ዘፀአት 22 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየንብረት አጠባበቅ ሕግ 1 “አንድ ሰው አንድ በሬ ወይም አንድ በግ ሰርቆ ቢያርድ ወይም ቢሸጥ ስለ አንድ በሬ አምስት በሬዎች፥ ስለ አንድ በግ አራት በጎች ይክፈል። 2-3 ሌባው የሰረቀውን ይመልስ፤ የሚከፍለው ቢያጣ በባሪያነት ይሸጥ፤ የሰረቀው እንስሳ ላምም ቢሆን፥ አህያም ቢሆን፥ ወይም በግ ቢሆንና በሕይወት በእጁ ቢገኝ ለያንዳንዱ እንስሳ እጥፍ ዋጋ ይክፈል። “አንድ ሌባ ቤት ሰብሮ ሲገባ ቢያዝና ተመትቶ ቢገደል ተከላካዩ ለደሙ ተጠያቂ አይሆንም። ሌባው ሰብሮ የገባው ፀሐይ ከወጣ በኋላ ሆኖ ተመትቶ ቢገደል ግን ተከላካዩ ለደሙ ተጠያቂ ይሆናል። 4 የሰረቀው እንስሳ ላምም ቢሆን፥ አህያም ቢሆን፥ ወይም በግ ቢሆንና በሕይወት ቢገኝ ለያንዳንዱ ዕጥፍ ዋጋ ይክፈል። 5 “አንድ ሰው እንስሶቹ በመስክ ወይም በወይን ተክል ቦታ አሰማርቶ ሳለ እንስሶቹ ወደ ሌላ ሰው እርሻ ገብተው ሰብሉን ቢበሉት ከራሱ ማሳ ወይም የወይን ተክል ቦታ ከሚያገኘው ምርት ካሣ ይክፈል። 6 “አንድ ሰው በእርሻው ውስጥ እሳት ቢያቀጣጥልና እሳቱ በቊጥቋጦ ተላልፎ ወደ ሌላው ሰው እርሻ በመዛመት በማደግ ላይ ያለውንም ሆነ ታጭዶ የተከመረውን እህል ቢያቃጥል፥ እሳቱን ያቀጣጠለው ሰው ካሣ ይክፈል። 7 “አንድ ሰው የሌላውን ሰው ገንዘብ ወይም የከበረ ዕቃ በዐደራ ለመጠበቅ ተስማምቶ ከቤቱ ተሰርቆበት ሌባው ቢገኝ እጥፍ አድርጎ ይክፈል። 8 ሌባው ካልተገኘ ግን ዕቃውን በዐደራ የተቀበለው ሰው የእግዚአብሔር አገልጋዮች በሆኑ ዳኞች ፊት ቀርቦ የዚያን ሰው ንብረት አለመስረቁን በመሐላ ያረጋግጥ። 9 “ስለ ከብት፥ ስለ አህያ፥ ስለ በግ ስለ ልብስና ወይም ስለ ማንኛውም የጠፋ ዕቃ ሁለት ሰዎች ቢካሰሱ፥ ስለ ንብረቱ ባለቤትነት የተጣሉት ሁለቱ ሰዎች የእግዚአብሔር አገልጋዮች በሆኑ ዳኞች ፊት ይቅረቡ፤ እግዚአብሔር በደሉን በዳኞቹ አማካይነት የሚገለጥበት ሰው፥ ለተበደለው ሰው ዕጥፍ አድርጎ ይክፈል። 10 “አንድ ሰው የሌላውን ሰው አህያ፥ ላም፥ በግ ወይም ማንኛውንም እንስሳ በዐደራ ቢያስቀምጥና እንስሳው ቢሞት ወይም ቢሰበር ወይም ተዘርፎ ቢወሰድ፥ ምስክር ከሌለው፥ 11 ያ ሰው የእግዚአብሔር አገልጋዮች ወደሆኑት ዳኞች ዘንድ ይሂድ፤ የሰውዬውን እንስሳ አለመስረቁንም በመሐላ ያረጋግጥ፤ እንስሳው ያልተሰረቀ ከሆነ የእንስሳው ባለቤት ካሳ አይጠይቅ፤ እንስሳው የጠፋበትም ሰው ካሳ አይክፈል። 12 እንስሳው የተሰረቀ ከሆነ ግን ለባለቤቱ ይመለስለት፤ 13 እንስሳውን አውሬ በልቶት ከሆነ ሰውየው የአውሬውን ትራፊ ለማስረጃ ያቅርብ፤ አውሬ ስለ ገደለውም እንስሳ ካሳ አይክፈል። 14 “አንድ ሰው ከሌላው ሰው እንስሳ በውሰት ወስዶ ባለቤቱ በሌለበት እንስሳው ቢሞት ወይም ቢሰበር በውሰት ለሰጠው ሰው ካሳ ይክፈል፤ 15 ነገር ግን ይህ የሆነው ባለንብረቱ ባለበት ከሆነ ሰውየው ካሳ መክፈል የለበትም፤ በኪራይ መልክ የወሰደው ከሆነ የተከፈለው ገንዘብ ጒዳቱን ያካክሳል። የሥነ ምግባርና የእምነት ኅጎች 16 “አንድ ሰው አንዲት ልጃገረድን አታሎ ክብረ ንጽሕናዋን ቢደፍር ማጫ ሰጥቶ ያግባት፤ 17 የልጅትዋ አባት ሊድርለት ባይፈቅድ ግን ከአንድ ልጃገረድ ማጫ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የገንዘብ ካሣ ለልጅትዋ አባት ይክፈል። 18 “አስማት የምታደርግ መተተኛ ሴት ብትኖር በሞት ትቀጣ፤ 19 “ከእንስሳ ጋር ተገናኝቶ የሚረክስ ሰው በሞት ይቀጣ። 20 “ለእግዚአብሔር ካልሆነ በቀር ለሌላ ለማንኛውም አምላክ መሥዋዕት የሚያቀርብ በሞት ይቀጣ። 21 “እናንተም በግብጽ ምድር መጻተኞች ስለ ነበራችሁ መጻተኛውን በመጨቈን አታጒላሉ፤ 22 ባልዋ የሞተባትን መበለት ወይም አባትና እናት የሞቱበትን ድኻ ዐደግ አታጒላሉ። 23 ይህን ብታደርጉ ወደ እኔ ሲጮኹ እኔ እግዚአብሔር ጩኸታቸውን በእርግጥ እሰማለሁ። 24 በእናንተም ላይ ተቈጥቼ በጦርነት እንድታልቁ አደርጋለሁ፤ ሚስቶቻችሁ ባል አልባ፥ ልጆቻችሁም አባት አልባ ሆነው ይቀራሉ። 25 “በድኽነት ከሚኖሩት ሕዝቤ መካከል ለአንዱ እንኳ ገንዘብ ብታበድር፥ እንደ ገንዘብ አበዳሪ በመሆን ወለድ ጨምሮ እንዲከፍልህ አትጠይቀው። 26 ልብሱን በመያዣ ስም የወሰድክበት ሰው ቢኖር ፀሐይ ከመጥለቅዋ በፊት መልስለት። 27 ብርድ የሚከላከልበት ሌላ ምንም ልብስ ስለሌለው ምን ለብሶ ሊያድር ይችላል? እኔ መሐሪ ስለ ሆንኩ እርሱ ወደ እኔ ቢጮኽ እሰማዋለሁ። 28 “በእግዚአብሔር ላይ የስድብ ቃል አትናገር፤ የሕዝብህንም መሪ አትስደብ። 29 “የእህልህን፥ የወይን ጠጅህንና የወይራ ዘይትህን በኲራት ለእኔ አቅርብ፤ “በኲር ሆነው የተወለዱትን ወንዶች ልጆችህን ለእኔ አቅርብ። 30 ከቀንድ ከብቶችህ፥ ከበጎችህም በኲር ሆነው የሚወለዱትን ለእኔ አቅርብ፤ ይኸውም በኲር ሆኖ የተወለደ ወንድ ሁሉ ለሰባት ቀን ከእናቱ ጋር ይቈይ፤ በስምንተኛው ቀን ለእኔ ታቀርበዋለህ። 31 “እናንተ ለእኔ የተለያችሁ ሰዎች ትሆኑልኛላችሁ፤ ስለዚህ አውሬ በሜዳ የገደለውን የማንኛውንም እንስሳ ሥጋ አትብሉ፤ ለውሾች ጣሉት። |