ዘፀአት 27 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየመሠዊያው አሠራር ( ዘፀ. 38፥1-7 ) 1 “ከግራር እንጨት መሠዊያ ሥራ፤ ርዝመቱ ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር የጐኑ ስፋት ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ቁመቱም አንድ ሜትር ከሠላሳ ሳንቲ ሜትር ይሁን። 2 በአራቱም ማእዘን ጫፍ ላይ ጠርበህ ቀንድ መሳይ ጒጦች አውጣ፤ ይህም ከመሠዊያው ጋር አብሮ የተሠራ ይሁን፤ እርሱም በነሐስ የተለበጠ ይሁን። 3 ዐመድ የሚጠራቀምባቸውን ድስቶችን፥ የእሳት መጫሪያዎችን፥ ጐድጓዳ ሳሕኖችን፥ ሜንጦዎችንና ማንደጃዎችን አዘጋጅ፤ ሁሉም ከነሐስ የተሠሩ ይሁኑ። 4 እንደ መረብ ሆኖ የተሠራ የነሐስ መከላከያ አብጅለት፤ ለመከላከያውም አራት የነሐስ ቀለበቶች በአራቱም ማእዘን አድርግለት። 5 መከላከያም እስከ መሠዊያው እኩሌታ እንዲደርስ ከመሠዊያው ክፈፍ በታች አድርገው፤ 6 ለመሠዊያው መሸከሚያ የሚሆኑ መሎጊያዎችንም ከግራር እንጨት ሠርተህ በነሐስ ለብጣቸው። 7 መሠዊያውን መሸከም በሚያስፈልግበትም ጊዜ መሎጊያዎቹን ከመሠዊያው በእያንዳንዱ ጐን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አግባ። 8 በተራራው ላይ ባሳየሁህ ዕቅድ መሠረት መሠዊያውን ከሳንቃዎች ሥራ፤ ውስጡም ባዶ ይሁን። የድንኳኑ አደባባይ ክልል ( ዘፀ. 38፥9-20 ) 9 “ለድንኳኑ አደባባይ ክልል መጋረጃዎች ከቀጭን ሐር ሥራ፤ የመጋረጃዎቹም ርዝመት ከደቡብ በኩል አርባ አራት ሜትር ይሁን፤ 10 ለእርሱም መደገፊያ ኻያ የነሐስ እግሮች ያላቸው ኻያ ምሰሶዎች ሥራ፤ በእነርሱም ላይ ከብር የተሠሩ ዘንጎችና ኩላቦች ይኑሩ፤ 11 በስተ ሰሜን በኩል ላለውም አደባባይ ልክ በዚሁ ዐይነት ይሠራ። 12 በምዕራብ በኩል አደባባይ ዐሥር እግሮች ካሉአቸው ዐሥር ምሰሶዎች ጋር ርዝመታቸው ኻያ ሁለት ሜትር የሚሆን መጋረጃዎች ይኑሩት። 13 የመግቢያው በር ባለበት በምሥራቅ በኩል የአደባባዩ ስፋት ኻያ ሁለት ሜትር ይሁን። 14 በበሩ በአንድ በኩል ያለው መጋረጃ ስድስት ሜትር ከስድሳ ሳንቲ ሜትር ሲሆን ሦስት ምሰሶዎች ከሦስት እግር ጋር ይሁኑ። 15 በሌላው በኩል ያለውም መጋረጃ እንደዚሁ ይሁን። 16 ለአደባባዩ በር ርዝመታቸው ዘጠኝ ሜትር የሆነ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ የተሠራ በጥልፍ ያጌጠ መጋረጃ ይኑረው፤ የሚደግፉትም አራት እግሮች ያሉአቸው አራት ምሰሶዎች ይኑሩት። 17 በአደባባዩ ዙሪያ ያሉት ምሰሶዎች ሁሉ በብር ዘንጎች ይያያዙ፤ ኲላቦቻቸው ከብር፥ እግሮቻቸውም ከነሐስ የተሠሩ ይሁኑ። 18 የድንኳኑ አደባባይ ርዝመቱ አርባ አራት ሜትር የጐኑ ስፋት ኻያ ሁለት ሜትር፥ ከፍታውም ሁለት ሜትር ከኻያ ሳንቲ ሜትር ይሁን፤ መጋረጃዎቹ ከጥሩ በፍታ የተሠሩ ሆነው የነሐስ እግሮች ይኑሩአቸው። 19 በድንኳኑ ውስጥ የሚገኙት ለማናቸውም ጥቅም የሚውሉ የመገልገያ ዕቃዎች ሁሉ፥ የድንኳኑና የአደባባዩ ካስማዎች ሁሉ ከነሐስ የተሠሩ ይሁኑ። ስለ መብራት የሚደረግ ጥንቃቄ ( ዘሌ. 24፥1-4 ) 20 “መብራቱ በየምሽቱ ሲበራ እንዲኖር ለመብራት የሚሆነውን ተጨምቆ የተጠለለ ምርጥ የወይራ ዘይት ያመጡልህ ዘንድ የእስራኤልን ሕዝብ እዘዝ፤ 21 አሮንና ልጆቹ ከምሽት እስከ ንጋት ይበራ ዘንድ የእግዚአብሔር መገኛ ከሆነው ፊት ከቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት ለፊት ካለው መጋረጃ ውጪ ያኑሩት፤ ይህም በእስራኤል ሕዝብና ወደፊትም በሚነሣው ትውልድ ዘንድ ቋሚ ሥርዓት ሆኖ ይኑር። |