትር ከስድሳ ሳንቲ ሜትር ርዝመት፥ ሦስት ምሰሶዎችና ሦስት እግሮች ነበሩት። 16 በድንኳኑ መግቢያ ዙሪያ ያሉት መጋረጃዎች ሁሉ ከጥሩ በፍታ የተሠሩ ነበሩ፤ 17 የምሰሶዎቹ እግሮች የተሠሩት ከነሐስ ነበር፤ ኩላቦቹ ዘንጎቹና የምሰሶዎቹ ጫፎች መሸፈኛዎች ከብር የተሠሩ ነበሩ፤ በአደባባዩ ዙሪያ ያሉት ምሰሶዎች ሁሉ በብር ዘንጎች የተያያዙ ነበሩ፤ 18 ወደ ድንኳኑ የሚያስገባው ደጃፍ መጋረጃ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ በፍታ ተፈትሎ በእጅ ጥበብ ካጌጠ ቀጭን ሐር የተሠራ ነበር፤ እርሱም እንደ ድንኳኑ በር መግቢያ መጋረጃዎች ሁሉ ርዝመቱ ዘጠኝ ሜትር ቁመቱም ሁለት ሜትር ነበር፤ 19 አራት የነሐስ እግሮች ባሉአቸው አራት ምሰሶዎች ተደግፎ ነበር፤ ኩላቦቻቸው፥ ጫፎቻቸውና ዘንጎቻቸው ከብር የተሠሩ ነበሩ፤ 20 ለድንኳኑና በዙሪያው ላለው የአደባባይ አጥር መጋረጃዎች የሚያገለግሉት ካስማዎች ሁሉ የተሠሩት ከነሐስ ነበር። በድንኳኑ ውስጥ በአገልግሎት ላይ የሚውሉ የብረታ ብረት ዐይነቶች 21 በሙሴ ትእዛዝ፥ በካህኑ በአሮን ልጅ በኢታማር መሪነት የሌዋውያን ተግባር የሆነው የተቀደሰው ድንኳን ዕቃዎች ዝርዝር ቈጠራ እነዚህ ናቸው፦ 22 ከይሁዳ ነገድ የሑር የልጅ ልጅ የሆነው የኡሪ ልጅ ባጽልኤል፥ እግዚአብሔር ለሙሴ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት ሁሉን ነገር ሠራ፤ 23 ከእርሱም ጋር ከዳን ነገድ የሆነው የአሒሳማክ ልጅ አሆሊአብም አንጥረኛ፥ ፕላን አውጪ ባለሞያ፥ እንዲሁም ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ እየጠለፈ ጥሩ በፍታ የሚሠራ ሸማኔ ነበር። 24 ለተቀደሰው ድንኳን መሥሪያ ይሆን ዘንድ ለእግዚአብሔር ተለይቶ የተሰጠ ወርቅ በሙሉ በይፋ በታወቀው ሚዛን ልክ አንድ ሺህ ኪሎ ግራም ይመዝን ነበር 25 ከመላው ከተቈጠረው ሕዝብ የተሰበሰበው ብር መጠን በይፋ በታወቀው ሚዛን ልክ ሦስት ሺህ አራት መቶ ሠላሳ ኪሎ ግራም ነበር፤ 26 ይህም በሕዝብ ቈጠራ ጊዜ የተመዘገቡት ሰዎች እያንዳንዳቸው በይፋ በታወቀው ሚዛን ልክ የከፈሉትን ድርሻ ጠቅላላ ድምር የሚያኽል ነበር፤ በሕዝብ ቈጠራ የተመዘገቡትም ኻያ ዓመት የሞላቸውና ከዚያም በላይ የሆኑት ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ ኀምሳ ወንዶች ነበሩ። 27 ከብሩም ሦስት ሺህ አራት መቶ ኪሎ የሚሆነው ለተቀደሰው ድንኳንና ለመጋረጃዎች መቆሚያ የሚሆኑ አንድ መቶ እግሮች የተሠሩበት ነበር፤ ይኸውም ለእያንዳንዱ እግር ሠላሳ አራት ኪሎ ግራም ተመድቦለት ነው። 28 በቀረውም ሠላሳ ኪሎ ብር ባጽልኤል ለምሰሶዎቹ ዘንጎችን፥ ኩላቦችንና ጒልላቶችን ሠራ። 29 ለእግዚአብሔር ተለይቶ የተሰጠ ነሐስ ሁለት ሺህ አራት መቶ ኻያ አምስት ኪሎ ግራም የሚመዝን ነበር፤ 30 ወደ መገናኛው ድንኳን መግቢያ የሆነው ደጃፍ የሚቆምባቸውን እግሮች፥ ከነሐስ መከላከያው ጋር የነሐስ መሠዊያውን፥ ለመሠዊያው መገልገያ የሆኑትን ዕቃዎች በሙሉ ከዚህ ነሐስ ሠራ፤ 31 በዙሪያ ያለው የአደባባይ አጥርና ወደ አደባባዩ የሚያስገባው ደጃፍ የሚቆሙባቸውን እግሮች፥ እንዲሁም የድንኳኑና በዙሪያው ያለውን የአደባባይ አጥር ካስማዎችን ሁሉ ሠራ። |