Biblia Todo Logo
在线圣经

- 广告 -

ዘፀአት 21 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ለባሪያዎች ሊደረግላቸው የሚገባ አያያዝ
( ዘዳ. 15፥12-18 )

1 “ለእስራኤላውያን የምትሰጣቸው ሕግ ይህ ነው፤

2 ዕብራዊ ባሪያ ብትገዛ ስድስት ዓመት ያገልግልህ፤ በሰባተኛው ዓመት ያለ ምንም ዕዳ ነጻ እንዲወጣ አድርገው፤

3 ባሪያ እንዲሆንህ አንተ በገዛኸው ጊዜ ሚስት ያላገባ ከሆነ፥ ለቆ በሚወጣበት ጊዜ ብቻውን ይሂድ፤ ባሪያው በገዛኸው ጊዜ ሚስት አግብቶ ከሆነ ግን ሚስቱን ይዞ ይውጣ።

4 ጌታው ሚስት የምትሆነው ሴት ሰጥቶት ወንዶችና ሴቶች ልጆችን ወልዳለት ከሆነ ሴትዮዋ ከነልጆችዋ የጌታው ትሁን፤ ሰውየው ግን ብቻውን ነጻ ይውጣ።

5 ባሪያው ግን ‘ጌታዬን፥ ሚስቴንና ልጆቼን እወዳለሁ’ ብሎ ነጻ መውጣት ባይፈልግ፥

6 ጌታው የእግዚአብሔር አገልጋዮች ወደ ሆኑ ፈራጆች ዘንድ ይውሰደው፤ እዚያም ከበር ወይም ከበር መቃን አጠገብ አቁሞ ጆሮውን በወስፌ ይብሳው፤ ከዚያም በኋላ እስከ ዕድሜ ልኩ ድረስ ባርያ ሆኖ ያገልግለው።

7 “አንድ ሰው ሴት ልጁን ለባርነት ቢሸጥ እንደ ወንዶቹ አገልጋዮች ነጻ አትውጣ፤

8 ሚስት ሊያደርጋት ለፈለገ ሰው ብትሸጥና በኋላም እርሱ ሳይወዳት ቢቀር ተመልሳ በሕዝብዋ ትዋጅ ጌታዋ የማይገባ ነገር ስላደረገባት ለባዕድ ሊሸጣት አይችልም።

9 ሚስት ትሆንለት ዘንድ ለልጁ ሊሰጣት ከፈለገ ግን እንደ ሴት ልጁ አድርጎ ይቊጠራት።

10 ሁለተኛ ሚስት ቢያገባ ለመጀመሪያ ሚስቱ ምግብና ልብስ መስጠቱን አይተው፤ ቀድሞ የነበራትንም የጋብቻ መብት አይከልክላት።

11 እነዚህን ሦስት ግዴታዎች የማይፈጽምላት ከሆነ ግን ያለ ምንም ዕዳ ነጻ ይልቀቃት።


ዐመፅ የሚፈጽሙ ሰዎች ስለሚቀጡበት ሕግ

12 “ሰውን ደብድቦ የሚገድል ሁሉ በሞት ይቀጣ፤

13 ሆን ብሎ ደፈጣ በማድረግ ሳይሆን በድንገተኛ አጋጣሚ ቢሞትበት ግን ሸሽቶ በማምለጥ በሰላም የሚኖርበትን ስፍራ እኔ አዘጋጅላችኋለሁ፤

14 ይሁን እንጂ ሰው በቊጣ ተነሣሥቶና ሆን ብሎ ሌላ ሰው ቢገድል፥ ሕይወቱን ለማዳን ወደ መሠዊያዬ ሸሽቶ ቢሄድ በሞት ይቀጣ።

15 “አባቱን ወይም እናቱን የሚመታ በሞት ይቀጣ፤

16 “ሊሸጠው ወይም ባርያ አድርጎ ሊገዛው አስቦ ሰውን አፍኖ የሚወስድ ሁሉ በሞት ይቀጣ።

17 “አባቱን ወይም እናቱን የሚሰድብ በሞት ይቀጣ።

18 “ሁለት ሰዎች ቢጣሉና አንደኛው ሌላውን በድንጋይ ቢፈነክተው ወይም በቡጢ ቢያቈስለው ካልገደለው በቀር በሞት አይቀጣ፤ የተመታው ሰው ታሞ በአልጋ ላይ ቢውል፥

19 በኋላም ተነሥቶ በትር እየተመረኰዘ መራመድ ቢቀጥል፤ ስለ ባከነበት ጊዜ የመታው ሰው ካሣ ይክፈለው፤ በደንብ እስከሚድንም ድረስ ተገቢውን እንክብካቤ ያድርግለት።

20 “አንድ ሰው ወንድም ሆነ ሴት ባሪያውን በበትር ቢመታና ወዲያው ቢሞትበት መቀጣት ይገባዋል፤

21 ነገር ግን ባሪያው በአንድ ቀን ወይም በሁለት ቀን ውስጥ ባይሞት አሳዳሪ ጌታው አይቀጣም፤ ባሪያውን ማጣቱ ራሱ ቅጣት ነው።

22 “ሁለት ሰዎች ሲጣሉ አንዲት ነፍሰ ጡር መተው ቢያስወርዳትና ሌላ ምንም ጒዳት ሳይደርስባት ቢቀር፥ ያ ጒዳት ያደረሰባት ሰው የሴቲቱ ባል የሚጠይቀውን ያኽል ካሣ ይክፈል፤ ይህም የሚከፍለው ካሣ መጠን በዳኞች የጸደቀ ይሁን።

23 ነገር ግን ሴትዮዋ ራስዋ ብርቱ ጒዳት የደረሰባት ከሆነች ቅጣቱ ‘በሕይወት ምትክ ሕይወት፥

24 በዐይን ምትክ ዐይን፥ በጥርስ ምትክ ጥርስ፥ በእጅ ምትክ እጅ፥ በእግር ምትክ እግር፥

25 በቃጠሎ ምትክ ቃጠሎ፥ በቊስል ምትክ ቊስል፥ በመፈንከት ምትክ መፈንከት’ በሚለው ሕግ መሠረት ይወሰን።

26 “አንድ ሰው የወንድ ወይም የሴት ባሪያውን ዐይን መትቶ ቢያጠፋ ስለ ዐይኑ ካሣ ባሪያውን ነጻ ይልቀቅ።

27 በዚሁ ዐይነት አንድ ጥርሱን እንኳ ቢሰብር፥ ስለ ጥርሱ ካሣ ባሪያውን ነጻ ይልቀቀው።


የባለ ንብረቶች ኀላፊነት

28 “በሬ ሰው ወግቶ ቢገድል በድንጋይ ተወግሮ ይሙት፤ ሥጋውም አይበላ፤ ባለ ንብረቱም በነጻ ይለቀቅ።

29 በሬው የተዋጊነት ልማድ ያለው ቢሆንና ባለቤቱም ቀደም ሲል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት በበረት ሳይዘው ቀርቶ ቢሆን ግን በሬው ሰው በሚወጋበት ጊዜ በድንጋይ ተወግሮ ይሙት፤ ባለ ንብረቱም በሞት ይቀጣ።

30 ሆኖም ባለ ንብረቱ ሕይወቱን ለመዋጀት ካሣ እንዲከፍል ከተፈቀደለት ካሣውን በሙሉ ይክፈል።

31 በሬው ወንድ ወይም ሴት ልጅ ወግቶ ቢገድል ቅጣቱ ተመሳሳይ ይሁን።

32 በሬው ወንድ ወይም ሴት ባሪያ ወግቶ ቢገድል የበሬው ባለቤት ለባሪያው ጌታ ሠላሳ ብር ይክፈለው፤ በሬውም በድንጋይ ተወግሮ ይሙት።

33 “አንድ ሰው የጒድጓድ መክደኛ ቢያነሣ ወይም ጒድጓድ ቆፍሮ ሳይከድነው ቢቀርና በሬ ወይም አህያ ወደዚያ ጒድጓድ ቢገባ፥

34 የእንስሳውን ዋጋ ይክፈል፤ ገንዘቡን ለእንስሳው ባለቤት ከከፈለ በኋላ የሞተውን እንስሳ ለራሱ ያስቀር።

35 የአንድ ሰው በሬ የሌላውን ሰው በሬ ወግቶ ቢገድል ሁለቱ ሰዎች በሕይወት ያለውን በሬ ሸጠው ገንዘቡን ለሁለት ይካፈሉት፤ የሞተውንም በሬ ሥጋ ለሁለት ይካፈሉ።

36 ነገር ግን በሬው ተዋጊ መሆኑ ታውቆ ሳለ ባለቤቱ በበረት ውስጥ ሳይዘው ቀርቶ ከሆነ፥ በሬው ለሞተበት ሰው አንድ በሕይወት ያለ በሬ ካሣ ይክፈል፤ የሞተውንም በሬ ለራሱ ያስቀር።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
跟着我们:



广告