Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 35 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የሰንበት አከባበር ሥርዓት

1 ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ በአንድነት ጠርቶ እንዲህ አላቸው፤ “ትፈጽሙት ዘንድ እግዚአብሔር የሰጣችሁ ትእዛዝ ይህ ነው፤

2 ሥራችሁን ሁሉ የምትሠሩባቸው ስድስት ቀኖች አሉላችሁ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ዕረፍት ታደርጉበት ዘንድ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ዕለት ነው፤ በዚህ ቀን ሥራ የሚሠራበት ማንኛውም ሰው በሞት ይቀጣል፤

3 ስለዚህ በሰንበት ቀን በቤታችሁ እሳት እንኳ አታንድዱ።”


ለተቀደሰው ድንኳን ሥራ የሚቀርብ መባ
( ዘፀ. 25፥1-9 )

4 ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው፤

5 ለእግዚአብሔር መባ አቅርቡ፤ መባ ለማቅረብ የፈለገ ሁሉ እያንዳንዱ ልቡ የፈቀደውን ያኽል የወርቅ፥ የብር፥ ወይም የነሐስ

6 ጥሩ ከፈይ ሰማያዊ፥ ሐምራዊና ቀይ ቀለም የተነከረ የበግ ጠጒር፥ ከፍየል ጠጒር የተሠራ ልብስ፥

7 ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፤ የለፋ ቊርበት፥ የግራር እንጨት፥

8 ለመብራት የሚሆን የወይራ ዘይት፥ ለቅባት ዘይትና ለዕጣን ሽታ የሚሆን ቅመማ ቅመም፥

9 በተቀደሰው ኤፉድና የደረት ኪስ ላይ የሚሆን መረግድና ሌላውንም ጌጠኛ ፈርጥ ያምጣ።


የመገናኛው ድንኳኑ መገልገያ ዕቃዎች
( ዘፀ. 39፥34-43 )

10 “በመካከላችሁ የሚገኙ የእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች ሁሉ እግዚአብሔር ያዘዘውን ማናቸውንም ነገር ለመሥራት ይምጡ፤

11 ይኸውም ድንኳኑን፥ የውስጥና የውጪ መደረቢያዎችን፥ መያዣዎችንና ተራዳዎችን መወርወሪያዎችንና ምሰሶዎችን፥ እግሮቹን፥

12 የኪዳኑን ታቦት፥ መሎጊያዎቹን፥ የስርየት መክደኛውንና የታቦቱ መሸፈኛ የሆነውን መጋረጃ፥

13 ጠረጴዛውን፥ መሎጊያዎቹንና የእርሱንም መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ እንዲሁም ለእግዚአብሔር የሚቀርበውን የተቀደሰ ኅብስት

14 ለመብራት ማኖሪያ የሚሆነውን መቅረዝና የእርሱንም መገልገያ ዕቃዎች፥ መብራቶቹም ከዘይታቸው ጋር፥

15 የዕጣን መሠዊያውንና መሎጊያዎቹን፥ የቅባቱን ዘይት፥ ጣፋጭ ሽታ ያለውን ዕጣን፥ የድንኳኑን በር መጋረጃ፥

16 የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበትን መሠዊያ፥ የነሐሱንም መከላከያ መሎጊያዎቹንና የእርሱን መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሳሕንና ማስቀመጫውን፥

17 ያደባባዩን መጋረጃዎች፥ ምሰሶዎቹንና እግሮቻቸውን፥ የአደባባዩን በር መጋረጃዎች፥

18 የድንኳኑንና የአደባባዩን ካስማዎች፥ አውታሮችና

19 ካህናቱ በተቀደሰው ስፍራ በሚያገለግሉበት ጊዜ የሚለብሱአቸው በጥበብ ያጌጡ ልብሶችን ይኸውም ለካህኑ ለአሮንና ለልጆቹ የተሠሩትን የተቀደሱ ልብሶች ይሥሩ።”


ሕዝቡ ያመጡት ስጦታ

20 ከዚህ በኋላም የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ ከሙሴ ፊት ወጡ፤

21 ለመሥራት እያንዳንዱ ለመስጠት ልቡ የፈቀደውን ለእግዚአብሔር መባ አመጣ፤ በዚህም ዐይነት እስራኤላውያን ለመንፈሳዊ አገልግሎት ለካህናት ልብስ የሚሆነውን ነገር ሁሉ አመጡ።

22 ስጦታ ማቅረብ የፈለገ ሴቱም ወንዱም እያንዳንዱ የደረት ጌጥ፥ የጆሮ ወርቅ፥ የጣት ቀለበት፥ ድሪዎችና የወርቅ ጌጦችን አምጥቶ ለእግዚአብሔር የተለዩ እንዲሆኑ አደረገ።

23 ጥሩ በፍታ፥ ሰማያዊ፥ ሐምራዊና ቀይ ከፈይ ከፍየል ጠጒር የተሠራ ልብስ፥ ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፤ እንዲሁም የለፋ ቊርበት ያለው ሁሉ ይዞ መጣ።

24 ብር ወይም ነሐስ ለማቅረብ ችሎታ ያላቸውም ሁሉ ስጦታቸውን ለእግዚአብሔር አመጡ፤ ለማንኛውም አገልግሎት የሚውል የግራር እንጨት ያለውም አመጣ።

25 የእጅ ጥበብ ችሎታ ያላቸው ሴቶችም በእጃቸው የሠሩትን ጥሩ በፍታና ሰማያዊ፥ ሐምራዊና ቀይ ከፈይ ይዘው መጡ፤

26 እንዲሁም ስጦታ ለማቅረብ የፈለጉ ሴቶች ከፍየል ጠጒር የተገመደ ክር ሠሩ፤

27 አለቆችም በተቀደሰው ኤፉድና በደረት ኪስ ላይ የሚሆኑ መረግድና ሌሎችም ጌጣጌጦች፥

28 ለመብራትና ለቅባት እንዲሁም ጣፋጭ ሽታ ለሚሰጥ ዕጣን የሚሆን ቅመማ ቅመምና ዘይት አመጡ፤

29 ወንዶችና ሴቶች የእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እግዚአብሔር ሙሴን ላዘዘው ሥራ የሚውል ልባቸው የፈቀደውን ስጦታ ለእግዚአብሔር አመጡ።


የመገኛውን ድንኳን የሚሠሩ የእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች
( ዘፀ. 31፥1-11 )

30 ሙሴ ለእስራኤላውያን እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ከይሁዳ ወገን የሑር የልጅ ልጅ የሆነውን የኡሪ ልጅ ባጽልኤልን መርጦታል፤

31 እግዚአብሔር እርሱን በመንፈሱ ኀይል እንዲሞላ አድርጎ ማናቸውንም የጥበብ ሥራ መሥራት እንዲችል ብልኀትን፥ ችሎታንና ማስተዋልን ሰጥቶታል።

32 ጥበብ የሞላበትን የሥራ ዕቅድ ለማውጣት፥ ያንንም ዕቅድ በወርቅ በብርና በነሐስ ለማስጌጥ፥

33 የዕንቊ ጌጣጌጦችን ለመሥራትና የእንጨት ቅርጾችን ለማውጣት እንዲሁም ሌሎችን የጥበብ ሥራዎች ለማከናወን ችሎታ ሰጥቶታል።

34 ለእርሱና ከዳን ወገን የአሒሳማክ ልጅ ለሆነው ኦሆሊአብ የእጅ ጥበብ ዕውቀታቸውን ለሌሎች የማስተማርን ችሎታ ሰጥቶአቸዋል።

35 በአንጥረኛ፥ በፕላን አውጪ ባለሞያ፥ ጥሩ በፍታ፥ ሰማያዊ፥ ሐምራዊና ቀይ ቀለም የተነከረ ከፈይ ሌላውንም የልብስ ሥራ በሚያከናውኑ ሸማኔዎች የተሠራውን ነገር ሁሉ ለማስጌጥ የሚችሉበትን ብልኀት ሰጥቶአቸዋል፤ እነርሱ ማናቸውንም የጥበብ ሥራ ለመሥራትና በብልኀት የሚሠራውንም ሁሉ ዕቅድ ለማውጣት የሚችሉ ናቸው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告