ዘፀአት 32 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየወርቅ ጥጃ ምስል ( ዘዳ. 9፥6-29 ) 1 ሕዝቡ ሙሴ ከተራራው ሳይወርድ እዚያ ብዙ እንደ ዘገየ ባዩ ጊዜ በአንድነት በመሰብሰብ አሮንን ከበው “ያ ከግብጽ ምድር መርቶ ያወጣን ሙሴ ምን እንደ ደረሰበት አናውቅም፤ ስለዚህ በፊት በፊታችን እየሄዱ የሚመሩን አማልክትን ሥራልን” አሉት። 2 አሮንም “ሚስቶቻችሁ፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ የሚያጌጡበትን የጆሮ ወርቅ ሁሉ ሰብስባችሁ አምጡልኝ” አላቸው። 3 ስለዚህ ሁሉም ያላቸውን የወርቅ ጒትቻ ሁሉ አውልቀው ወደ አሮን አመጡለት። 4 እርሱም የወርቅ ጒትቻውን ሁሉ ወስዶ በእሳት አቀለጠው፤ የቀለጠውንም ወርቅ በቅርጽ መሥሪያ ውስጥ አግብቶ የወርቅ ጥጃ አድርጎ ሠራው። እነርሱም “እስራኤል ሆይ! ከግብጽ ምድር መርቶ ያወጣን አምላካችን ይህ ነው!” አሉ። 5 አሮንም ይህን ባየ ጊዜ በወርቁ ጥጃ ፊት መሠዊያ ሠርቶ “ነገ ለእግዚአብሔር ክብር በዓል ይደረጋል” ሲል አስታወቀ። 6 በማግስቱ ሰዎቹ ተነሥተው የሚቃጠል መሥዋዕትና የአንድነት መሥዋዕት አቀረቡ፤ እነርሱም ተቀምጠው ከበሉና ከጠጡ በኋላ ከመጠን በላይ ሊፈነጥዙ ተነሡ። 7 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “ከግብጽ ምድር መርተህ ያወጣኸው ሕዝብህ ራሱን ስላረከሰ ፈጥነህ ውረድ፤ 8 እነርሱ እንዲከተሉት ካዘዝኳቸው መንገድ ወዲያውኑ ወጥተዋል፤ ከቀለጠ ወርቅ ጥጃ ሠርተውም ሰግደውለታል፤ መሥዋዕትም አቅርበውለት ‘ከግብጽ ምድር ያወጣን አምላካችን ይህ ነው’ ብለዋል። 9 እነርሱ ምን ያኽል ልበ ደንዳኖች እንደ ሆኑ እኔ ዐውቃለሁ፤ 10 አሁንም እነሆ፥ በእነርሱ ላይ እጅግ ተቈጥቼ ላጠፋቸው ስለ ተዘጋጀሁ ተወኝ፤ አንተንም ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ።” 11 ሙሴ ግን እግዚአብሔር አምላኩን በመማለድ እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር ሆይ፥ በሥልጣንህና በታላቅ ኀይልህ ከግብጽ ምድር ያወጣኸውን ሕዝብህን እስከዚህ የምትቈጣው ስለምነው? 12 ግብጻውያን ‘እግዚአብሔር ከግብጽ ምድር መርቶ ያወጣቸው ለክፉ ነገር፥ ማለት በተራራዎች ላይ ሊገድላቸውና ፈጽሞ ሊያጠፋቸው ነው’ እያሉ መዘባበቻ እንዲያደርጉን ለምን ትፈቅዳለህ? አሁንም ከቊጣህ ወደ ምሕረት ተመለስ፤ ይህንንም ሁሉ ጥፋት በሕዝብህ ላይ አታምጣ። 13 አገልጋዮችህን አብርሃምን፥ ይስሐቅንና ያዕቆብን አስብ፤ ዘራቸውን እንደ ሰማይ ከዋክብት ልታበዛውና የተስፋይቱንም ምድር ርስት ለዘለዓለም አድርገህ ልትሰጣቸው በመሐላ የገባህላቸውንም ቃል ኪዳን አስብ።” 14 ስለዚህ እግዚአብሔር ከቊጣ ወደ ምሕረት ተመልሶ፥ ሊያመጣባቸው የነበረውን መቅሠፍት እንዲገታ አደረገ። 15 ከዚህ በኋላ ሙሴ ተነሥቶ በሁለቱም በኩል ዐሥሩ ትእዛዞች የተጻፉባቸውን ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶች በመያዝ ከተራራው ወረደ። 16 እነዚህም ጽላቶች የእግዚአብሔር ሥራ ናቸው። በላያቸው ላይ ያሉት ጽሑፎች የተቀረጹት በእግዚአብሔር ነው። 17 ኢያሱ የሕዝቡን ጫጫታ ሰምቶ ሙሴን “በሰፈሩ ውስጥ የጦርነት ድምፅ ይሰማል” አለው። 18 ሙሴም “ይህ የምሰማው የዘፈን ድምፅ እንጂ የድል አድራጊዎች ድንፋታ ወይም የተሸነፈ ሕዝብ የለቅሶ ጫጫታ አይደለም” አለው። 19 ሙሴም ወደ ሰፈሩ ተጠግቶ ጥጃውንና ጭፈራ ባየ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፤ ይዞአቸው የመጣውንም ጽላቶች በተራራው ሥር ወርውሮ ሰባበራቸው። 20 እነርሱ የሠሩትንም ጥጃ ወስዶ አቀለጠው፤ እስኪልም ድረስ አደቀቀውና ከውሃ ጋር ደባልቆ የእስራኤል ሕዝብ እንዲጠጣው አደረገ። 21 አሮንንም “ከቶ ይህ ሕዝብ ምን አድርጎህ ነው ይህን የመሰለ አስከፊ ኃጢአት እንዲሠራ ያደረግኸው?” አለው። 22 አሮንም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ጌታዬ በእኔ ላይ አትቈጣ፤ ይህ ሕዝብ ምን ያኽል የክፋት ዝንባሌ እንዳለው አንተ ታውቃለህ 23 እነርሱ ‘ያ ከግብጽ መርቶ ያወጣን ሰው፥ ሙሴ ምን እንደ ደረሰበት አናውቅም፤ ስለዚህ በፊታችን እየሄዱ የሚመሩን አማልክት ሥራልን’ አሉኝ። 24 እኔ ከወርቅ የተሠሩ ጌጣጌጦቻቸውን አውልቀው እንዲያመጡልኝ ነገርኳቸው፤ እነርሱም ያላቸውን ጌጣጌጥ ሁሉ አመጡልኝ፤ ጌጣጌጦቹንም ወደ እሳት ውስጥ በጣልኳቸው ጊዜ ይህ የጥጃ ምስል ወጣ።” 25 አሮን ሕዝቡን በጠላቶቻቸው ፊት መሳለቂያ እስኪሆኑ ድረስ መረን እንደ ለቀቃቸው ሙሴ ተመለከተ። 26 ስለዚህ በሰፈሩ ደጃፍ ቆሞ “የእግዚአብሔር ወገን የሆነ ሁሉ ወደ እኔ ይምጣ!” በማለት ድምፁን ከፍ አድርጎ ተናገረ፤ ሌዋውያንም ሁሉ በዙሪያው ተሰበሰቡ፤ 27 እንዲህም አላቸው፦ “እያንዳንዳችሁ ሰይፋችሁን መዛችሁ ከዚህ በር እስከ ወዲያኛው በር ድረስ በሰፈሩ ውስጥ በመመላለስ ያለ ምንም ምሕረት ወንድሞቻችሁን፥ ወዳጆቻችሁንና ጐረቤቶቻችሁን እንድትገድሉ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር አዞአችኋል።” 28 ሌዋውያንም ለቃሉ ታዛዦች በመሆን በዚያን ቀን ሦስት ሺህ ሰው ገደሉ። 29 ሙሴም ሌዋውያንን እንዲህ አለ፤ “ዛሬ ልጆቻችሁንና ወንድሞቻችሁን በመግደል እግዚአብሔርን የምታገለግሉ ካህናት ሆናችሁ ራሳችሁን ቀድሳችኋል፤ እግዚአብሔርም በረከቱን ሰጥቶአችኋል።” 30 በማግስቱም ሙሴ ለእስራኤላውያን “አስከፊ የሆነ ታላቅ በደል ሠርታችኋል፤ ነገር ግን እነሆ አሁንም እንደገና እግዚአብሔር ወደሚገለጥበት ተራራ እወጣለሁ፤ ምናልባት ስለ ኃጢአታችሁ ይቅርታ አስገኝላችሁ ይሆናል” አለ። 31 ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ተመልሶ እንዲህ አለው፤ “ይህ ሕዝብ አስከፊ የሆነ ታላቅ በደል በፊትህ ፈጽሞአል፤ ከወርቅ የሠሩትን ምስል አምላክ አድርገው ሰግደውለታል፤ 32 እባክህ ኃጢአታቸውን ይቅር በል፤ ይቅር የማትላቸው ከሆነ ግን የሕዝብህ ስሞች ከተጻፉበት መዝገብ የእኔን ስም ደምስስ።” 33 እግዚአብሔርም እንዲህ ሲል መለሰ፦ “ስሞቻቸውን ከመዝገቤ የምደመስሰው ኃጢአት በመሥራታቸው ያሳዘኑኝን ሰዎች ነው። 34 አሁንም ሂድ፤ ወደነገርኩህ ስፍራ ሕዝቡን ምራ፤ መልአኬም እየመራህ በፊትህ እንደሚሄድ አስታውስ፤ ነገር ግን ይህን ሕዝብ ስለ ኃጢአቱ የምቀጣበት ጊዜ መምጣቱ አይቀርም።” 35 የወርቅ ጥጃ ምስል እንዲሠራላቸው አሮንን በማስገደዳቸው እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ከባድ በሽታ ላከ። |