ዘፀአት 29 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምስለ ክህነት ሥልጣን ለአሮንና ለልጆቹ የተሰጠ መመሪያ ( ዘሌ. 8፥1-36 ) 1 “አሮንና ልጆቹ ካህናት ሆነው በፊቴ ያገለግሉኝ ዘንድ ለመለየት የምታደርገው ይህ ነው፤ ምንም ነውር የሌለባቸውን አንድ ወይፈንና ሁለት የበግ አውራዎችን ውሰድ፤ 2 እርሾ ያልነካው ምርጥ የሆነ የስንዴ ዱቄት ወስደህ የወይራ ዘይት በመጨመር ቂጣ አዘጋጅ፤ እንዲሁም ዘይት ያልገባበት ሌላ ቂጣ አዘጋጅ፤ ሌላ ስስ ቂጣም ጋግረህ ዘይት ቀባው፤ 3 ሁሉንም በመሶብ አኑረህ ኰርማና ሁለቱን የበግ አውራዎች በምትሠዋበት ጊዜ ለእኔ መባ አድርገህ አቅርብልኝ። 4 “አሮንንና ልጆቹን እኔ ወደምመለክበት ድንኳን ደጃፍ አምጥተህ በውሃ እንዲታጠቡ ንገራቸው። 5 ከዚህ በኋላ አሮንን የክህነት ልብስ አልብሰው፤ ሸሚዙን፥ ኤፉዱን፥ የኤፉዱን መደረቢያ ቀሚስ፥ የደረት ኪሱን አልብሰው፤ መታጠቂያውን አስታጥቀው፤ 6 በራሱም ላይ መጠምጠሚያውን አኑር፤ በመጠምጠሚያውም ላይ የተቀደሰውን አክሊል አድርግለት። 7 የቅባት ዘይቱንም ወስደህ በራሱ ላይ በማፍሰስ ቀባው፤ 8 “ልጆቹንም አቅርበህ ሸሚዝ አልብሳቸው፤ 9 ለወገባቸውም መታጠቂያ አድርግላቸው፤ በራሳቸውም ላይ ቆብ ድፋላቸው፤ ክህነታቸው ለዘለዓለም ቋሚ ሥርዓት ይሆናል፤ በዚህም ዐይነት አሮንንና ልጆቹን ትሾማለህ። 10 “ኰርማውን ወደ ድንኳኑ ፊት ለፊት አምጥተህ፥ አሮንና ልጆቹ እጃቸውን በራሱ ላይ እንዲጭኑበት አድርግ። 11 ኰርማውን በድንኳኑ ደጃፍ በእኔ በእግዚአብሔር ፊት ዕረደው። 12 ከኰርማው ደም ጣትህን ነክረህ የመሠዊያውን ጒጦች ቀባ፤ የተረፈውንም ደም በመሠዊያው ሥር አፍስሰው። 13 ከዚህ በኋላ የሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሞራ እንደ መረብ ሆኖ ጉበቱን የሚሸፍነውን ሞራ ሁለቱን ኲላሊቶቹንና እነርሱን የሚሸፍነውን ሞራ ወስደህ በመሠዊያው ላይ አቃጥለው። 14 የኰርማውን ሥጋ፥ ቆዳውን፥ አንጀቱን ሁሉ ወስደህ ከሰፈር ውጪ አቃጥለው፤ ይህ የኃጢአት መሥዋዕት ነው። 15 “ከሁለቱ የበግ አውራዎች አንዱን ወስደህ አሮንና ልጆቹ እጃቸውን በራሱ ላይ እንዲጭኑ አድርግ። 16 እርሱንም ዐርደህ ደሙን በመሠዊያው ጐን በአራቱም ማእዘን እርጨው፤ 17 ሥጋውን በየብልቱ ቈራርጠው፤ የውስጥ ዕቃውንና የኋላ እግሮቹን በውሃ አጥበህ ከራሱና ከሌሎቹ የሥጋ ብልቶች ጋር አኑር፤ 18 ከዚያም በኋላ የአውራውን በግ ሥጋ በሙሉ ለእኔ ለእግዚአብሔር የምግብ መሥዋዕት አድርገህ አቃጥለው፤ ይህም መባ ሽታው እኔን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። 19 “ለክህነት ሥርዓት የተመደበውን ሌላውንም አውራ በግ ወስደህ አሮንና ልጆቹ እጃቸውን በራሱ ላይ እንዲጭኑበት ንገራቸው፤ 20 እርሱንም ዕረድና ከደሙ ጥቂት ወስደህ የአሮንንና የልጆቹን ቀኝ ጆሮዎች ጫፍ፥ የቀኝ እጃቸውንና የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት ትቀባለህ፤ የተረፈውንም ደም በመሠዊያው ጐን በአራቱም ማእዘን ርጨው። 21 በመሠዊያው ላይ ካለው ደም ጥቂት፥ ከቅባቱም ዘይት ጥቂት ወስደህ በአሮንና በልብሱ ላይ በአሮን ልጆችና በልብሶቻቸው ላይ ርጨው፤ በዚህ ዐይነት እርሱና ልጆቹ ከነልብሶቻቸው ለእኔ የተለዩ ይሆናሉ። 22 “የሚካኑበት ስለ ሆነ የአውራውን በግ ሞራ ላቱን፥ የውስጥ ዕቃውን የሚሸፍነውን ሞራ፥ እንደ መረብ ሆኖ ጉበቱን ከሚሸፍነው ሞራ የተሻለውን ክፍል፥ ሁለቱን ኲላሊቶቹን፥ እነርሱን የሚሸፍነውን ሞራና በቀኝ በኩል ያለውን የኋላ እግር ቈርጠህ ለያቸው። 23 በመሶብ ሆኖ ለእኔ ለእግዚአብሔር ከቀረበው ቂጣ ከየአንዳንዱ ዐይነት አንድ ሙልሙል ውሰድ፤ ይኸውም ዘይት ተጨምሮበት ከተጋገረው አንድ፥ ዘይት ካልገባበትም አንድ፥ እንዲሁም ሌላ አንድ ስስ ቂጣ ጨምረህ ትወስዳለህ ማለት ነው። 24 ይህን ሁሉ ምግብ በአሮንና በልጆቹ እጅ ላይ አኑር፤ እርሱንም ወዝውዘው ለእኔ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መሥዋዕት አድርገው ያቅርቡት። 25 ከእነርሱም በመቀበል ለእኔ የምግብ መባ አድርገህ ታቀርበው ዘንድ በሚቃጠለው መሥዋዕት ጫፍ ላይ አኑረህ በመሠዊያው ላይ አቃጥለው፤ ይህም መባ መዓዛው እኔን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። 26 “ለአሮን ክህነት ሥርዓት ከታረደው የበግ አውራ ፍርምባውን ወስደህ ለእኔ ለእግዚአብሔር በመወዝወዝ የሚቀርብ መባ አድርገህ አንሣ፤ ይህም ለእናንተው የሚመደብ ድርሻ ይሆናል። 27 “አሮንና ልጆቹ ከሚካኑበት አውራ በግ ተወስዶ ለመሥዋዕት የተወዘወዘውን ፍርምባና የተነሣውን ወርች ትቀድሳለህ። እርሱም ተመልሶ ለካህናቱ የሚመደብ ድርሻ ይሆናል። 28 ሕዝቤ የአንድነት መሥዋዕት በሚያቀርብበት ጊዜ የእንስሳው ፍርምባና በቀኝ በኩል ያለውን የኋላ እግር ለአሮንና ለልጆቹ ድርሻ ሆኖ እንዲመደብ ወስኛለሁ፤ ውሳኔውም ቋሚ ሥርዓት ይሆናል፤ ይህ እንግዲህ ሕዝቡ ለእኔ ለእግዚአብሔር የሚያቀርበው መባ ነው። 29 “አሮን በሚሞትበት ጊዜ የክህነት ልብሶቹ ለልጆቹ ይተላለፉ፤ እነርሱም ተቀብተው የክህነት ሥልጣን በሚቀበሉበት ጊዜ ይልበሱት። 30 የክህነቱ ሥልጣን ወራሽ በመሆን በተቀደሰው ስፍራ እኔን ለማገልገል ካህን ሆኖ ወደ ቅዱሱ ድንኳኔ የሚገባው የአሮን ልጅ እነዚህን ልብሶች ለሰባት ቀን ይልበስ። 31 “አሮንና ልጆቹ የክህነት ሥልጣን በሚቀበሉበት ጊዜ የታረደውን የአውራ በግ ሥጋ ወስደህ በተቀደሰ ስፍራ ቀቅለው። 32 ይህንንም ሥጋ በመሶብ ውስጥ ተርፎ ከቀረው ቂጣ ጋር በቅዱሱ ድንኳኔ ደጃፍ ሆነው ይብሉት። 33 የክህነት ሥልጣን ሲቀበሉ ስለ ኃጢአት ይቅርታ የተሠዋውንም ይብሉ። ይህ ምግብ የተቀደሰ ስለ ሆነ ካህናት ብቻ ይብሉት። 34 ከሥጋውም ሆነ ከኅብስቱ ሳይበላ ተርፎ ያደረ ቢኖር በእሳት ይቃጠል፤ የተቀደሰ ስለ ሆነም መበላት የለበትም። 35 “አሮንና ልጆቹ የክህነት ሥልጣን የሚቀበሉበትን ሥርዓት ልክ እኔ ባዘዝኩህ መሠረት ለሰባት ቀን ፈጽም። 36 ስለ ኃጢአትም ይቅርታ በእያንዳንዱ ቀን አንድ ኰርማ መሥዋዕት አድርገህ አቅርብ፤ ይህም መሠዊያውን ያነጻል፤ የተቀደሰም ይሆን ዘንድ የወይራ ዘይት ቀባው። 37 ይህንንም ለሰባት ቀን በየዕለቱ አድርግ፤ በዚህም ዐይነት መሠዊያው ፍጹም የተቀደሰ ይሆናል፤ የተቀደሰም ስለ ሆነ፥ ሰውም ሆነ ሌላ ነገር እርሱን ቢነካ በቅድስናው ኀይል ቅሥፈት ይደርስበታል። የሠርክ መሥዋዕት ( ዘኍ. 28፥1-8 ) 38 “በሚመጡት ዘመናት ሁሉ በየዕለቱ አንድ ዓመት የሆናቸው ሁለት ጠቦቶች መሥዋዕት አድርገህ በመሠዊያው ላይ ታቀርባለህ፤ 39 ከጠቦቶቹ አንዱን ጠዋት ሌላውን ማታ ትሠዋለህ። 40 ከመጀመሪያው ጠቦት ጋር አንድ ኪሎ ግራም ምርጥ የሆነ የስንዴ ዱቄት ከአንድ ሊትር ተጨምቆ የተጠለለ የወይራ ዘይት ጋር ለውሰህ አቅርብ፤ አንድ ሊትር የወይን ጠጅም መባ አድርገህ አፍስስበት። 41 ሁለተኛውንም ጠቦት በምሽት ጊዜ መሥዋዕት አድርገህ አቅርብ፤ በማለዳው መሥዋዕት ባቀረብከውም መጠን ተመሳሳይ ዱቄት፥ ዘይትና ወይን ጠጅ አቅርብ፤ ይህ ለእኔ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ የምግብ መባ ነው፤ መዓዛውም እኔን ደስ የሚያሰኝ ይሆናል። 42 ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ ይህ የሚቃጠል መሥዋዕት በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ መቅረብ አለበት፤ እኔ ሕዝቤን የምገናኘውና አንተንም የማነጋግርበት ስፍራ ይኸው ነው። 43 በዚህም ከሕዝቤ ከእስራኤል ጋር እገናኛለሁ፤ ክብሬም ይህን ስፍራ የተቀደሰ ያደርገዋል። 44 እኔ መሠዊያውንና ድንኳኑን እቀድሳለሁ፤ በክህነት ያገለግሉኝም ዘንድ አሮንንና ልጆቹን እለያለሁ። 45 በእስራኤል ሕዝብ መካከል እኖራለሁ፤ አምላካቸውም እሆናለሁ፤ 46 በመካከላቸው እኖር ዘንድ ከግብጽ ምድር መርቼ ያወጣኋቸው እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው መሆኔን ያውቃሉ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ነኝ። |