ዘፀአት 19 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእስራኤላውያን በሲና ተራራ 1 እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ በሦስተኛው ወር በዚያው በመጀመሪያው ቀን ወደ ሲና በረሓ ደረሱ፤ 2 እነርሱም ከረፊዲም ተነሥተው ወደ ሲና በረሓ ተጒዘው በተራራው ፊት ለፊት ባለው በረሓ ሰፈሩ። 3 ሙሴም ከእግዚአብሔር ጋር ለመነጋገር ወደ ተራራው ወጣ፤ እግዚአብሔርም ከተራራው ላይ በመናገር የያዕቆብ ተወላጆች ለሆኑት እስራኤላውያን እንዲህ ብሎ እንዲናገር አዘዘው፥ 4 “ ‘እኔ እግዚአብሔር በግብጻውያን ላይ ያደረግኹትንና ንስር ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ እንደምትሸከም እኔም እናንተን እስከዚህ ስፍራ እንዴት ወደ እኔ እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል፤ 5 አሁንም እነሆ፥ ለእኔ ብትታዘዙና ቃል ኪዳኔንም ብትጠብቁ ምንም እንኳ ምድር ሁሉ የእኔ ብትሆን የተለያችሁ ሕዝብ ትሆናላችሁ፤ 6 ለእኔም ብቻ የተለያችሁ ቅዱሳን ሕዝብ ትሆናላችሁ፤ እንደ ካህናትም ሆናችሁ ታገለግሉኛላችሁ፤’ ለእስራኤላውያን የምትነግራቸው ቃል ይኸው ነው።” 7 ስለዚህም ሙሴ ከተራራ ወርዶ የሕዝቡን አለቆች ሁሉ በአንድነት በመጥራት እግዚአብሔር ለእርሱ የሰጠውን ትእዛዝ ሁሉ ነገራቸው። 8 ከዚህም በኋላ ሁሉም በአንድ ድምፅ ተባብረው “እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ እንፈጽማለን” አሉ፤ ሙሴም ይህንኑ ለእግዚአብሔር አቀረበ። 9 እግዚአብሔርም ሙሴን “እኔ ግዙፍ በሆነ ደመና ወደ አንተ እመጣለሁ፤ ስለዚህም ሕዝቡ እኔ ከአንተ ጋር ስነጋገር በመስማት ከአሁን ጀምሮ አንተ የምትለውን ሁሉ ያምናሉ።” ሙሴም ሕዝቡ የሰጠውን መልስ ወደ እግዚአብሔር አቀረበ፤ 10 እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፥ “ወደ ሰዎቹ ሂድ፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሱ አድርገህ ታቀርባቸው ዘንድ ዛሬና ነገ ሰውነታቸውን እንዲያነጹና ልብሳቸውንም እንዲያጥቡ ንገራቸው፤ 11 በሦስተኛው ቀን በሕዝቡ ፊት በሲና ተራራ ላይ እኔ እግዚአብሔር ስለምወርድ ሁሉም በዚያ ቀን ይዘጋጁ። 12 በተራራው ዙሪያ ድንበር አብጅ፤ እነርሱም ያንን ድንበር አልፈው ወደ ተራራው እንዳይወጡና እንዲያውም ድንበሩን እንዳይነኩ ንገራቸው፤ ማንም ሰው ከተወሰነው ድንበር አልፎ፥ ተራራውን ቢነካ በሞት ይቀጣ፤ 13 ይኸውም ማንም ሳይነካው በድንጋይ ተወግሮ ወይም በፍላጻ ተወግቶ ይገደል፤ ይህን የሚያደርጉ ሰዎችም ሆኑ እንስሶች በዚሁ ዐይነት ይገደሉ፤ ሕዝቡ ወደ ተራራው መውጣት የሚገባው ለረጅም ጊዜ መለከት ሲነፋ ብቻ ነው።” 14 ከዚህ በኋላ ሙሴ ከተራራው ወርዶ ሕዝቡ ልብሱን አጥቦ እንዲቀደስ አደረገ፤ 15 ሙሴም ሰዎቹን “ለተነገወዲያው ዕለት ተዘጋጁ፤ እስከዚያም ቀን ድረስ ወደ ሴት አትቅረቡ” አላቸው። 16 በሦስተኛው ቀን ማለዳ የነጐድጓድ ድምፅ አስተጋባ፤ የመብረቅ ብልጭልጭታና ጥቅጥቅ ያለ ደመና በተራራው ላይ ታየ፤ እንዲሁም ከፍተኛ የሆነ የእምቢልታ ድምፅ ተሰማ። ሰዎቹም በሰፈሩበት ቦታ ፈርተው ተንቀጠቀጡ። 17 ሙሴም ከሰፈር እየመራ አውጥቶ ወደ እግዚአብሔር አቀረባቸው፤ እነርሱም በተራራው እግር ሥር ቆሙ። 18 እግዚአብሔር በእሳት ስለ ወረደበት መላው የሲና ተራራ በጢስ ተሞላ። ጢሱም ከእሳት ምድጃ እንደሚወጣ ዐይነት ሆኖ ወደ አየር ተትጐለጐለ፤ ሰዎቹም እጅግ ፈርተው ተንቀጠቀጡ። 19 የእምቢልታውም ብርቱ ድምፅ እያከታተለ ማስተጋባት ቀጠለ፤ ሙሴ ሲናገር እግዚአብሔር በነጐድጓድ ይመልስለት ነበር፤ 20 እግዚአብሔር በሲና ተራራ ራስ ላይ ወርዶ፥ ወደ ተራራው ጫፍ እንዲመጣ ሙሴን ጠራው፤ ሙሴም ወደ ተራራው ጫፍ ወጣ፤ 21 እግዚአብሔርም እንዲህ አለው፤ “እኔን እግዚአብሔርን ለማየት የተወሰነውን ክልል አልፈው እንዳይመጡ ወርደህ ለሕዝቡ ንገር፤ ይህን ቢያደርጉ ግን ከእነርሱ ብዙዎቹ ይሞታሉ፤ 22 ለአገልግሎት ወደ እኔ የሚቀርቡ ካህናት እንኳ ሳይቀሩ ራሳቸውን ያንጹ፤ ይህ ካልሆነ እኔ እግዚአብሔር እቀጣቸዋለሁ።” 23 ሙሴም እንዲህ ሲል ለእግዚአብሔር መለሰ፦ “ቦታው ቅዱስ ስለ ሆነ ከዚህ ራቁ ብለህ ስለ አስጠነቀቅከን ሕዝቡ ወደ ተራራው ሊወጣ አይችልም።” 24 እግዚአብሔርም “ውረድና አሮንን ይዘህ ና፤ ካህናቱም ሆኑ ሕዝቡ ወደ እኔ ለመውጣት ወሰኑን ማለፍ የለባቸውም፤ ይህን ቢያደርጉ ግን እኔ እግዚአብሔር እቀጣቸዋለሁ።” 25 ሙሴም ወደ እነርሱ ወርዶ እግዚአብሔር ያዘዘውን ሁሉ ነገራቸው። |