Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 26 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የተቀደሰው ድንኳን
( ዘፀ. 36፥8-38 )

1 “እንዲሁም የተቀደሰውን ድንኳን ውስጠኛ ክፍል ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ ከተፈተለ በፍታ በተሠሩ ዐሥር መጋረጃዎች አብጀው፤ በእነርሱም ላይ ኪሩቤል በጥልፍ ጥበብ እንዲሳሉ አድርግ።

2 እያንዳንዱ መጋረጃ ርዝመቱ ዐሥራ ሁለት ሜትር የጐኑ ስፋት ሁለት ሜትር ሆኖ ሁሉም እኩል ይሁኑ።

3 አምስቱ መጋረጃዎች እርስ በርሳቸው የተገጣጠሙ ይሁኑ፤ ሌሎቹም አምስቱ መጋረጃዎች እርስ በርሳቸው በመገጣጠም ተሰፍተው በሌላ በኩል ይሁኑ።

4 ተገጣጥመው በተሠሩት በሁለቱም መጋረጃዎች በየአንዳንዱ ጠርዝ ላይ ከሰማያዊ ጨርቅ የተሠሩ ቀለበቶችን አድርግ።

5 በመጀመሪያው መጋረጃ መጀመሪያ ክፍል ላይ ኀምሳ ቀለበቶች፥ በሁለተኛው መጋረጃ መጨረሻ ክፍል ላይ ከሌሎቹ ቀለበቶች ፊት ለፊት ኀምሳ ቀለበቶች አድርግ።

6 የተቀደሰው ድንኳን አንድ ይሆን ዘንድ ለእነዚህ ሁለት ክፍሎች ኀምሳ የወርቅ መያዣዎችን ሠርተህ በቀለበቶቹ አገጣጥማቸው።።

7 “ከፍየል ጠጒር የተሠሩ ዐሥራ አንድ መጋረጃዎችን ለድንኳኑ ክዳን አድርግ።

8 የእያንዳንዱ ርዝመት ዐሥራ ሦስት ሜትር፥ የጐኑም ስፋት ሁለት ሜትር ሆኖ የሁሉም መጠን እኩል ይሁን።

9 አምስቱን በአንድ በኩል፥ ስድስቱን በሌላ በኩል አድርገህ በአንድነት በማጋጠም ስፋቸው፤ ስድስተኛው መጋረጃ ታጥፎ ከፊት በኩል በድንኳኑ ላይ ይደረብ።

10 በአንድ በኩል ካለው መጋረጃ መጨረሻ ክፍል ጠርዝ ላይ ኀምሳ ቀለበቶች፥ በሌላም በኩል ካለው መጋረጃ መጨረሻ ጠርዝ ላይ ኀምሳ ቀለበቶች አድርግ።

11 በቀለበቶቹም ውስጥ ኀምሳ የነሐስ መያዣዎችን አስገባ፤ በዚህም ዐይነት ሁለቱን ክፍሎች በማገጣጠም አንድ ክዳን እንዲሆኑ አድርግ።

12 ትርፍ የሆነውን ግማሽ መጋረጃ ወስደህ በድንኳኑ ጀርባ አንጠልጥለው።

13 በርዝመቱ በኩል ከእያንዳንዱ መጋረጃ ትርፍ ሆነው የቀሩት ግማሽ ሜትር ስፋት ያላቸው መጋረጃዎች በጐንና ጐን ተንጠልጥለው ድንኳኑን ይሸፍኑት።

14 “ለውጪው ክዳን ይሆኑ ዘንድ፥ አንደኛው ቀይ ቀለም ከተነከረ አውራ በግ ቆዳ፥ ሌላው ከተለፋ የፍየል ቆዳ ሁለት ተጨማሪ ክዳኖችን ሥራ።

15 “ድንኳኑን የሚደግፉ ቋሚ ተራዳዎች ከግራር እንጨት ሥራ።

16 እያንዳንዱ ተራዳ ርዝመቱ አራት ሜትር፥ የጐኑም ስፋት ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር ይሁን።

17 የተራዳ ሁለት ሳንቃዎች መገጣጠም ይችሉ ዘንድ ለእያንዳንዱ ተራዳ ማያያዣዎች ይኑሩት። ለማደሪያው ተራዳዎችም ሁሉ እንዲሁ አድርግ።

18 ከድንኳኑ በስተ ደቡብ በኩል ኻያ ተራዳዎችን አድርግ፤

19 በእነርሱም ሥር አርባ የብር እግሮችን አድርግ፤ ሁለቱን ተራዳዎች ለማያያዝ እንዲረዱ እያንዳንዱ ተራዳ ሁለት እግሮች ይኑሩት።

20 ከድንኳኑ በስተ ሰሜን በኩል ኻያ ተራዳዎችን አድርግ፤

21 በእያንዳንዱ ተራዳ ሥር ሁለት እግሮችን በመሥራት አርባ እግሮች እንዲኖሩአቸው አድርግ።

22 በድንኳኑ በስተ ጀርባ ባለው በምዕራብ በኩል፥ ስድስት ተራዳዎችን አድርግ።

23 ለማእዘኖቹም ሁለት ተራዳዎች አድርግ።

24 እነዚህ በማእዘኖቹ ላይ ያሉት ተራዳዎች ከታች በኩል ተጣምረው እስከ ላይ አንደኛው ዋልታ መያያዝ አለባቸው፤ ሁለቱን ማእዘኖች የሚያገናኙት ሁለት ተራዳዎች በዚሁ ዐይነት ይሠሩ።

25 በዚህ ዐይነት በእያንዳንዱ ተራዳ ሥር ሁለት እግር ሆኖ ዐሥራ ስድስት የብር እግሮች ያሉአቸው ስምንት ተራዳዎች ይኖራሉ።

26 “ዐሥራ አምስት መወርወሪያዎች ከግራር እንጨት ሥራ፤ ከእነርሱም አምስቱ ከድንኳኑ በአንድ ጐን ላሉት ተራዳዎች

27 አምስቱም በሌላው ጐን ላሉት ተራዳዎች የቀሩት አምስቱ ደግሞ በስተ ምዕራብ ከኋላ በኩል ላሉት ተራዳዎች ይሆናሉ።

28 መካከለኛውም መወርወሪያ በተራዳዎች መካከል ከዳር እስከ ዳር ይለፍ።

29 ተራዳዎችንም በወርቅ ለብጣቸው፤ ለመወርወሪያዎቹም መያዣ እንዲሆኑ የወርቅ ዋልታዎች አብጅላቸው፤ መወርወሪያዎቹም በወርቅ የተለበጡ ይሁኑ፤

30 ድንኳኑን በተራራው ላይ ባሳየሁህ ዕቅድ መሠረት ትከል።

31 “ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ ከተፈተለ በፍታ መጋረጃን ሥራ፤ በእርሱም ላይ ኪሩቤል፥ በጥልፍ ጥበብ እንዲሳሉ አድርግ።

32 እርሱንም ከግራር እንጨት ተሠርተው በወርቅ በተለበጡት፥ ኩላቦችና አራት የብር እግሮች ባሉአቸው ምሰሶዎች ላይ ስቀለው።

33 መጋረጃውንም በድንኳኑ ጣራ ላይ በተርታ በተደረደሩት መያዣዎች ሥር ታንጠለጥለዋለህ፤ ሁለቱን የድንጋይ ጽላቶች የያዘውንም የቃል ኪዳን ታቦት ከመጋረጃው በስተኋላ በኩል ታኖረዋለህ፤ በዚህ ዐይነት መጋረጃው ቅድስት የተባለውን ስፍራ ከቅድስተ ቅዱሳኑ ይለያል፤

34 ከዚህ በኋላ የቃል ኪዳኑን ታቦት በስርየት መክደኛው ክደነው፤

35 ጠረጴዛውን ከቅድስተ ቅዱሳኑ ውጪ፥ ከድንኳኑ በስተ ሰሜን በኩል አኑር፤ መቅረዙንም በደቡብ በኩል አኑር።

36 “ለድንኳኑም ደጃፍ ከሰማያዊ፥ ከሐምራዊና ከቀይ ከፈይ ከተፈተለ ከጥሩ በፍታ በጥልፍ ያጌጠ መጋረጃ አድርግለት።

37 ለመጋረጃውም አምስት ምሰሶዎችን ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው፤ ኩላቦቻቸውም ከወርቅ የተሠሩ ይሁኑ፤ ለእነዚህ ምሰሶዎች ከነሐስ የተሠሩ አምስት እግሮች አብጅላቸው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告