ዘፀአት 30 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየዕጣን መሠዊያ ( ዘፀ. 37፥25-28 ) 1 “ለሚጤስ ዕጣን የሚያገለግል መሠዊያ ከግራር እንጨት ሥራ፤ 2 ርዝመቱ አርባ አምስት ሳንቲ ሜትር የጐኑ ስፋት አርባ አምስት ሳንቲ ሜትር ከፍታውም ዘጠና ሳንቲ ሜትር ሆኖ የተስተካከለ አራት ማእዘን ይሁን። በአራቱም ማእዘን ያሉት ጒጦች ከእርሱ ጋር አንድ ወጥ ይሁኑ፤ 3 የመሠዊያውን ጫፍ፥ አራት ጐኖቹንና ጒጦቹን ሁሉ በንጹሕ ወርቅ ለብጠው፤ የወርቅ ክፈፍም አብጅለት። 4 ሁለት የወርቅ ቀለበቶችን ሠርተህ መሠዊያውን ለመሸከም የሚያገለግሉት መሎጊያዎች እንዲገቡበት ከክፈፉ ሥር አያይዛቸው። 5 መሎጊያዎችንም ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው። 6 ይህንንም መሠዊያ ከቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት ከተሰቀለው መጋረጃ ውጪ አኑረው፤ እኔም በዚያ ለአንተ እገለጥልሃለሁ፤ 7 አሮን በየማለዳው መብራቶችን ለማዘጋጀት በሚመጣበት ጊዜ መልካም መዓዛ ያለውን ዕጣን በመሠዊያው ላይ ይጠን። 8 በየምሽቱም መብራቶቹን ሲያበራ እንዲሁ ያድርግ፤ ይህ የዕጣን መባ አቀራረብ በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ባለማቋረጥ የሚቀጥል መሆን አለበት። 9 በዚህ መሠዊያ ላይ ማናቸውም የተከለከለ ዕጣን፥ የእንስሳ መሥዋዕት፥ ወይም የእህል ቊርባን አታቅርብ፤ የወይን ጠጅ መባም አታፍስስበት። 10 አሮን በዓመት አንድ ጊዜ ለኃጢአት ስርየት መሥዋዕት ከታረደው እንስሳ ደም ወስዶ በአራቱም ጒጦች ላይ በማድረግ መሠዊያው የሚነጻበትን ሥርዓት ይፈጽም፤ ይህም ሥርዓት በሚመጡት ዘመናት ሁሉ በየዓመቱ ይፈጸም፤ በዚህ ዐይነት ይህ መሠዊያ ለእግዚአብሔር በፍጹም የተቀደሰ ይሁን።” የቤዛነት ክፍያ 11 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 12 “የእስራኤልን ሕዝብ በምትቈጥርበት ጊዜ በሕዝብ ቈጠራው ወቅት መቅሠፍት እንዳይደርስባቸው እያንዳንዱ ሰው ለሕይወቱ ቤዛ የሚሆን ዋጋ ይክፈል። 13 ከሕዝብ ቈጠራ ውስጥ የሚገባ እያንዳንዱ ሰው በተቀደሰው ድንኳን በታወቀው ሚዛን ልክ አንድ ጥሬ ብር ይክፈል፤ እያንዳንዱ ሰው ይህን ለእግዚአብሔር መባ አድርጎ ያቅርብ፤ 14 ከሕዝብ ቈጠራው ለመግባት ዕድሜው የፈቀደለት፥ ማለትም ኻያ ዓመት የሞላውና ከዚያም በላይ የሆነ ሁሉ ይህን የእግዚአብሔር መባ ያቅርብ፤ 15 ለሕይወታቸው ቤዛ ይህን መባ ሲያቀርቡ ሀብታሙም ሆነ ድኻው እኩል ይክፈል እንጂ የሀብታሙ ክፍያ ብዙ የድኻው ክፍያ አነስተኛ አይሁን። 16 ይህን መባ ከእስራኤል ሕዝብ ሰብስበህ ለተቀደሰው ድንኳን መንከባከቢያ እንዲውል አድርግ፤ ይህም መባ ለሕይወታቸው ቤዛ ይሆናል፤ እኔም እጠብቃቸው ዘንድ እነርሱን አስታውሳለሁ።” ከነሐስ የተሠራ መታጠቢያ ሳሕን 17 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 18 “መታጠቢያ ገንዳ ከነሐስ ሠርተህ፥ እግሮች ባሉት ከነሐስ በተሠራ የሳሕን መቀመጫ ላይ አኑረው፤ እርሱንም በመሠዊያውና በድንኳኑ መካከል አድርገህ ውሃ ጨምርበት። 19 አሮንና ልጆቹ በዚህ ውሃ እጃቸውንና እግራቸውን ለመታጠብ ይጠቀሙበት። 20 ይህንንም ማድረግ ያለባቸው ወደ ድንኳኑ ከመግባታቸውና የሚቃጠል መሥዋዕት ከማቅረባቸው በፊት ነው፤ ይህንንም ካደረጉ ከሞት ይድናሉ፤ 21 ስለዚህ እንዳይሞቱ እጃቸውንና እግራቸውን ይታጠቡ፤ ይህም እነርሱና ከእነርሱ በኋላ የሚነሡት ዘሮቻቸው ለዘለዓለም የሚጠብቁት ቋሚ ሥርዓት ነው።” የቅባት ዘይት 22 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ አለው፦ 23 “ምርጥ የሆኑ ቅመሞችን፥ ስድስት ኪሎ ግራም ፈሳሽ ከርቤ፥ ሦስት ኪሎ ግራም ጣፋጭ ሽታ ያለውን ቀረፋ፥ ሦስት ኪሎ ግራም ጣፋጭ ሽታ ያለውን የጠጅ ሣርና፥ 24 ስድስት ኪሎ ግራም ብርጒድ ውሰድ ይህም ሁሉ በተቀደሰው ድንኳን በታወቀው ሚዛን ልክ ይሁን፤ በዚህም ላይ አራት ሊትር ዘይት ጨምርበትና፥ 25 እንደ ሽቶ ቀላቅለህ የተቀደሰ የቅባት ዘይት ሥራ፤ 26 በእርሱም የመገናኛውን ድንኳንና የቃል ኪዳኑን ታቦት ትቀባለህ፤ 27 እንዲሁም ጠረጴዛውንና በእርሱ ላይ ያሉትን ዕቃዎች፥ መቅረዙንና የእርሱን ማዘጋጃ ዕቃዎች፥ የዕጣን ማዕጠንት ማቅረቢያውን መሠዊያ ትቀባለህ፤ 28 ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያገለግለውን መሠዊያና በላዩ ላይ ያሉትን ዕቃዎች ሁሉ፥ እንዲሁም የመታጠቢያውን ሳሕንና ማስቀመጫውን ትቀባለህ። 29 በዚህ ዐይነት እነዚህን ሁሉ በመለየት ፍጹም የተቀደሱ ታደርጋቸዋለህ፤ እነርሱንም ፍጹም ቅዱሳን ስለ ሆኑ ሰውም ሆነ ሌላ ነገር ቢነካቸው ቅሥፈት ይደርስበታል። 30 ከዚህ በኋላ አሮንና ልጆቹ በክህነት ያገለግሉኝ ዘንድ በመቀባት እንዲካኑ አድርግ፤ 31 ለእስራኤልም ሕዝብ እንዲህ ብለህ ንገራቸው፤ ‘ይህ የተቀደሰ የቅባት ዘይት ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ ለእኔ አገልግሎት ይዋል፤ 32 በማንኛውም ተራ ሰው ላይ አይፍሰስ፤ ይህንንም የመሰለ ቅባት ለመሥራት በዚህ ዘዴ ከመጠቀም ተጠንቀቁ፤ ቅዱስ ስለ ሆነ እናንተም ቅድስናውን ዕወቁ። 33 ይህን የመሰለ ቅባት የሚሠራ ወይም ከዚህ ቅባት ወስዶ ካህን ያልሆነውን ሰው የሚቀባ ከሕዝቤ መካከል ይወገዳል።’ ” የዕጣን ዝግጅት 34 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የእያንዳንዳቸው ሚዛን እኩል የሆነ ጣፋጭ ቅመሞችን ይኸውም የሚንጠባጠብ ፈሳሽነት ያለው ሙጫ፥ በዛጎል ውስጥ የሚገኝ ሽቱ፥ የሚሸት ሙጫና ጣፋጭ ሽታ ያለው ዕጣን ወስደህ፥ 35 እንደ ሽቶ የተቀላቀለ ዕጣን አድርገህ ተጠቀምባቸው። ንጹሕና ቅዱስ ይሆንም ዘንድ ጨው ጨምርበት። 36 ከእርሱም ጥቂቱን ወስደህ በመውቀጥ ካላምከው በኋላ ወደ ድንኳኑ ወስደህ በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት እርጨው፤ ይህንንም ዕጣን ፍጹም የተቀደሰ እንዲሆን አድርግ። 37 በዚህ ዐይነት የምታደባልቁትን ዕጣን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ አድርጉት እንጂ ለራሳችሁ መጠቀሚያ አታድርጉት። 38 ይህን የመሰለ ነገር ሠርቶ በመዓዛው ሊደሰት የሚፈልግ ሰው ቢኖር፥ ከሕዝቤ መካከል ይወገዳል።” |