ዘፀአት 25 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምለቤተ እግዚአብሔር የሚቀርብ ስጦታ ( ዘፀ. 35፥4-9 ) 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “ስጦታን ያመጡልኝ ዘንድ ለእስራኤላውያን ንገር፤ ማንኛውም ሰው በፈቃዱ የሚያመጣውን መባ ሁሉ ተቀበል። 3 የስጦታውም ዐይነት ይህ ነው፦ ወርቅ፥ ብር፥ ነሐስ፥ 4 ሰማያዊና ሐምራዊ፥ ቀይም ከፈይ፥ ጥሩ በፍታ፥ ከፍየል ጠጒር የተሠራ ልብስ፥ 5 ተለፍቶ ቀይ ቀለም የተነከረ የአውራ በግ ቆዳ፤ የተለፋ የፍየል ቆዳ፥ የግራር እንጨት፥ 6 ለመብራት የሚሆን የወይራ ዘይት፥ ለቅባት ዘይትና ለዕጣን ሽታ የሚሆን ቅመማ ቅመም፥ 7 መረግድ፥ (ቅጠልያ ዕንቊ) በሊቀ ካህናቱ ኤፉድና በደረት ኪስ ላይ የሚደረግ ፈርጥ፥ 8 በመካከላቸውም እኖር ዘንድ ሕዝቡ ቤተ መቅደስ ይሥሩልኝ፤ 9 ድንኳኑንና በውስጡ ያሉትን ዕቃዎች ሁሉ እኔ በማሳይህ ዕቅድ መሠረት ሥሩት። የቃል ኪዳኑ ታቦት ( ዘፀ. 37፥1-9 ) 10 “ከግራር እንጨት የተሠራ አንድ ሣጥን፥ ታቦት አድርገው ይሥሩ፤ ርዝመቱ መቶ ዐሥር የጐኑ ስፋት ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር፥ ቁመቱም ስድሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር ይሁን፤ 11 ውስጡንም ውጪውንም በንጹሕ ወርቅ ለብጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አብጅለት፤ 12 አራት የወርቅ ዋልታዎችንም ሠርተህ ሁለቱን በአንድ በኩል፥ ሁለቱንም በሌላ በኩል በማድረግ ከአራቱም እግሮቹ ጋር እንዲያጣብቁ አድርግ፤ 13 ለታቦቱ መሸከሚያ የሚሆኑ መሎጊያዎችንም ከግራር እንጨት ሥራ፤ በወርቅም ለብጣቸው፤ 14 እነዚህንም መሎጊያዎች በታቦቱ አራት ማእዘን ባሉት ቀለበቶች ውስጥ አስገባ። 15 መሎጊያዎቹም በታቦቱ ቀለበቶች ውስጥ ይኑሩ፤ ከቶም ከዚያ አይውጡ። 16 ከዚህም በኋላ እኔ የምሰጥህን፥ ትእዛዞቹ የተጻፉባቸውን ሁለት ጽላቶች በታቦቱ ውስጥ አኑር። 17 “ርዝመቱ መቶ ኻያ አምስት ሳንቲ ሜትር፥ የጐኑም ስፋት ሰባ አምስት ሳንቲ ሜትር የሆነም የስርየት መክደኛ ሥራለት። 18 ከተቀጠቀጠም ወርቅ ክንፎች ያሉአቸው የሁለት ኪሩቤል ምስል ሥራ፤ 19 በስርየት መክደኛውም ላይ በሁለት በኩል በጫፍና በጫፍ አኑራቸው፤ እነርሱም ከክዳኑ ጋር አብረው የተሠሩ ይሁኑ። 20 እነዚህም ክንፍ ያላቸው ኪሩቤል በመክደኛው ግራና ቀኝ ሆነው ፊት ለፊት የሚተያዩ ይሁኑ፤ በተዘረጉትም ክንፎቻቸው መክደኛውን ይሸፍኑት። 21 በታቦቱ ላይ መክደኛውን አድርግ፤ የምሰጥህንም ጽላት በታቦቱ ውስጥ አኑረው፤ 22 እኔም በዚያ ለአንተ እገለጥልሃለሁ፤ በመክደኛው ላይ በተሠሩት ክንፍ ባላቸው በሁለቱ ኪሩቤል መካከል ሆኜ ለእስራኤል ሕዝብ የምታቀርበውን ትእዛዞቼን ሁሉ እሰጥሃለሁ። ለእግዚአብሔር መባ ሆኖ የሚቀርበው ኅብስት ማኖሪያ ጠረጴዛ ( ዘፀ. 37፥10-16 ) 23 “ርዝመቱ ሰማኒያ ስምንት ሳንቲ ሜትር፥ የጐኑ ስፋት አርባ አራት ሳንቲ ሜትር፥ ከፍታውም ሥልሳ ስድስት ሳንቲ ሜትር የሆነ ጠረጴዛ ከግራር እንጨት ሥራ። 24 በንጹሕ ወርቅም ለብጠው፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ አድርግለት። 25 በዙሪያው ሰባ አምስት ሳንቲ ሜትር ስፋት የሚሆን ጠርዝ አብጅለት፤ በጠርዙም ዙሪያ የወርቅ ክፈፍ አድርግለት። 26 ከወርቅ የተሠሩ አራት መሸከሚያ ቀለበቶች አድርግለት፤ ቀለበቶቹንም እግሮቹ ባሉበት በአራቱም ማእዘን አኑራቸው። 27 ጠረጴዛውንም ለመሸከም መሎጊያዎቹ የሚሰኩባቸው ቀለበቶች ከክፈፉ ጋር የተቀራረቡ ይሁኑ። 28 መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት ሠርተህ በወርቅ ለብጣቸው። 29 ሳሕኖችንና ጭልፋዎችን እንዲሁም ለወይን ጠጅ መቅጃ የሚሆኑ ማንቆርቆሪያዎችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን ከንጹሕ ወርቅ ሥራ። 30 ጠረጴዛውም በታቦቱ ፊት ለፊት ይቀመጥ፤ ለእኔ የሚቀርበው የተቀደሰ ኅብስት ዘወትር በጠረጴዛው ላይ መኖር አለበት። የመብራቱ መቅረዝ ( ዘፀ. 37፥17-24 ) 31 “ከንጹሕም ወርቅ መቅረዝ ሥራ፤ የመቅረዙን መሠረትና ዘንግ ከተቀጠቀጠ ወርቅ ሥራ፤ ለጌጥ የሚሠሩት የአበባዎች ወርድ እንቡጦችና ቀንበጦች ጨምሮ ከእርሱ ጋር አንድ ሆነው ይሠሩ። 32 በስተጐኑ ስድስት ቅርንጫፎች አውጣለት፤ ይኸውም ሦስቱ በአንድ ጐን ሲሆኑ፥ ሦስቱ ደግሞ በሌላ ጐን ይሁኑ። 33 ስድስቱም ቅርንጫፎች እያንዳንዳቸው እንቡጥና ቀንበጥ ያለው የለውዝ አበባ የሚመስል ሦስት የአበባ ወርድ ጌጥ ይኑራቸው። 34 የመቅረዙም ዘንግ እንቡጥና ቀንበጥ ያለው የለውዝ አበባ የሚመስል አራት የአበባ ወርድ ጌጥ ያለው ይሁን። 35 ከሦስቱ ጥንድ ቅርንጫፎች በእያንዳንዱ ጥንድ ሥር አንድ እንቡጥ ይኑር። 36 እንቡጦቹ፥ ቅርንጫፎቹና መቅረዙ ሁሉም አንድ ወጥ ሆነው ከንጹሕ ወርቅ ተቀርጸው ይሠሩ። 37 ለመቅረዙም ሰባት መብራቶች ሠርተህ ከፊት ለፊት በኩል እንዲያበሩ፥ ከፍ አድርገህ አስቀምጣቸው። 38 መኰስተሪያዎችንና የኲስታሪ ማስቀመጫ ሳሕኖችን ከንጹሕ ወርቅ ሥራ፤ 39 መቅረዙንና እነዚህን ሁሉ ዕቃዎች የምትሠራበት ሠላሳ አምስት ኪሎ ግራም ንጹሕ ወርቅ ይሁን። 40 በተራራው ላይ ባሳየሁህ ዕቅድ መሠረት ለመሥራት ጥንቃቄ አድርግ። |