ዘፀአት 31 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበጽልኤልና ኦሆሊአብ ( ዘፀ. 35፥30—36፥1 ) 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሑር የልጅ ልጅ የሆነውን የኡሪን ልጅ ባጽልኤልን በስም ጠርቼአለሁ። 3 ማንኛውንም የእጅ ጥበብ መሥራት እንዲችል ማስተዋልና ብልኀት የማወቅም ችሎታ ይኖረው ዘንድ በመንፈሴ እንዲሞላ አድርጌአለሁ፤ 4 ስለዚህም በብልኀት የሥራ ዕቅድ እያወጣ ከወርቅ፥ ከብርና ከነሐስ ልዩ ልዩ ነገሮችን ይሠራል። 5 እንዲሁም ለፈርጥ የሚሆነውን ድንጋይ ለመቅረጽ፥ እንጨትንም ለመጥረብ፥ ሌላውንም ሥራ ሁሉ በጥበብ ለማከናወን እንዲችል አድርጌዋለሁ። 6 ከእርሱም ጋር እንዲሠራ ከዳን ነገድ የአሒሳማክን ልጅ ኦሆሊአብን መርጬአለሁ፤ እኔ ያዘዝኩህን ነገር ሁሉ እንዲሠሩ ሌሎችም የእጅ ጥበብ ዐዋቂዎች ሁሉ ታላቅ ችሎታ እንዲኖራቸው አድርጌአለሁ። 7 እንዲሠራ ያዘዝኩትም ይህ ነው፤ የመገናኛው ድንኳን፥ የቃል ኪዳኑ ታቦትና መክደኛው፥ የድንኳኑ መገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፥ 8 ጠረጴዛውና ለእርሱ የሚያስፈልገው ዕቃ፥ የጠራ መቅረዝና ለእርሱ የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ፥ የዕጣን መሠዊያው፥ 9 ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነው መሠዊያና ለእርሱ የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ፥ የመታጠቢያው ሳሕንና ማስቀመጫው፥ 10 አሮንና ልጆቹ በክህነት አገልግሎት ላይ ሲሆኑ የሚጠቀሙባቸው የተዋቡ አልባሳት፥ 11 የቅባቱ ዘይትና ለተቀደሰው ስፍራ የሚሆነው መዓዛው ጣፋጭ የሆነ ዕጣን፤ ልክ እኔ አንተን ባዘዝኩት ዐይነት እነዚህን ሁሉ ነገሮች ይሠራሉ።” ሰንበት 12 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ አዘዘው፤ 13 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው፦ እኔ እግዚአብሔር እናንተን ለእኔ የተለየ ሕዝብ አድርጌ የመረጥኳችሁ መሆኔን የሚያሳይ ሆኖ በሚመጡት ዘመናት ሁሉ በእኔና በእናንተ መካከል ጸንቶ የሚኖር ምልክት ስለ ሆነ የዕረፍት ቀን አድርጌ የመረጥኩትን ሰንበትን ጠብቁ፤ 14 የተቀደሰ ስለ ሆነ ሰንበትን የዕረፍት ቀን አድርጋችሁ ጠብቁት፤ ይህን የሰንበት ቀን የማይጠብቅና የሥራ ቀን አድርጎ የሚጠቀምበት ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ። 15 ሥራችሁን ሁሉ የምታከናውኑባቸው ስድስት የሥራ ቀኖች አሉላችሁ፤ ሰባተኛው ቀን ግን ለእኔ ተለይቶ የተቀደሰ የዕረፍት ቀን ነው፤ በዚህ ቀን ሥራ የሚሠራበት ሁሉ በሞት ይቀጣ። 16 የእስራኤል ሕዝብ ለሚመጣው ትውልድ ሁሉ ይህ ቀን ጸንቶ የሚኖር የቃል ኪዳን ምልክት አድርገው ይጠብቁት፤ 17 እኔ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀኖች ውስጥ ከፈጠርኩ በኋላ ሰባተኛው ቀን ሥራዬን አቁሜ ያረፍኩበት ስለ ሆነ በእኔና በእስራኤል ሕዝብ መካከል ለዘለዓለም ጸንቶ የሚኖር ምልክት ይሁን።” 18 እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ተራራ ላይ ማነጋገሩን ከፈጸመ በኋላ በእግዚአብሔር ጣት በድንጋይ ላይ የተጻፈባቸውን ሁለቱን የቃል ኪዳን ጽላቶች ሰጠው። |