ዘፀአት 36 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 “ባጽልኤልና ኦሆሊአብ እንዲሁም ለተቀደሰው ድንኳን ዝግጅት እግዚአብሔር ማናቸውንም ሥራ ለመሥራት ችሎታንና ዕውቀትን የሰጣቸው ሌሎች ሰዎች እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ይሠራሉ።” የሕዝቡ ስጦታ ብዛት 2 ሙሴም ባጽልኤልንና ኦሆሊአብን፥ እንዲሁም እግዚአብሔር ልዩ ችሎታ የሰጣቸውንና ለመርዳት ፈቃደኞች የነበሩትን ሌሎችን ጥበበኞች ሁሉ ጠርቶ ሥራውን እንዲጀምሩ ነገራቸው። 3 እነርሱም እስራኤላውያን ለተቀደሰው ድንኳን መሥሪያ እንዲውል ያመጡትን ስጦታ ከሙሴ እጅ ተቀበሉ፤ የእስራኤል ሕዝብ ግን በየማለዳው ስጦታቸውን ለሙሴ ከማምጣት አልተቈጠቡም። 4 ከዚህም በኋላ ሥራውን የሚያከናውኑት ጥበበኞች ሁሉ ሥራቸውን ትተው ወደ ሙሴ በመሄድ፥ 5 “ሕዝቡ እግዚአብሔር ላዘዘው ሥራ ከሚያስፈልገው በላይ እጅግ ብዙ ስጦታ በማምጣት ላይ ናቸው” አሉት። 6 ስለዚህ ሙሴ ለተቀደሰው ድንኳን መሥሪያ የሚሆን ስጦታ ከእንግዲህ ወዲህ እንዳያመጡ በሰፈሩ ሁሉ ትእዛዝ አስተላለፈ፤ ከዚያም በኋላ ሕዝቡ ስጦታ ማምጣቱን አቆመ፤ 7 የቀረበውም ስጦታ ሥራውን ሁሉ ለማከናወን በቅቶ የሚተርፍ ነበር። የመገናኛው ድንኳን አሠራር ( ዘፀ. 26፥1-37 ) 8 ሥራውን ከሚያከናውኑት መካከል እጅግ ጥበበኞች የነበሩት የተቀደሰውን ድንኳን ሠሩ፤ እነርሱም ድንኳኑን ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ ከተፈተሉ፥ የኪሩቤል ሥዕል ከተጠለፈባቸው ዐሥር የበፍታ መጋረጃዎች ሠሩት። 9 የእያንዳንዱም መጋረጃ መጠን ተመሳሳይ ሆኖ ርዝመቱ ዐሥራ ሁለት ሜትር፥ የጐኑ ስፋት ሁለት ሜትር ነበር። 10 እነርሱንም አምስቱን በአንድ በኩል፥ ሌሎቹንም አምስቱን በሌላ በኩል አገጣጥመው ሰፉ። 11 ከተገጣጠሙት መጋረጃዎች በአንደኛው ክፍል ጠርዝ ላይ ከሰማያዊ ግምጃ የተሠሩ ቀለበቶችን አደረጉ፤ በሌላም በኩል ተገጣጥመው ከተሰፉት መጋረጃዎችም በአንደኛው ጠርዝ ላይ እንዲሁ አደረጉ፤ 12 በመጀመሪያው ክፍል የመጀመሪያ መጋረጃ ላይ ኀምሳ ቀለበቶች፥ እንዲሁም በሁለተኛው ክፍል መጨረሻ መጋረጃ ላይ ከሌሎቹ ቀለበቶች ፊት ለፊት የሚሆኑ ኀምሳ ቀለበቶች አደረጉ። 13 በሁለቱም በኩል ያሉትን መጋረጃዎች አገጣጥሞ አንድ ለማድረግ ኀምሳ የወርቅ መያዣዎች ሠሩላቸው። 14 ለድንኳኑ መክደኛ የሚሆኑ ዐሥራ አንድ መጋረጃዎችንም ከፍየል ጠጒር የተፈተለ ጨርቅ አዘጋጁ። 15 የሁሉም መጠን እኩል ሆኖ የእያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመት ዐሥራ ሦስት ሜትር፥ የጐኑም ስፋት ሁለት ሜትር ነበር። 16 አምስቱን በአንድ በኩል፥ ስድስቱንም በሌላ በኩል በማድረግ አገጣጥመው ሰፉአቸው። 17 በአንደኛው ክፍል የመጨረሻ መጋረጃ ዘርፍ ላይ ኀምሳ ቀለበቶች፥ በሁለተኛው ክፍል የመጨረሻ መጋረጃ ዘርፍ ላይ ኀምሳ ቀለበቶች አስገቡ። 18 በሁለቱም በኩል ያሉትን መጋረጃዎች አገጣጥመው አንድ መክደኛ ለማበጀት ኀምሳ የነሐስ መያዣዎችን ሠሩ። 19 ከውጪ በኩል መክደኛ ይሆኑ ዘንድ አንደኛውን ቀይ ቀለም ከተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፥ ሌላውንም ከለፋ ቊርበት ሌሎች ሁለት መጋረጃዎችን ሠሩ። 20 ለድንኳኑም መደገፊያ ቀጥተኛ የሆኑ ተራዳዎች ከግራር እንጨት ሠሩ፤ 21 እያንዳንዱ ተራዳ ቁመቱ አራት ሜትር የጐኑም ስፋት ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር ሲሆን፥ 22 የተራዳው ሁለት ሳንቃዎች መገጣጠም ይችሉ ዘንድ ማያያዣዎች ነበሩአቸው፤ ለማደሪያው ተራዳዎች ሁሉ እንዲሁ አደረጉ። 23 በድንኳኑም በደቡብ በኩል ኻያ ተራዳዎች አደረጉ፤ 24 ከኻያውም ተራዳዎች በታች ሁለት ማገጣጠሚያ ጒጦች ባሉት በእያንዳንዱ ተራዳ ሥር ሁለት ሁለት በማኖር አርባ የብር እግሮችን አደረጉ። 25 ከድንኳኑ በስተ ሰሜን በኩል ኻያ ተራዳዎችን አደረጉ፤ 26 በእያንዳንዱም ተራዳ ሥር ሁለት ሁለት በማኖር አርባ የብር እግሮችን አደረጉ፤ 27 ከድንኳኑ በስተጀርባ በምዕራብ በኩል ስድስት ተራዳዎችን አደረጉ፤ 28 በስተጀርባ ማእዘኖቹም ሁለት ሁለት ተራዳዎች ሠሩ። 29 እነዚህ በማእዘኖቹ ያሉት ተራዳዎች በግርጌ በኩል ተገጣጥመው እስከ ላይ አንደኛው ዋልታ ድረስ የተያያዙ ነበሩ፤ በሁለቱ ማእዘኖች ላይ የተደረጉት ሁለቱ ተራዳዎች የተሠሩት በዚህ ዐይነት ነበር። 30 ስለዚህ እያንዳንዱ ተራዳ በሥሩ ሁለት እግሮች እንዲኖሩት በማድረግ ስምንት ተራዳዎችና ከብር የተሠሩ ዐሥራ ስድስት እግሮች ነበሩ። 31 ዐሥራ አምስት መወርወሪያዎችንም ከግራር እንጨት ሠሩ፤ በዚህ ዐይነት አምስቱ ከድንኳኑ በአንድ በኩል ላሉት ተራዳዎች ሲሆኑ፥ 32 አምስቱ ደግሞ በሌላ በኩል ላሉት ተራዳዎች ሆኑ፤ እንዲሁም አምስቱ ከድንኳኑ በስተጀርባ በምዕራብ በኩል እንዲሆኑ ተደረገ። 33 ከተራዳዎቹ በጐን በኩል በመካከል ያለው መወርወሪያ ከድንኳኑ ከአንድ ጫፍ መጨረሻ ተያይዞ እስከ ሌላው ጫፍ ይደርስ ነበር። 34 ተራዳዎቹንም በወርቅ ለበጡአቸው፤ ዋልታዎቻቸውንም የመወርወሪያው መተላለፊያ ይሆኑ ዘንድ ከወርቅ ሠሩ፤ መወርወሪያዎቹም በወርቅ የተለበጡ ነበሩ። 35 መጋረጃዎችንም ከጥሩ በፍታ ሠሩ፤ እርሱም ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ የተፈተለ ሲሆን የኪሩቤል ሥዕል ተጠልፎበት ነበር። 36 መጋረጃዎቹን የሚያያይዙ አራት ምሰሶዎችንም ከግራር እንጨት ሠርተው በወርቅ ለበጡአቸው፤ ኩላቦቻቸውንም ከወርቅ ሠሩ፤ ምሰሶዎቹ የሚቆሙባቸውን አራት እግሮችንም ከብር ሠሩ፤ 37 ለድንኳኑም ደጃፍ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ቀይ ከፈይ በጥልፍ የተጌጠ መጋረጃ ሠሩ፤ 38 ለዚህም መጋረጃ ኩላቦች ያሉአቸው አምስት ምሰሶዎችን ሠሩ፤ የእነርሱንም ጒልላቶችና ዘንጎቹን በወርቅ ለበጡ፤ ለምሰሶዎቹም ማቆሚያ አምስት የነሐስ እግሮች ሠሩ። |