Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 23 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ትክክለኛ ፍርድ

1 “ሐሰተኛ ወሬ አታሠራጭ፤ በሐሰት በመመስከርም ከወንጀለኛ ሰው ጋር አትተባበር፤

2 ክፉ ለማድረግ የተሰባሰቡ ሰዎችን አትከተል፤ ፍርድን ለማጣመም ከብዙ ሰዎች ጋር ተስማምተህ አትመስክር።

3 ድኻ ለፍርድ ቢቀርብ ድኽነቱን በማየት አድልዎ አታድርግለት።

4 “የጠላትህ በሬ ወይም አህያ ጠፍቶ ብታገኝ መልስለት።

5 የሚጠላህ ሰው አህያ ከጭነቱ ክብደት የተነሣ ወድቆ ብታገኝ፥ አህያውን ከወደቀበት ለማንሣት እንዲችል እርዳው እንጂ አልፈኸው አትሂድ።

6 “በፍርድ አደባባይ አድልዎ በማድረግ የድኻውን ፍርድ አታጣምበት፤

7 ማንንም በሐሰት አትክሰስ፤ ንጹሑንም ሰው በሞት አትቅጣ፤ እንደዚህ ያለ በደል የሚፈጽመውን ሰው ከቅጣት ነጻ አላደርገውም፤

8 ሰዎች ትክክለኛ የሆነውን ነገር እንዳያዩ ዐይናቸውን ስለሚያሳውርና የንጹሕ ሰዎችንም ፍርድ ስለሚያጣምም ጉቦ አትቀበል።

9 “እናንተ በግብጽ ምድር መጻተኞች ስለ ነበራችሁ መጻተኛ ምን ዐይነት ሐዘን እንደሚደርስበት ታውቃላችሁና መጻተኛውን አታጒላሉ።”


ሰባተኛው ዓመትና ሰባተኛው ቀን

10 “ስድስት ዓመት እርሻህን በማረስ ዘርተህ፥ ምርትህን ሰብስብ፤

11 በሰባተኛው ዓመት ግን በሕዝብህ መካከል የሚገኙ ድኾች ምግብ ያገኙ ዘንድ በምድሪቱ ላይ ምንም ነገር አታምርት፤ ምድሪቱ ታርፍ ዘንድ ተዋት፤ ከእነርሱ የተረፈውንም የምድር አራዊት ይመገቡት፤ የወይን ተክል ቦታህንና የወይራ ዘይት ዛፎችህንም እንደዚሁ አሳርፋቸው።

12 “በሳምንት ስድስት ቀን ሥራህን ሁሉ ሥራ፤ በሰባተኛው ቀን ግን ምንም ሥራ አትሥራበት፤ በዚህ ዐይነት አገልጋዮችህና ለአንተ የሚሠሩ መጻተኞች፥ እንዲሁም በሬህና አህያህ ዕረፍት አድርገው ይዋሉ።

13 “እኔ እግዚአብሔር የነገርኳችሁን ሁሉ በጥንቃቄ አድምጡ፤ ወደ ሌሎች አማልክት አትጸልዩ፤ ሌላው ቀርቶ ስማቸውን እንኳ አትጥሩ።


ሦስቱ ታላላቅ በዓላት
( ዘፀ. 34፥18-26 ፤ ዘዳ. 16፥1-17 )

14 “እኔን የምታከብሩባቸው በዓመት ሦስት በዓላት ይኑሩአችሁ፤

15 ከግብጽ በወጣችሁበት በአቢብ ወር፥ እኔ ባዘዝኳችሁ አኳኋን የቂጣን በዓል አክብሩ፤ ይህ በዓል በሚከበርባቸው በሰባቱ ቀኖች ውስጥ እርሾ የነካው እንጀራ አትብሉ፤ ለእኔ ልትሰግዱ በምትመጡበት ጊዜ መባ ሳትይዙ አትምጡ።

16 “የምድራችሁን ሰብል በምትሰበስቡበት ጊዜ የመከር በዓል አክብሩ፤ “ከወይን ተክሎቻችሁና ከፍራፍሬ ዛፎቻችሁ ፍሬ በምትሰበስቡበት ጊዜ በዓመቱ መጨረሻ የዳስ በዓል አክብሩ፤

17 በዓመት ሦስት ጊዜ እነዚህ በዓላት በሚከበሩባቸው ቀኖች ወንዶች ሁሉ ወደ እኔ ወደ አምላካቸው ይምጡ።

18 “እንስሳ በምትሠዉልኝ ጊዜ እርሾ የነካው እንጀራ መባ አድርጋችሁ አታቅርቡ፤ በእነዚህ በዓላት የሚሠዉት እንስሶች ስብ ለሚቀጥለው ቀን አይትረፍ።

19 “በየዓመቱ ከምታመርቱት ምርት መጀመሪያ የደረሰውን በኲራት ወደ እኔ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት አምጡ። “የበግን ወይም የፍየልን ግልገል በእናቱ ወተት አትቀቅል።


የተስፋ ቃሎችና መመሪያዎች

20 “በመንገድህ እንዲጠብቅህና እኔ ወዳዘጋጀሁልህ ምድር በሰላም እንዲያስገባህ በፊትህ የሚሄድ መልአክ እልካለሁ፤

21 የሚነግርህን በማዳመጥ ለእርሱ ታዘዝ፤ በእርሱም ላይ አታምፅ፤ ለእርሱ ሙሉ ሥልጣን የሰጠሁት ስለ ሆነ የምትፈጽመውን ዐመፅ እየተመለከተ ይቅርታ አያደርግልህም።

22 ለእርሱ ብትታዘዝና እኔ ያዘዝኩህንም ሁሉ ብትፈጽም ጠላቶችህን እጠላለሁ፤ ተቃዋሚዎችህንም እዋጋለሁ፤

23 መልአኬም ፊት ፊትህ በመሄድ ወደ አሞራውያን፥ ሒታውያን፥ ፈሪዛውያን፥ ከነዓናውያን፥ ሒዋውያንና ኢያቡሳውያን ምድር ይወስድሃል፤ እኔም እነርሱን አጠፋቸዋለሁ።

24 ለእነርሱ አማልክት በመንበርከክ አትስገድ፤ አታምልካቸው፤ ሃይማኖታዊ ልማዶቻቸውንም አትከተል፤ አማልክታቸውን አጥፋ፤ ለእነርሱ ቅዱሳን የሆኑትን የድንጋይ ዐምዶቻቸውንም አፈራርስ፤

25 ለእኔ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ብትሰግድ በቂ ምግብና ውሃ በመስጠት እባርክሃለሁ፤ በሽታህንም ሁሉ አስወግዳለሁ።

26 በምድርህ ፅንስ የሚያስወርዳት ወይም መኻን ሴት አትኖርም፤ ዕድሜህንም አረዝመዋለሁ።

27 “አንተን የሚቃወሙህ ሁሉ እኔን እንዲፈሩ አደርጋለሁ፤ በአንተ ላይ ጦርነት በሚያስነሡ ሕዝቦች ላይ ሁከት አመጣለሁ፤ ጠላቶችህ ወደ ኋላ ተመልሰው እንዲሸሹ አደርጋለሁ፤

28 በጠላቶችህ ላይ ሽብር እልክባቸዋለሁ። አንተም ወደ ፊት ስትሄድ ሒዋውያንን፥ ከነዓናውያንንና ሒታውያንን ከፊትህ አባርራለሁ።

29 ሆኖም በአንድ ዓመት ውስጥ እንዲጠፉ አላደርግም፤ ይህን ካደረግሁ ምድሪቱ ሰው አልባ ትሆናለች፤ አራዊትም ይበዙብሃል፤

30 ስለዚህ በዚህ ፈንታ በቊጥር በዝተህ ምድሪቱን እስክትወርስ ድረስ ጥቂት በጥቂት አስወጣልሃለሁ።

31 የምድርህንም ወሰን ከቀይ ባሕር እስከ ፍልስጥኤም ባሕር፥ ከምድረ በዳው እስከ ኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ እንዲሰፋ አደርጋለሁ፤ በምድሪቱ የሚኖሩትን በእጅህ እጥላለሁ፤ ከፊትህም ታሳድዳቸዋለህ።

32 ከእነርሱም ሆነ ከአማልክታቸው ጋር ምንም ዐይነት ስምምነት አታድርግ፤

33 እነዚያ ሕዝቦች በአገርህ እንዲኖሩ አትፍቀድላቸው፤ የምትፈቅድላቸው ከሆነ ግን ኃጢአት በመሥራት እኔን እንድትበድል ያደርጉሃል፤ ለአማልክቶቻቸውም ብትሰግድ ለሞት የሚያደርስ ወጥመድ ይሆንብሃል።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告