Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 37 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የቃል ኪዳኑ ታቦት አሠራር
( ዘፀ. 25፥10-22 )

1 ባጽልኤልም ከግራር እንጨት የቃል ኪዳኑን ታቦት ሠራ፤ ርዝመቱ መቶ ዐሥር ሳንቲ ሜትር፥ የጐኑ ስፋት ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር፥ ቁመቱም ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር ነበር።

2 ውስጡንም ውጪውንም በጥሩ ወርቅ ለበጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አደረገለት፤

3 ለመሸከሚያ የሚያገለግሉ አራት የወርቅ ቀለበቶችም አደረገለት፤ እነርሱንም በአንድ ወገን ሁለት ቀለበቶች በሌላውም ወገን ሁለት ቀለበቶች በማድረግ በአራቱ እግሮች ላይ አኖራቸው፤

4 መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው።

5 በታቦቱ ጐንና ጐን ላይ በተሠሩትም ቀለበቶች ውስጥ አስገባቸው።

6 ርዝመቱ መቶ ዐሥር ሳንቲ ሜትር ስፋቱም ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር የሆነ የስርየት መክደኛ ከንጹሕ ወርቅ ሠራ፤

7 ክንፍ ያላቸውንም ሁለት ኪሩቤል ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሠርቶ፥

8 በመክደኛው ላይ አንዱን በአንድ በኩል፥ ሁለተኛውንም በሌላ በኩል አደረገው፤ ከመክደኛውም ጋር አንድ ወጥ አድርጎ ሠራቸው።

9 ኪሩቤልም ክንፎቻቸውን ወደ ላይ ዘርግተው መክደኛውን በመሸፈን እርስ በርስ እንዲተያዩ አደረገ።


የተቀደሰው ኅብስት ማኖሪያ ጠረጴዛ አሠራር
( ዘፀ. 25፥23-30 )

10 ርዝመቱ ሰማኒያ ስምንት ሳንቲ ሜትር የጐኑ ስፋት አርባ አራት ሳንቲ ሜትር፥ ቁመቱም ስድሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር የሚሆን ጠረጴዛ ከግራር እንጨት ሠራ።

11 በንጹሕም ወርቅ ለብጦ፥ በዙሪያው የወርቅ ክፈፍ አደረገለት።

12 ደግሞም በዙሪያው ሰባ አምስት ሚሊ ሜትር ስፋት ያለው ጠርዝና በጠርዙም ዙሪያ የወርቅ ክፈፍ አደረገለት።

13 አራት የወርቅ ቀለበቶች ሠርቶ አራቱ እግሮቹ በተተከሉበት አራት ማእዘኖች ላይ አደረገ።

14 ጠረጴዛውን ለመሸከም የሚያገለግሉ የመሎጊያ ማስገቢያዎቹ ቀለበቶችም በክፈፉ አጠገብ ነበሩ።

15 መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው።

16 በጠረጴዛው ላይ የሚቀመጡ ልዩ ልዩ የመገልገያ ዕቃዎችን ከንጹሕ ወርቅ ሠራ፤ ይኸውም፦ የዕጣን ማስቀመጫ ዝርግ ሳሕኖችንና ወጭቶችን፥ ጭልፋዎችን ለወይን ጠጅ መቅጃ የሚሆኑ ማንቈርቈሪያዎችንና ጐድጓዳ ሣሕኖችን ሠራ።


የመቅረዙ አሠራር
( ዘፀ. 25፥31-40 )

17 መቅረዙንም ከንጹሕ ወርቅ ሠራ፤ ማቆሚያውንና ዘንጉንም ከተቀጠቀጠ ወርቅ አበጀ፤ ለጌጥ የሚሆኑትንም የአበባዎች ቅርጽ ከነእንቡጣቸውና ከነቀንበጣቸው አንድ ወጥ አድርጎ ሠራቸው።

18 በአንድ በኩል ሦስት፥ በሌላ በኩል ሦስት በመሆን ከጐኖቹ ስድስት ቅርንጫፎች እንዲወጡ አደረገ።

19 ስድስቱም ቅርንጫፎች እያንዳንዱ እንቡጥና ቀንበጥ ያላቸውን የለውዝ አበባዎችን የሚመስሉ ሦስት ሦስት ጌጠኛ የአበባ ወርድ ተስለውበት ነበር።

20 የመቅረዙም ዘንግ እንቡጥና ቀንበጥ ያላቸውን የለውዝ አበባዎችን የሚመስሉ አራት የጌጠኛ አበባ ወርዶች ተስለውበት ነበር።

21 ከሦስቱም ጥንድ ቅርንጫፎች በእያንዳንዱ ጥንድ ሥር አንድ እንቡጥ ተስሎ ነበር፤

22 እንቡጦቹ ቅርንጫፎቹና መቅረዙ ከተቀጠቀጠ ወርቅ አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ።

23 ለመቅረዙም ሰባት መብራቶችን፥ መኰስተሪያዎችንና የኲስታሪ ማኖሪያዎችን ከንጹሕ ወርቅ ሠራ።

24 መቅረዙንና የእርሱን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ ለመሥራት የፈጀበት የወርቅ መጠን ሠላሳ አምስት ኪሎ ግራም ነበር።


የዕጣን መሠዊያው አሠራር
( ዘፀ. 30፥1-5 )

25 ርዝመቱ አርባ አምስት ሳንቲ ሜትር፥ የጐኑ ስፋት አርባ አምስት ሳንቲ ሜትር ቁመቱም ዘጠና ሳንቲ ሜትር የሆነ አራት ማእዘን የዕጣን መሠዊያ ከግራር እንጨት ሠራ፤ በአራቱም ማእዘን ያሉት ጒጦቹ ከእርሱ ጋር አንድ ወጥ ሆነው የተሠሩ ነበሩ።

26 ጫፉን፥ አራት ጐኖቹንና ጒጦቹን ሁሉ በንጹሕ ወርቅ ለበጠ፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አበጀለት።

27 ከክፈፉም ሥር ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን አደረገ፤ በሁለቱም ጐን ግራና ቀኝ አኖራቸው፤ እነርሱም የዕጣን መሠዊያውን ለመሸከም የሚያገለግሉ መሎጊያዎች የሚሾልኩባቸው ነበሩ።

28 መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠርቶ በወርቅ ለበጣቸው።


የቅባቱ ዘይትና የዕጣኑ አዘገጃጀት
( ዘፀ. 30፥22-38 )

29 የተቀደሰውን የቅባት ዘይትና መልካም መዓዛ ያለውንም ጥሩ ዕጣን እንደ ሽቶ ቀላቅሎ ሠራ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告