Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 28 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ልብሰ ተክህኖ
( ዘፀ. 39፥1-7 )

1 “ወንድምህን አሮንንና ልጆቹን ናዳብን፥ አቢሁን፥ አልዓዛርንና ኢታማርን ወደ አንተ አቅርብ፤ ካህናት ሆነው ያገለግሉኝም ዘንድ ከእስራኤል ሕዝብ መካከል ለያቸው።

2 ለክብርና ለውበት ይሆነው ዘንድ ለወንድምህ ለአሮን የክህነት ልብስ ሥራለት።

3 እኔ ልዩ ችሎታ እንዲኖራቸው ያደረግኋቸውን የእጅ ጥበብ ዐዋቂዎችን ጠርተህ ለአሮን ልብስ እንዲሠሩለት ንገራቸው፤ በዚህ ዐይነት አሮን ካህን በመሆን ያገለግለኝ ዘንድ ለእኔ የተለየ ይሆናል።

4 በዐይነት የሚሠሩአቸውም ልብሶች እነዚህ ናቸው፤ የደረት ኪስ፥ ኤፉድ፥ ቀሚስ፥ በጥልፍ ያጌጠ ሸሚዝ፥ ጥምጥምና መታጠቂያ፤ ወንድምህ አሮንና ልጆቹ ካህናት ሆነው ያገለግሉኝ ዘንድ እነዚህን የተቀደሱ ልብሶች ይሥሩላቸው።

5 ጥበበኞቹም ልብሶቹን ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ፥ ከቀይ ከፈይ ከወርቅ ምዝምዝና ከጥሩ በፍታ በጥልፍ አስጊጠው ይሥሩ።

6 “ኤፉድንም ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊ ከቀይ ከፈይ ከወርቅ ምዝምዝና ከጥሩ በፍታ በጥልፍ አስጊጠው ይሥሩ።

7 ሁለቱ ወገን አንድ እንዲሆን በሁለቱ ትከሻ ላይ የሚጋጠም የጥብጣብ ዐይነት ማንገቻ ይኑር።

8 ኤፉዱ ከተሠራባቸው ተመሳሳይ ነገሮች በብልኀት የተጠለፈ መታጠቂያ አንድ ላይ እንደ ተሠራ ሆኖ ከኤፉዱ ጋር ይጣበቅ።

9 ሁለትም የመረግድ ድንጋይ ወስደህ የዐሥራ ሁለቱን የያዕቆብ ልጆች ስም ቅረጽባቸው፤

10 ይኸውም የልደታቸውን ቅደም ተከተል ሳታፋልስ ስድስቱን በአንድ ድንጋይ ላይ፥ ስድስቱንም በሌላ ድንጋይ ላይ ጻፍ።

11 በሁለቱ ድንጋዮች ላይ የዐሥራ ሁለቱን የያዕቆብ ልጆች ስሞች ለመቅረጽም ችሎታ ያለው ብልኅ ሰው አግኝ፤ ድንጋዮቹንም ከወርቅ በተሠራ ፈርጥ ላይ አኑራቸው።

12 ለዐሥራ ሁለቱ የእስራኤል ነገዶች መታሰቢያ ይሆኑ ዘንድ ሁለቱን ዕንቆች በትከሻ ላይ በሚያልፉት የኤፉድ ማንገቻዎች ላይ ታደርጋቸዋለህ። በዚህ ዐይነት እኔ እግዚአብሔር ዘወትር ሕዝቤን አስታውስ ዘንድ አሮን የእነርሱን ስሞች በትከሻው ይሸከማል።

13 ሁለት የወርቅ ፈርጦች ሥራ፤

14 እንደ ገመድ ተጐንጒነው ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ሁለት ድሪዎችንም አበጅተህ ከሁለቱ ፈርጦች ጋር እንዲያያዙ አድርግ።


የደረት ኪስ
( ዘፀ. 39፥8-21 )

15 “የእግዚአብሔር ፈቃድ የሚጠየቅበትን የደረት ኪስ ለሊቀ ካህናቱ ሥራ፤ አሠራሩ እንደ ኤፉድ ሆኖ በተመሳሳይ ጥልፍ ያጌጠ ይሁን።

16 ርዝመቱ ኻያ ሁለት ሳንቲ ሜትር የጐኑም ስፋት ኻያ ሁለት ሳንቲ ሜትር ሆኖ ታጥፎ የተደረበ ትክክል አራት ማእዘን ይሁን።

17 አራት ረድፍ የሆነ የዕንቊ ፈርጥ አድርግበት፤ በመጀመሪያው ረድፍ ሰርድዮን፥ ቶጳዝዮንና፥ የሚያብረቀርቅ ዕንቊ፥ 18

18 በሁለተኛው ረድፍ በሉር፥ ሰንፔርና መረግድ፤

19 በሦስተኛው ረድፍ ያክንት፥ ኬልቄዶንና አሜቲስጦስ፥

20 በአራተኛው ረድፍ ቢረሌ፥ መረግድና ኢያስጲድ በወርቅ ፈርጥ ላይ ይቀመጣሉ።

21 ለእስራኤል ነገዶች መታሰቢያ ይሆኑ ዘንድ ከእነዚህ ዐሥራ ሁለት የዕንቊ ድንጋዮች በእያንዳንዱ ላይ ከያዕቆብ ልጆች የአንዱ ስም ይቀረጽበታል።

22 ለደረት ኪሱም እንደ ገመድ የተጐነጐነ ድሪ ከንጹሕ ወርቅ ሥራ።

23 ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠርተህ በደረት ኪሱ ከላይኛው ማእዘን በኩል እንዲጋጠሙ አድርግ።

24 ሁለቱን የወርቅ ድሪዎች ከሁለቱ ቀለበቶች ጋር አያይዛቸው።

25 በሌላ በኩል ያሉትንም የሁለቱን ድሪዎች ጫፎች ከሁለቱ ፈርጦች ጋር አገናኛቸው፤ በዚህም ዐይነት ከፊት ለፊት በኩል በትከሻ ላይ ከሚወርዱት ከኤፉዱ ማንገቻዎች ጋር ታያይዛቸዋለህ፤

26 እንደገናም ሁለት የወርቅ ቀለበቶች ሠርተህ በውስጥ በኩል ከኤፉዱ ቀጥሎ ባለው የደረት ኪስ ከታችኛዎቹ ማእዘኖች ጋር እንዲገጣጠሙ አድርግ።

27 ከነዚህም ሌላ ሁለት ተጨማሪ የወርቅ ቀለበቶች ሠርተህ ከፊት ለፊት በኩል በትከሻ ላይ ከሚወርዱት ከኤፉዱ ማንገቻዎች ጋር ከታች በኩል ታያይዘዋለህ፤ መያያዝ ያለበትም በስፌቱ መጋጠሚያ አጠገብና በብልኀት ከተጠለፈው መታጠቂያ በላይ በኩል ነው።

28 በደረት ኪሱ ላይ ያሉትን ቀለበቶች በኤፉዱ ላይ ካሉት ቀለበቶች ጋር በሰማያዊ ድሪ እሰራቸው፤ በዚህ ዐይነት የደረት ኪሱ ከመታጠቂያው በላይ ስለሚሆን ልል አይሆንም።

29 “አሮን ወደ ተቀደሰው ስፍራ ሲገባ የእስራኤል ነገዶች ስሞች የተቀረጹበትን ይህን የደረት ኪስ ይለብሳል፤ በዚህ ዐይነት እኔ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ሕዝቤን አስታውሳለሁ።

30 ዑሪምና ቱሚም የተባሉትን ነገሮች በደረት ኪሱ ውስጥ ታስገባቸዋለህ፤ አሮንም ወደ ቅዱሱ ድንኳን ሲገባ በደረት ኪሱ ተሸክሞአቸው ይግባ፤ የእኔን ፈቃድ ለእስራኤል ሕዝብ ማስታወቅ ይችል ዘንድ በፊቴ ለማገልገል በሚገባበት ጊዜ ሁሉ በደረት ኪሱ ያድርጋቸው።


ሌሎች የክህነት አልባሳት
( ዘፀ. 39፥22-31 )

31 “በኤፉዱ መደረቢያ ቀሚስ ሙሉ በሙሉ ከሰማያዊ በፍታ የተሠራ ይሁን፤

32 የራስ ማጥለቂያ አንገትጌም ይኑረው፤ ይህም አንገትጌ እንዳይተረተር ወደ ውስጥ ታጥፎ በእጅ ሥራ የተቀመቀመ ይሁን።

33 በታችኛው ዘርፍ ዙሪያ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ የተሠሩ የሮማን ፍሬ ቅርጽ አድርግበት፤ በፍሬዎቹ መካከል ጣልቃ የሚገቡ ከወርቅ የተሠሩ ትናንሽ ቃጭሎች አድርግበት።

34 ሮማን የመሰለውና የወርቅ መርገፍ በቀሚሱ ዘርፍ ዙሪያውን ተከታትለው ይደረጋሉ።

35 አሮን በክህነት በሚያገለግልበት ጊዜ ይህን ቀሚስ ይልበስ፤ በተቀደሰው ስፍራ በፊቴ በተገኘ ጊዜ ወይም ከዚያ በሚወጣበት ጊዜ የመርገፉ ድምፅ ስለሚሰማ ከመሞት ይድናል።

36 “ከንጹሕ ወርቅ አንድ ጌጥ ሥራና በላዩ ላይ ‘ለእግዚአብሔር የተለየ’ የሚል ቃል ቅረጽበት።

37 በመጠምጠሚያውም ፊት በሰማያዊ ድሪ እንዲንጠለጠል አድርግ፤

38 አሮንም በግንባሩ ላይ ያድርገው፤ በዚህ ዐይነት ባቀራረብ እንኳ ስሕተት ቢፈጽሙ እስራኤላውያን የሚያቀርቡልኝን መባ ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እቀበላቸዋለሁ።

39 “የአሮንን ሸሚዝና መጠምጠሚያ ከጥሩ በፍታ ሥራው፤ መታጠቂያውም ከጥሩ በፍታ ተሠርቶ በጥልፍ ጥበብ ያጌጠ ይሁን።

40 “ለአሮንም ልጆች ክብርና ውበት ይሆንላቸው ዘንድ ሸሚዞችን፥ መታጠቂያዎችንና ቆቦችን ሥራላቸው።

41 እንግዲህ እነዚህን ልብሶች ለወንድምህ ለአሮንና ለልጆቹ አልብሳቸው፤ በክህነት ያገለግሉኝም ዘንድ የወይራ ዘይት በመቀባት የክህነትን ማዕርግ ትሰጣቸዋለህ፤ ትቀድሳቸዋለህም፤

42 የውስጥ ሰውነታቸው እንዳይጋለጥ ከጥሩ በፍታ፥ ከወገባቸው እስከ ጭናቸው የሚደርስ ቊምጣ ሱሪ ትሠራላቸዋለህ፤

43 አሮንና ልጆቹ ዘወትር ወደ ድንኳን ሲገቡ ወይም በተቀደሰው ስፍራ በክህነት ለማገልገል ወደ መሠዊያው ሲቀርቡ ይለብሱታል፥ በዚህ ዐይነት የውስጥ ሰውነታቸው ስለማይጋለጥ ከሞት ይድናሉ፤ ይህ እንግዲህ ለአሮንና ለትውልዱ ሁሉ ጸንቶ የሚኖር ሥርዓት ነው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告